​” አሁን ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ” መሐመድ ናስር

መሐመድ ናስር ያለፉትን 12 አመታት በጅማ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መከላከያ ፣ ኒያላ ፣ ኢትዮ ኤሌትክሪክ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ኢትዮዽያ መድን ፣ ኢትዮዽያ ቡና ፣ በሱዳን አሃሊ ሸንዲ እና ጅማ አባቡና መጫወት የቻለ ስኬታማ ተጨዋች ነው። በዘንድሮ ውድድር አመት ዘግይቶ ፋሲል ከተማን የተቀላቀለው መሐመድ ናስር አመዛኝ የጨዋታ ሳምንታትን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ነው ያሳለፈው ። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን ወደመጀመርያ ተሰላፊነት በመመለስ ከረጅም ወራት በኋላ ወደ ጎል አስቆጣሪነት በመመለስ ሁለት ተከታታይ ጨዋታ ላይ ጎል አስቆጥሯል። መሐመድ ናስር አሁን ስላለበት ወቅታዊ አቋም ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ጥሩ ቆይታ አድርጓል።

ከፋሲል ጋር እስካሁን ያለህ ቆይታ ምን ይመስላል ?

ከፋሲል ጋር የአንድ አመት ኮንትራት ተፈራርሜ ከቡድኑ ጋር የተቀላቀልኩት ዘግይቼ ነው። ከዛም በኋላ ብዙም የመሰለፍ እድል አላገኘውም። በ13 ጨዋታ 18 ውስጥ ብገባም የቋሚ ተሰላፊነት እድል አላገኘሁም። እስካሁን ታግሼ እዚህ ደርሻለው። በእግርኳስ ህይወቴ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም። አንድ ሁለት ጨዋታ ላይ ትቀመጣለህ ፤ ሆኖም ሲደጋገም በስነ ልቦናው ረገድ ትጎዳለህ። ደጋፊውም ከእኔ ብዙ  ጠብቆ ነበር። ሆኖም ብዙ ሊያየኝ አልቻለም። ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። አሁን ጥሩ ነገር አለ ደስተኛ ነኝ።


ልምድ ያለህ በብዙ ክለቦች ያገለገልክ ተጨዋች ነህ። ሆኖም በ13 ጨዋታ ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ማሳለፍህን እንዴት ታየዋለህ? ያሳደረብህስ ተፅእኖ አለ ?

በእርግጥ እኔ ጀማሪ ተጨዋች አይደለሁም ፣ ጀማሪ ተጨዋች ባልሆንም ብዙ ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የመቀመጥ ልምድ የለኝም። ሁለት ሦስት ደቂቃ ተቀይሮ የመጫወትም ልምድ ራሱ እንኳ የለኝም። ማንም ሰው መጫወት ነው የሚፈልገው። ለእኔም ይህ ነገር ገርሞኝ ምን ሆኜ ነው እያልኩ አስብ ነበር። ከቡድኑ ጋር ሁሉ ለመለያየት አስቤ ነበር። ልጄን እና ባለቤቴን ትቼ መጥቼ ባለመጫወቴ ደስተኛ አልነበርኩም። እግርኳስ ብዙ ነገር ያስተምርሃል ፤ ሁሌ የተመቸ እና አልጋ ባልጋ ሊሆን አይችልም ።  በመጨረሻ ግን ይህ ህዝብ እኔ ማነኝ የሚለውን ነገር ለማሳየት ጊዜው ሩቅ እንደማይሆን እጠብቅ ነበር። በመጨረሻም አሰልጣኙ አምኖብኝ የቋሚ ተሰላፊነት እድሉን ስለሰጠኝ አመሰግናለው ።


አሁን በሁለት ጨዋታ ላይ ወደ ቋሚ ተሰላፊነት መጥተህ በሁለት ጨዋታ ሁለት ጎል አስቆጥረሀል። ወደ ቋሚ ተሰላፊነት መምጣትህ ይህን እንዴት ታየዋለህ ?

እኔ በእግርኳስ የማምነው አንድ አሰልጣኝ የአንድ ቡድን ራስ ነው። አሰልጣኙ እኔን ያላጫወተበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል። ያው እሱን በማክበር ነበር ሁለትም ሦስትም ደቂቃ ሲቀረው ሲያስገባኝ ተነስቼ አንድ ነገር ለማሳየት እሞክር የነበረው ። ሆኖም አሁን ጊዜው ደረሰ እና በሁለቱ ጨዋታ ላይ በጣም የተሻለ ነገር ባላሳይም አጥቂ ብዙ ጊዜ ራሱን የሚገልፀው ጎል በማስቆጠር ነው። እኔ በተቀያሪ ወንበር ተቀምጬ እድል የተሰጣቸው አጥቂዎች እረጅም ጊዜ ጎል ማስቆጠር አቅቷቸው ሲቸገሩ አይ ነበር ። እኔም ገብቼ ላይሳካ እንደምችል እገምታለው እግርኳስ ስለሆነ ያው ፈጣሪ እረድቶኝ የተሻለ ነገር በማሳየቴ ደስተኛ ነኝ።


ቀድሞ በነበርከረባቸው ክለቦች በርከት ያሉ ጎሎችን ታስቆጥር ነበር። ሆኖም አምናና ከጅማ አባቡና ጋር ሁለት ጎል ዘንድሮ ከፋሲል ጋር ምንም እንኳ ቀጣይ ጨዋታዎች ቢኖርም እስካሁን ሁለት ጎል ብቻ አስቆጥረሀል ። ይህ የሚያሳየው የጎል አስቆጣሪነትህ አቅም እያነሰ መምጣቱን ነው  ?

ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅከኝ። በእግርኳስ ህይወቴ በጣም የሚቆጨኝ የባለፈው ውድድር አመት ነው። ምክንያቱም ለ11 አመት ከትውልድ ከተማዬ ርቄ ነበር የተጫወትኩት። ጅማ አባቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ መጥቶ ሄጄ ለመጫወት አሰብኩ። ህዝቡም ደግሞ በጣም ጠብቆኝ ነበር ። በተፈጥሮዬ ብዙ ጉዳት የለብኝም ሆኖም የተለያዩ ጉዳቶች አጋጥመውኝ በዘጠኝ ጨዋታ ላይ ብቻ ተሰልፌ ሁለት ጎል አስቆጥሬያለው ። ብዙ አልተጫወትኩም ጉዳት ስለነበረኝ ሌላው አሰልጣኙ ከአሜ ጀርባ ያጫውተኝ ስለነበር በርከት ያሉ ጎሎችን እንዳላስቆጥር ሆኛለው ። አንድ አጥቂ የሚፈተነው በጨዋታ ነው። ሰው እድሜው እየጨመረ ሲመጣ እንቅስቃሴው ሊገደብ ይችላል። ሆኖም ጎሉን ያጣዋል ብዬ አላስብም። እኔ በተፈጥሮዬ እየሮጥኩ የምጫወት ተጨዋች ነኝ። 10 አመት ሮጫለው መሮጥ ካቃተኝ ደግሞ ወደ ቤት ነው የምሄደው። በእግርኳስ ማጭበርበር አልፈልግም። አሁንም ያለው ነገር ሰው ወደ ሜዳ ከገባ ይጫወታል። ቤንች ላይ ተቀምጦ ጎል አያስቆጥርም ይሄን አምናለው።


የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች ምን ማለት ትፈልጋለህ? እንዴትስ አየሀቸው ?

የደጋፊውን ስሜት በሁለት ጨዋታ ነው ያየሁት ፤ ፍፁም ልዩ ናቸው። የቡናን ደጋፊ ነው የሚያስታውሱኝ እና እውነት ነው የምነግርህ የውሸት ተናግሮ መኖር አልፈልገም። የሌላቸውን ነገር አልናገርም። የእውነት ነው የምነግርህ ትላልቅ ወንዶች ፣ ትላልቅ ሴቶች ፣ ህፃናት የቤታቸውን መጋረዣ ሳይቀር የፋሲልን አርማ አድርገው ስታይ በጣም ትገረማለህ። ስለ ቡድኑ የሚያወሩ መነኩሴ ገጥሞኛል። በጣም ከባድ ስሜት ነው ያላቸው። ትልቅ ክለብ ትልቅ ደጋፊ ነው ብዬ አስባለው። እንደዚህ ባለ ክለብ ገብተህ የተሻለ ነገር ሰርተህ ማለፍ አስፈላጊ ነው  ፣ ጥሩ ነገር ሰርተህ ሌሎች ታዳጊዎችን አፍርተህ መሄድ ጥሩ ነው እኔ ነገ ከዚህ ልሄድ እችላለው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *