የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የገንዘብ እና የ3 ወር ቅጣት ተላለፈባቸው

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ደደቢት ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ  2-1 ከተረታበት ጨዋታ በኋላ የደደቢቱ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በዕለቱ ዳኛ ላይ የሰነዘሩት አስተያየት ተከትሎ በዕለቱ የጨዋታው ኮሚሽነር በሚቀርብ ሪፖርት መነሻነት ከበድ ያለ ቅጣት የፌዴሬሽኑ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ሊያስተላልፍ እንደሚችል የተጠበቀ ሲሆን የካቲት 1 የዲሲፒሊን ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ላይ በቀነ ቀጠሮ በይደር ያቆየውን ጉዳይ ከመረመረ በኋላ በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ላይ የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና ለ3 ወር ያህል ቡድኑን እንዳይመሩ ከበድ ያለ ውሳኔ አስተላልፏል። ውሳኔውን ተከትሎ ደደቢት በ15ኛ ሳምንት ከመከላከያ ጋር ካለው ጨዋታ ጀምሮ ቡድናቸውን ሊመሩ እንደማይችሉ የታወቀ ሲሆን በቀጣይ በሚኖሩ ጨዋታዎች በምክትል አሰልጣኞቹ ደብሮም ሀጎስ እና ጌቱ ተሾመ ቡድኑን የሚመሩ ይሆናል።

የደደቢት እግርኳስ ክለብ በውሳኔው ዙርያ ይግባኝ ይጠይቃል ብለን ላነሳነው ጥያቄ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደ መስቀል ሲመልሱ ” ስህተት ተሰርቶ ይግባኝ የምንጠይቅበት ምንም ምክንያት የለም። ከስህቶቻችን እየተማርን እንሄዳለን ፤ አስቀድመን ቢሆንም ፌዴሬሽኑ በሚያስተላልፈው ማንኛውንም ውሳኔ በፀጋ እንደምንቀበል መግለፃችን ይታወቃል። ” ብለዋል

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በወቅቱ የሰጡት አስተያየት ትክክል እንዳልነበረ እና ” በስሜት ሆኜ የተናገርኩት በመሆኑ በይፋ ይቅርታ እጠይቃለው” ማለታቸው ይታወቃል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *