ቻምፒየንስ ሊግ | የአልሰላም ዋኡ ጉዳይ…

በ2018ቱ የካፍ ቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣሪያው ከደቡብ ሱዳኑ አል ሰላም ዋኡ ጋር ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርገው ጨዋታ ወደሌላ ጊዜ እንደማይሸጋገር ካፍ አስታውቋል። እስከ ዛሬ ድረስ አዲስ አበባ ያልገባው የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ጨዋታው ወደ ሰኞ እንዲራዘምለት ለኮንፌዴሬሽኑ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በፀጥታ ችግር፣ በአየር በረራዎች መሰረዝ እና በሌሎች ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ምክኒያት ክለቦች ጨዋታዎቻቸው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍላቸው ሲጠይቁ ሁኔታዎችን አገናዝቦ ጥያቄዎችን የሚቀበል ቢሆንም በክለቦች አስተዳደር ስህተት እና የዝግጁነት ችግሮችን ተከትሎ የሚደረጉ የጨዋታ ይራዘምልን ጥያቄዎችን ሲያስተናግድ አይታይም።

አል ሰላም ዋኡ በቻምፒዮንስ ሊጉ ቅድመ ማጣሪያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ትኩረት በመስጠት ተጫዋቾቹን በሆቴል ሰብስቦ ላለፉት 4 ሳምንታት ዝግጅት እያደረገ የቆየ ቢሆንም የክለቡ አስተዳደር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ቡድኑ በጊዜ ጨዋታው ወደሚደረግበት አዲስ አበባ እንዲገባ አለማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል። የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ነገ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ በኬንያ አየርመንገድ በረራ አዲስ አበባ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታውን ለማድረግ የሚገደድ ይሆናል።

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከቱኒዚያው ዩኤስ ቤን ጉዌርዴን ጋር ተደልድሎ የነበረው ሌላኛው የደቡብ ሱዳን ክለብ አል ሂላል ጁባ በተመሳሳይ ዛሬ እንዲደረግ መርሀግብር ወጥቶለት የነበረው ጨዋታ ወደ ነገ እንዲሸጋገርለት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ከሆነበት በኋላ ጨዋታውን ለማድረግ ቱኒዚያ መድረስ ባለመቻሉ ፎርፌ እንዲሰጥ ተወስኖበታል። አል ሰላም ዋኡ ነገ ከጨዋታው በፊት አዲስ አበባ መድረስ ካልቻለም ተመሳሳይ ዕጣ የሚደርሰው ሲሆን ተጨማሪ ቅጣትም በካፍ ሊጣልበት ይችላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *