ኮንፌድሬሽን ዋንጫ| ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ አቻ ተለያይቷል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎ ያደረገው ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ ከዛንዚባሩ ዚማሞቶ ጋር 1-1 ተለያይቶ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለውን እድል አስፍቷል፡፡ ድቻ በአፍሪካ የክለብ ውድድር ላይ ሲሳተፍ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ሲሆን ከሜዳው ውጪም ወሳኝ ግብ አስቆጥሮ መውጣት ችሏል፡፡

ቶጎዋዊ አጥቂ አረፋት ጃኮ ድቻን የፊት መስመር ሲመራ በአምስት አማካዮች የተዋቀረው የመሃል ክፍሉ ዚማሞቶ ላይ ለወሰደው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቁልፍ ሚና ነበረው፡፡ ወንደወሰን ገረመው በግብ ጠባቂነት ጨዋታውን ሲጀምር ተክሉ ታፈሰ፣ ሙባረክ ሽኩሪ፣ ዘላለም ኢሳያስ እና እሸቱ መና በተከላካይ መስመር ላይ ተሰልፈዋል፡፡ ከጃኮ በስተቀር አብዛኞቹ የቡድኑ ስብስብ በውድድሩ ላይ ልምድ ባይኖራቸውም ክለቡ በመጀመሪያው ጨዋታ አቻ መለያየት ችሏል፡፡

በጨዋታው ወላይታ ድቻ በኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢወስድም ወደ ግብ በመድረስ እና ሙከራ በማድረግ በተቃራኒው ዚማሞቶዎች ተሽለው ታይተዋል፡፡ ባለሜዳዎቹ በ31ኛው ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ መሪነትን ጨብጠዋል፡፡ ሃኪም ካሚስ አሊ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ዚማሞቶን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ድቻዎች በኳስ ቁጥጥራቸው ቀጥለው የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አረፋት ጃኮ የአቻነቷን ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ዳግም በቀለ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ የዚማሞቶ ግብ ጠባቂ ናሶር ሚርሾ ሳሊም ሲተፋ በቅርብ ርቀት የነበረው ጃኮ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡ ጃኮ በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ላይ የመጀመሪያ ተሳትፎ እያደረገ ለሚገኙት የጦና ንቦች የመጀመሪያ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከእረፍት መልስ በተለይ ዚማሞቶች ከ16.50 ውጪ በሚያገኟቸው የቅጣት ምቶች ውጤቱን ለመለወጥ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ወላይታ ድቻ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ለመልስ ጨዋታ የሚረዳውን ወሳኝ ውጤት አስጠብቆ መውጣት ችሏል፡፡

ወላይታ ድቻ እና ዚማሞቶ የመልስ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ያገኘው የመጀመሪያ ውጤት ከቅድመ ማጣሪያ ዙሩ እንዲያልፍ ሁኔታዎችን የሚያመቻችለት ሲሆን ወደ አንደኛው ዙር ማለፍ ከቻለ የሚገጥመው ሃያሉን የግብፅ ክለብ ዛማሌክን ይሆናል፡፡ የቡድኑ አባላት ነገ አመሻሽ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *