የአሰልጣኞች ገጽ | የአስራት ኃይሌ 40 አመታት የዘለቀ ስኬታማ ጉዞ [ክፍል 3]


አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በአሰልጣኞች ገጽ አምዳችን ለ40 አመታት የዘለቀው የስራ ህይወት ተሞክሯቸውን ፣ እምነታቸውን እና መንገዳቸውን  በስፋት በሁለት ክፍሎች አጋርተውናል። በዛሬው 3ኛ ክፍል ደግሞ ረጅሙን እና የመጨረሻውን ቆይታችንን እናካፍላችኋለን።


በሚልኪያስ አበራ እና አብሀርም ገብረማርያም


ክፍል አንድ | Link

ክፍል ሁለት | Link

(ክፍል ሁለትን በአሰልጣኝነት ዘመናቸው የ”አስራት” እና “ስዩም” የስልጠና መንገድን በተመለከተ ባብራሩት ምላሽ ነበር የቋጨነው።)

ሁለቱን የአጨዋወት መንገድ በመቀላቀል ( “የአካል ብቃትን መሰረት ያደረገ ” እና ” ኳስን መሰረት ያደረገ” ) የመጠቀም ዝንባሌን ያሳየ አሰልጣኝ ነበር?

ሐጎስ ደስታ በሁለቱም የአጨዋወት መንገዶች የሚቀርብ ቅይጥ ዘዴን የሚከተል አሰልጣኝ ነበር፡፡ ካሳሁንና ስዩም የኳስ ቁጥጥር የበለይነት ላይ ያመዝናሉ፡፡ በውጤት ረገድ ግን እኔ ለተከታታይ ዘጠኝ አመታት ስኬታማ ሆኛለው፡፡ ስለዚህ የእኔ መንገድ የተሻለ ነበረ ማለት ነው ብዬ አምናለው፡፡


በእርስዎ የጨዋታ አቀራረብ ስኬታማ መሆን ምክንያት ተጽዕኖ ያረፈባቸው አሰልጣኞች ነበሩ?

የሀጎስ አየር ሐይል የኔ አይነት አጨዋወትን ይተገብር ነበር፡፡ በመስመሮች በማጥቃት፣ የተጋጣሚ አጨዋወት ላይ በመዘጋጀትና በአካል ብቃት ጠንካራ ቡድን በማቅረብ ሀጎስ በተሻለ ለእኔ የቀረበ መንገድን ይከተል ነበር፡፡


በስልጠና ወቅት ተጫዋቾች በዋነኝነት እንዲረዱ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አጥብቀው የሚሹት ነገር ምንድን ነው?

ለምፈልገው የጨዋታ ስርዓት ሁሉም ተጫዋቾች ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲሰጡኝ እፈልጋለው፡፡ የምናገረውንና የማስረዳውን መሠረታዊ ነገር እንዲገነዘቡ እሻለው፡፡ ሳስረዳ ሀሳቡ ከኔ ጋር የማይሆን ተጫዋች አልፈልግም፡፡ በቡድን የጨዋታ እንቅስቃሴ ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ በሚኖራቸው ሚና ላይ ያላቸውን ግንዛቤና አረዳድ መገምገም እፈልጋለው፡፡ ይህንንም በልምምድ ወቅት በትክክል እንዲተገብሩት እፈልጋለው፡፡ ለስህተቶችም እርማት እሰጣለው፡፡ በልምምድ ወቅት በቀጣይ ጨዋታ ላይ የተሻለ ታክቲካዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደጋጋሚ ትምህርቶችን አስተምራለው፡፡ ተጫዋቾቼ በደንብ እንዲገባቸው እፈልጋለው፡፡ በምነግራቸው ነገሮች ላይም እንዲወያዩበት አደርጋለሁ፡፡ የተረዱበትን መጠንም ለማወቅ ጥያቄዎችን እጠይቃቸዋለው፡፡ በሜዳ ውስጥ የተጋጣሚ ቡድኖችን አሰላለፎች እንዲሁም የተጫዋችችን የግል ብቃት እንዲያዩ አዛቸዋለው፡፡


ስኬታማ አሰልጣኝ ቢሆኑም ጫናዎቸን የሚጋፈጡባቸው ወቅቶች ይኖራሉና በምን  መልኩ አሳለፏቸው?

የሚገርመኝ ጉዳይ ውጤት እያመጣሁም ጫናዎችን አስተናግድ ነበር፡፡ ከአጨዋወት ዘይቤዬ ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ድሌን የማጣጣል ነገሮች እና ውጤቱን ያገኘሁበትን መንገድ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የማኮሰስ ስራ  ይሰራብኝ ነበር፡፡ጋዜጦች ላይ በሚወጡና የአጨዋወት ስልቴን የሚነቅፉ ጽሁፎችን በመመልከት በጋዜጦቹ ፍላጎትና ሐሳብ አጨዋወቴን እንድቀይር የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሸንፌ እየወጣሁም የሚሰድቡኝ እና የሚያወግዙኝ ብዙዎች ነበሩ፡፡ እኔ ግን በአቋሜ የምጸና ሰው ነኝ፡፡ በጫና የምበረግግ እና ሰኬታማ የሚያደርገኝን መንገድ የምቀይር አሰልጣኝ አይደለሁም፡፡ በአካል ብቃት ልምምዴ ላይ የነበረብኝ የትችት ውርጅብኝም ከመጠን በላይ ነበር፡፡ ከአሰልጣኞችም ራሱ ከፍተኛ ትችት ይገጥመኝ ነበር፡፡ ጋዜጦችም በብቃት መዉረድ ምክንያት ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾችን ቃለ መጠይቅ እያደረጉ እኔን ጫና ውስጥ ይከቱኝ ነበር፡፡ ዋንጫዎችን አሸንፌም ከክለቦች የለቀኩባቸው ጊዜዎችን አሳልፌአለው፡፡ ሆኖም በማምንበት ነገር በመጽናቴ፣አሸናፊ በመሆኔ እና በስነ ልቦና ዝግጅቴ ስሜቴ አልተጎዳም፡፡ እንዲያውም ይበልጥ እየጠነከርኩ ሄድኩ፡፡ውጤታማ የአሰልጣኝነት ህይወት ባሳልፍም መንገዶች ሁሉ አልጋባልጋ አልነበሩም፡፡


ቅዱስ ጊዮርጊስን በ1993 ከለቀቁ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ሊይዙ እንደነበር በወቅቱ በጋዜጦች ተጽፎ አንብበናል፡፡ የእርስዎ እና የቡና የአጨዋወት ልዩነትን በምን መንገድ ሊያስማሙ አስበው ነበር? ቡናን ሊይዙ ነው ሲባል ስለደረሰብዎ የግድያ ዛቻስ ምን ይላሉ ?

በእርግጥ እኔ ቡድኑን ብይዘው ውጤታማ አደርገው ነበር፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እስካሁን ድረስ በወሬ ደረጃ ይነገራል እንጂ አንድም የቡና ሰው ደጋፊም ይሁን በአመራር ደረጃ ያለ አካል እኔን ያናገረኝ አልነበረም፡፡ ቡናን እንዳሰልጥን የቀረበልኝ ጥያቄ የለም፡፡ በጋዜጦች ግን የተጻፈ ይመስለኛል፡፡ በዚህ መረጃ መሰረት  እንግዲህ የቡና ደጋፊዎች ይመስሉኛል ”ቡናን ብትይዝ እንገድልሀለን፡፡” ይሉኛል፡፡ እኔም ”አይ ፉከራው እንኳን ይቅር፤ የ’እንገድልሀለን’ ዛቻም ለእኔ አዲስ አይደለም፡፡” አልኳቸው፡፡ ቡና ኢትዮጵያዊ ክለብ ነው፡፡ ቢጠይቁኝ 100% እገባ ነበር፡፡ ብዙ ክለቦችን አሰልጥኛለሁ፡፡ በቡናም ሰርቼ ውጤት የማላመጣበት ምክንያት የለም፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ከቡና የጠየቀኝ አካል የለም፡፡ በስልክ ዛቻ ያደረሰብኝ ሰውዬም ገናለገና ‘ቡና ይገባል’ ብሎ ደንብሮ ይሆናል የደወለልኝ፡፡


ተጫዋቾቻችን በውጪ ሀገሮች የተሳካ የእግርኳስ ህይወት የማይኖራቸው ለምን ይመስልዎታል? ከእንናንተ ቀደም ያለ የአሰልጣኝነት ጊዜ ይልቅ በአሁኑ ወቅት የሚታየው መጠነኛ መሻሻልስ?

ቀደም ባለው የአሰልጣኝነት ጊዜዬ ተጫዋቾቻችን ወደ ዉጪ እየሄዱ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች የመሞከር እድል ሲገጥማቸው እምብዛም አልተመለከትኩም፡፡ በርግጥ ከኔ ተጫዋቾች ባዩ ሙሉ በቤልጂየም ጥሩ ቆይታ አድርጓል፡፡ እኔ ጋር በነበረ ጊዜ በአካል ብቃቱ ረገድ የሰራው ስራ ተጠቃሚ ያደረገው ይመስለኛል፡፡ አሸናፊ ሲሳይም እንዲሁ ሞክሮ በ Home Sickness ምክንያት በቶሎ ተመልሷል፡፡ አሸናፊ ቤተሰቦቼን በማለት ጥሎ መጣ፡፡ ተስፋዬ ኡርጌቾም ጥሩ ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡ እንደተረዳሁት ተስፋዬ በፊንላንድ የነበረውን ቅዝቃዜ መቋቋም አልቻለም፡፡ ደህና የእግር ኳስ አገር ሄዶ ጥሩ የሰነበተው ባዩ ሙሉ ነው፡፡ ሴካፋ ዋንጫ ስናገኝም የቡድኑ ቋሚ ነበር፡፡


ተጫዋቾቻችን አዳዲስ የሆኑ እግርኳሳዊ ሐሳቦችን ተረድተው ተግባራዊ የማድረግ አቅማቸው ምን ያህል አድጓል?

የቀድሞዎቹ ተጫዋቾች አዳዲስ ሀሳቦችንና ስልጠናዎችን በደምብ የመረዳት አዝማሚያን ያሳያሉ፡፡ የአሁኖቹ ግን በሬዲዮ ከሚሰሙት እና  በቴሌቪዥን ከሚያዩት አንፃር ይመስለኛል ራሳቸውን በጣም አዋቂ አድርገው ያያሉ፡፡ የሚያወሩት እና የሚተገብሩት ለየቅል ነው፡፡ መሠረታዊ በሆኑ ጥያቄዎች ላይ የሚሰጡህ ምላሽም አጥጋቢ አይደለም፡፡ አንድ አጥቂ በመከላከል እና በማጥቃት የጨዋታ ሒደቶች ውስጥ ያሉትን ድርሻዎች ጥቀስልኝ ብትል ከሁለት ዓረፍተ ነገሮች በላይ በሆነ ዝርዝር የተብራራ መልስ አይመለስልህም፡፡ በውይይት ወቅትም ፍላጎት አታይባቸውም፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ጥሩ ይናገሩና ትግበራው ላይ ይቸገራሉ፡፡ በእኔ ስር ካለፉት ሳላዲን ባርጌቾ ጥሩ ይገነዘባል፡፡ ኡመድ ኡኩሪም በደምብ ይረዳሀል፡፡ ከቀድሞዎቹ ደግሞ ፋሲል፣ ዘሪሁን፣ አሸናፊ፣ ዳኛቸው ደምሴ፣ ዮሀንስ ሳህሌ እና ሰለሞን (የዩኒቨርስቲው) በእጅጉ ይረዱኝ ነበር፡፡


ከጨዋታ በፊት ስለ ተጋጣሚ ቡድን ግምገማ የሚያደርጉት እንዴት ባለ ሁኔታ ነው?

ቀጣይ ተጋጣሚዬን ስታዲየም በመገኘት አያለው፤ እገመግማለው፡፡ ከአሰላለፋቸው ጀምሬ ቅያሪዎችን እንዲሁም ደካማና ጠንካራ ጎኖችን በአግባቡ ለይቼ በልምምድ ወቅት ለተጫዋቾቼ መረጃዎችን እሰጣለው፡፡ በየልምምዱ በተጋጣሚያችን ላይ ያየኋቸውን ነገሮች በሙሉ ለተጫዋቾቼ አሳያለው፡፡ ከጨዋታው በፊት ባለው የመጨረሻው ቀን ልምምድ ወቅት ሰፊ ውይይት እናደርጋለን፡፡ ከሳምንት ጀምሮ የሰራናቸውን ልምምዶች ተንተርሰን በጨዋታው ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ክለሳ እናደርጋለን፡፡


በተጫዋችነት ዘመናቸው ጥሩ አሰልጣኝ ይሆናሉ ብለው የጠበቋቸውና ሆነው ያገኟቸው ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

በተጫዋችነት ዘመናቸው ጥሩ አሰልጣኝ ይወጣቸዋል ብዬ ያሰብኳቸው እነ ፋሲልና ዘሪሁን ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ባዩ ጥሩ ይጓዛል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ እስካሁን አሰልጣኝ አልሆነም፡፡ ገብረመድህን ጥሩ ይናገር ነበር፡፡ እንዳሰብኩትም የተሻለ አሰልጣኝ እየሆነ ነው፡፡ በብሔራዊ ቡድን ካገኘኋቸው ደግሞ እነ ደብሮም፣ ጌቱ እና እድሉ ጥሩ ጀምረዋል፡፡ በተጫዋችነት ዘመናቸው ጠያቂዎች፣ ለማወቅ እና ለመረዳት ዝግጁ የነበሩ ናቸው፡፡ ከበረቱ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡


በግንዛቤያቸው፣ በመሪነት ብቃታቸው እና ኃላፊነትን በአግባቡ በመወጣት ረገድ አሰልጣኝ እንዲሆኑ ፈልገው ያልሆኑትስ?

በምን ምክንያት ከኳስ እንደራቁ ባላውቅም አስቤያቸው አሰልጣኝ ያልሆኑም አሉ፡፡ የኔን ፈለግ ተከትሎ የት ይደርሳል ብዬ የጠበቅኩት በህንፃ ያሰለጠንኩት ጌታቸውን ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአዕምሮ ጤና ችግር ገጥሞታል፡፡ ጥሩ ተጫዋችና በሳል ተናጋሪ ነበር፡፡ ከሱ በመቀጠል በትልቁ ያሰብኩት ባዩ ሙሉን ነው፡፡ አሁን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መሪ ሆኗል፡፡ ባዩ አስተያየት ሲሰጥና ሐላፊነት ሲወስድ ጎበዝ ነበር፡፡ ሳገኘውም ‘ለምንድነው ከትንንሽ ልጆች ጀምረህ ወደ ስልጠናው የማትገባው?’ እያልኩ እቆጣዋለሁ፡፡

በቀደመው የአሰልጣኝነት ጊዜያችሁ የነበረውን ተደራራቢ ኃላፊነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዴት ይገልፁታል?

በእኛ ጊዜ የአሰልጣኞች አባላት ቁጥር እንዲህ እንዳሁኑ ብዙ አልነበረም፡፡ በሒደት እና በእግርኳስ እድገት የመጣ ይመስለኛል፡፡ በተጫዋቾችም ዘንድ እምብዛም የማሰልጠን ፍላጎት ስላልነበረ ከተጫዋችነት ህይወት በኋላ ወደ ስልጠናው የሚገባው ጥቂቱ ነው፡፡ ከእኔ የተጫዋችነት ዘመን ጓደኞቼ እንኳ ወደ ስልጠናው የገባነው በቁጥር አምስት አካባቢ ነን፡፡ እኔ፣ ስዩም፣ ካሳሁን፣ መንግሥቱ እና ሐጎስ ነበርን ፡፡ ወደ ኋላ ንጉሴ ገብሬ መጥቶ ብዙም ሳይገፋበት ተወው፡፡ በትልልቅ ክለቦች የምንሰራውም እኛው ነበርን፤ መንግሥቱ በመብራት ሐይል፣ ካሳሁን በመድን፣ ስዩም በቡና፣ ሐጎስ በአየርሐይል እና ሌላኛው ትልቅ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ማንያዘዋል በኦሜድላ ጠንካራ ፉክክር እናደርግ ነበር፡፡ ገዛኸኝ በአካል ብቃቱ በኩል ጠንካራ ቡድን ሲሰራ አስታውሳለው፡፡ የባለሙያ እጥረትም ስለነበር ዋናው አሰልጣኝ በርካታ ስራዎችን እንዲሰራ ስለሚገደድ ከፍ ያለ የስራ ጫና ያርፍበታል፡፡ ምክትል አሰልጣኝና የበረኛ አሰልጣኝ ብታገኝ እንኳ ተጫውቶ ያላለፈ በመሆኑ ብዙ ላያግዝህ ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ አካባቢህ የሚገኘው የስራ ድርሻው አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የቡድን መሪ ነው፡፡ በእርግጥ በሒደት በዘመናዊ እግርኳስ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በብዙ ባለሙያዎች የመታገዝ እድል ታገኛለህ፡፡ በቅርቡ በአላሙዲ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ የሴካፋ ውድድር በስሬ ሶስት አሰልጣኞች-ሰዉነት ቢሻው፣ገ/መድህን ሐይሌና የበረኛ አሰልጣኝ ንጉሴ በስራዬ አግዘውኛል፡፡ እንደየሐላፊነታችን የስራ ክፍፍል በማድረግ በዋና አሰልጣኙ ላይ የሚኖረውን ጫና ቀንሰናል፡፡ በፊትማ እኮ የማሟሟቁ ፣ የአካል ብቃቱ፣ ዋናው የማዋሀድና  የታክቲክ ስራ አልፎ አልፎ ወጌሻነቱም ጭምር በዋናው አሰልጣኝ ላይ ይጫናል፡፡ የሆነ ወቅት ላይ ቃሬዛ ጠፍቶ የተጎዳ ተጫዋችን እኔ ራሴ ተሸክሜ ከሜዳ ያስወጣሁበት አጋጣሚ አለ፡፡ ‘አስራት አምቡላንስ ሆነ፡፡’ ተብሎም ተፊዟል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ያለፍንበት ሁኔታ ብዙ ችግሮችን አሳይቶናል፡፡ አንዳንዴ አሰልጣኞች ‘ሁሉንም ነገር አኔ ልያዘው፡፡’ የሚሉበት አሰራር ብዙ የሚያስኬድ አይመስለኝም ፡፡ በራስ ካለመተማመን ችግር ጋር አያይዘዋለው፡፡ ስራዬን ይሻማብኛል ብለህ መፍራት ሳይሆን ያለብህ በባለሙያ በመታገዝህ ተጠቃሚ መሆንህን መረዳት አለብህ፡፡


ለወጣት ተጫዋቾች እድል በመስጠትና በበዛ ደጋፊ ፊት በማጫወት ረገድ የተወጡት የአሰልጣኝነት ድርሻ ምንድነው?

በወጣት ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ እነ ፋሲልን፣ ዘሪሁን እና አሸናፊን ከቀድሞዎቹ ፤ እነ ኡመድን ደግሞ ካሁኖቹ ያሳደኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ባዩንም ከC ቡድን በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን ያሻገርኩት እኔ ነኝ፡፡ ወጣት ተጫዋቾች ሀላፊነት መሸከም እንዲለምዱ በማሰብ በቡድኔ ውስጥ እንደነ ሙሉጌታ ከበደ እና ገ/መድህን ሐይሌ የመሳሰሉ  ትልልቅና ነባር ተጫዋቾች እያሉ በአምበልነት የመረጥኩት ፋሲልን ነበር፡፡ ወጣቶች ትኩስ ጉልበት አላቸው፤ ታዛዦችም ናቸው፤ በእነሱ ላይ የምትፈልገውን እንድትሰራ ያስችሉሀል፡፡ ሳላዲን ባርጌቾን እንመልከት፡፡ በመብራት ሐይል እያለው ከC ወደ A አሳደኩት፤ በዚህም ምክንያት ‘እንዴት ያለ እድሜው በዋናው ቡድን ውስጥ እድል ይሰጠዋል?’ በሚል ጥያቄዎች ይነሱብኝ ጀመር ፡፡ ‘መታየት ያለበት የልጁ ችሎታ እንጂ እድሜው አይደለም፤ በዋናው ቡድን ውስጥ ካሉት ልጆች ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡’ ስል ተሟገትኩ፡፡ ክለቡን ከለቀኩ በኋላ ያደጉትን ወጣቶች ከቡድኑ አስወጧቸው፡፡ ሳላዲን መድንን እያሰለጠንኩ ‘ጋሼ እድል ይሰጠኛል’ ብሎ በማመን እኔ ጋር መጣ፡፡ ተቀበልኩት፤ ጥሩ ተጫዋች ወጣው፤ ብሔራዊ ቡድን ተጫወተ፤ አሁን ያለበት ደረጃም ደረሰ፡፡ ሳላዲን ወደ መድን የመጣው በነፃም ቢሆን የመጫወት እድል አግኝቶ ራሱን የማሳየት ፍላጎት ስለነበረው ነው፡፡ የተጫዋቹን ሞራል መጠበቅ ስለነበረብኝ በ10ሺህ ብር ለሁለት አመት እንዲፈርም አደረኩት፡፡ ዛሬ በትልቅ ክለብ የሚጫወት ትልቅ ተጫዋች ሆኗል፡፡

የኡመድም ታሪክ ተመሳሳይ ነው፡፡ በሲዊድን አገር በሚደረግ ከ17 አመት ውድድር ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ከጋምቤላ ተመልምሎ ይመጣል፡፡አሰልጣኙ ስዩም ነበር፡፡ ልምምዳቸውን በአቃቂ አካባቢ ያደርጋሉ፡፡ ኳስ አያያዙ እና ፍጥነቱ አይኔ ስለገባ ይህ ልጅ ጥሩ ቦታ ይደርሳል ብዬ አሰብኩ ፡፡ ጥሩ ተፎካካሪዎች ስለነበሩት ኡመድ አልተሳካለትም፤ ተቀነሰ፡፡ በመቀነሱ አዝኖ አንገቱን ደፍቶ ሲሄድ ጠራሁት፡፡ በወቅቱ እኔ የመከላከያ አሰልጣኝ ነበርኩ፡፡ ‘እወስድህና መከላከያ አስገባሀለው’ አልኩት፡፡ ደስተኛ ሆነ፡፡ ወደ ክለቡ ካምፕ አስገባሁት፡፡ ትንሽና ገራገር ብጤ ስለነበር  በነፃ ጥሩ መስራት ጀመረ፡፡ 5ሺ ብር እንዲሰጡት ጠየኩለትና ሲፈቀድለት ‘ይህ ሁሉ ገንዘብ ምን ያደርግልኛል?’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ‘በቀጥታ ሂድና ለቤተሰቦችህ ስጥ’ ብዬው ይህንኑ አደረገ፡፡ በመከላከያ ገባ-ወጣ በሚል ሒደት እድሎችን እንዲጠቀም አስቻልኩት፡፡ እኔ መከላከያ ን ስለቅ እሱ ወደ ጊዮርጊስ አመራ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለበት ደረጃ ከፍ ያለ ሆኗል፡፡ ተተኪ ማለት ታዳጊና ወጣቱ እኮ ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ ላይ በእጅጉ ማመን ይኖርብናል፡፡


የተናጠል የተጫዋቾች ብቃት ማሻሻያ ልምምዶችን በማሰራት የሰሩት ስራስ ምን ያህል ስኬታማ ሆኗል?

የተናጠል ስልጠናን ለመስጠት በመጀመሪያ ተጫዋቾች <ጉድለታቸውን የምታሻሽልበትና ችግሮቻቸውን እንዲያውቁ የምታደርግበት> መንገድ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ማሳመን አለብህ፡፡ በኳስ ቁጥጥር፣ አካል ብቃት፣ ፍጥነትና ሌሎችም ጉዳዮች ከተጫዋቾቼ ጋር በግልጽ እወያያለው፡፡ የግል ልምምዶች ፕሮግራምን በማውጣት ተጫዋቾቼ ከእኔ ጋር እንዲሰሩ አደርጋለው፡፡ እንደ አሰልጣኝ ተጫዋቾች የተሻለ እንዲሆኑ መትጋት ይኖርብሀል፡፡ ሁሌም ላይሳካ ቢችል እንኳ ለውጡን ለማየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አጭርና ረጅም እቅድ በመጠቀም ተጫዋቾችን የማሻሻል ሒደቱን መቀጠል ይኖርብሀል፡፡በአብዛኛው በጂም እንዲሰሩ፣ በተወሰነ የሰዓት ገደብም ፉትሳልን በመጫወት ቴክኒካዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መሻሻል እንዲያመጡ፣ ለኢንዱራንስ ደግሞ ዋና እንዲዋኙ፣ ለመተጣጠፍ የቅርጫት ኳስን እንዲጫወቱ አዛቸዋለሁ፡፡ ተጫዋቾቼም የምነግራቸውን ያደርጋሉ፡፡ በጊዮርጊስ እያለው በአንድ ወቅት በመሀል ተከላካይና በአማካይ ቦታ  በተጫዋቾች እጥረት ተቸገርኩ፡፡ ከኪራይ ቤት አንተነህ አላምረውን ፣ ከደሴ ደግሞ ብርሐኑ ፈይሳ (ፈየራን) አመጣኋቸው ፡፡ አንተነህ በኪራይ ቤት የተከላካይ ተጫዋች ነበር፡፡ በጊዮርጊስ የሆልዲንግ ሚና እንዲወጣ አሳመንኩት፡፡ የአሰልጣኝነት ሙያን እጅግ በጣም ነው የምወደው፡፡ የምለፋው የተለየ ጥቅም ለማግኘት አይደለም፡፡ ይህን ጠይቄም አላውቅም፡፡

በክረምቱ ዝግጅት ወቅት አንተነህና ብርሐኑን በአካል ብቃቱ ረገድ በደንብ አሰራኋቸው፡፡ ውድድሩ ሲጀመር አንተነህ የማይታለፍ ሆልደር ሆነ፤ በሱዳንም የተጫወተው በዚሁ ሚና ነበር፡፡ ብርሐኑም አስገራሚ ተከላካይ ወጣው፡፡ ጥሩ ቀሚና አቀባይ ሆነ፡፡ ይልማ ተስፋዬ (ካቻማሊ) ላይም እንዲሁ የቦታና የሚና ሽግሽግ አድርጌያለው፡፡ በአየር መንገድ ይልማ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ነበር፡፡ የሸርተቴ ታክሉን፣ ጥሩ የግንባር ኳስ ተጠቃሚ መሆኑንና ፍጥነቱን በማስተዋል ወደ ኋላ መለስኩትና ገራሁት፡፡ ከፍተኛ ትችቶች ቀረቡብኝ፡፡ ከብርሐኑ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ጠንካራ የተከላካይ ጥምረት ሰሩልኝ፡፡ በጊዮርጊስም በብሔራዊ ቡድንም የተሳካላቸው ተከላካዮች ሆኑ፡፡


በኢትየጵያ አሰልጣኞች ቢያሻሽሉት ወይም ቢያደርጓቸው በእግርኳሱ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለው የሚያነሷቸው የመፍትሔ ሐሳቦች…

በአሰልጣኞቻችን ላይ በቶሎ ራሳቸውን ትልቅ አድርገው የማየት ሁኔታን አስተውላለሁ፡፡ ትልቁ ችግራችን ይህ ይመስለኛል፡፡ እንደማናውቅና ወደ ኋላ የቀረን መሆናችንን ማመን ይኖርብናል፡፡ በሰራነው ትንሽ ነገር የመኮፈስ ዝንባሌ እናሳያለን፡፡ መመጻደቅና መኮፈስ መምጣት ያለበት ከውጤት በኋላ ነው- እሱም አስፈላጊ ከሆነ፡፡ ጠንክረህ ሰርተህ ቡድን ስትለውጥና ለፍተህ ዉጤታማ ስትሆን ነው መኩራራት ያለብህ፡፡ ላፕቶፕ መሸከሙ ሳይሆን ቁምነገሩ በላፕቶፕ ውስጥ ያለውን መረጃ ወደ መሬት በማውረድ ተግባራዊ አድርጎ ውጤት ማሳየቱ ነው፡፡ የምንመዘነው በስራችን እንጂ በዲስኩራችን እንዳልሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ በስራህ መደሰት ያለብህም ቡድንን ስትለውጥና ተጫዋቾችን የተሻለ ደረጃ ስታደርስ ነው፡፡ እንደ አሰልጣኝ ራሳችንን ዘላቂ የሆነ የውጤት ሒደት ውስጥ ማግኘት አለብን፡፡ በተደጋጋሚም ስኬታማ መሆንን መልመድ አለብን፡፡ ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ውጤታማነት ዋጋ የለውም፡፡ ጠንካራነትህ የሚለካው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ‘አለምአቀፋዊው የስልጠና ደረጃ የት ደርሷል?’ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በአፍሪካና በሌላው አለም ከእኛ በኋላ እግርኳስን የጀመሩ አገሮች ጥለውን ሄደዋል፡፡ ‘የተበለጥንበት ምክንያት ምንድን ነው?’ ተብሎ ሊጠና ይገባል፡፡ ስልጠናችን ላይ ችግር ካለም በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ በአጠቃላይም አሰልጣኞች ‘ምን ሰራው? ፤ምንስ ቀየርኩ?’ምን የተለየ ነገር አመጣው?’ ብለን ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ዝምብሎ ካለሚታይ ስራ ኮርሶችን መውሰድና ወረቀት መሰብሰብ ትርጉመ ቢስ ነው፡፡ ወረቀት ስራ አይሆንም፡፡ ብር ከፍለህ የስፔኑን ባርሴሎና በመጎብኘትህና የጥቂት ቀናት ኮርስ በመውሰድህ ብቻ ራስህን በትልቅ ደረጃ መመልከት ከጀመርክ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ የብሔራዊ ቡድናችን ውጤት የክለቦቻችን ደረጃ ማሳያ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በእግርኳሱ ዘርፍ የሚወጣው ገንዘብ ጥሩ ሆኖ ወደ ኋላ የሚጎትት እግርኳስ ማየት አሰሪውም ሰራተኛውም ላይ ችግር እንዳለ ይጠቁማል፡፡ ተጫዋቾችም ቢሆኑ ህግና ደንብ አክባሪ ሆነው ለተሰለፉበት ቡድን ያላቸውን በሙሉ በመስጠት ራሳቸውንና ክለቦቻቸውን ውጤታማ አድርገው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ስኬት ማስመዝገብ መቻል አለባቸው፡፡ አሰልጣኞችም ስርዓት ባለው መንገድ በስነምግባር የታነፀ ተጫዋቾችን መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ የአሰልጣኞች ስራ በጉልህ የሚታይ መሆን አለበት፡፡ በ300 ብር ደመወዝ እየሰራን የምንጨነቀው ስለ ውጤት፣ የምናሰለጥነውን ቡድን ደረጃ ከፍ ስለማድረግ እና እግርኳስን ስለማሳደግ ነበር፡፡ ለተጫዋችቻችን መሻሻልም እጅጉን እንታገላለን፡፡ የአሰልጣኙ ከፍተኛ ክፍያ ተጫዋቾች ተለውጠው ትልቅ ቦታ ደርሰው መመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ተጫዋቾች “አስራት እንዲህ አድጎልኝ….” ብለው ሲመሰክሩ የሚሰማኝን ደስታ ልነግርህ አልችልም!!! ሰው የማብቃትንና የማፍራትን ያህል ትልቅ ነገር የለም፡፡ በገንዘብ የሚመጣ ስም መጥፎ ነው፡፡ በሄድክበት ቦታ ሁሉ ራስህንና ቤተሰብህን ማሰደብ ነው ትርፉ፡፡ ተዓማኒነትም ተሰሚነትም ያሳጣሀል፡፡ በእንዲህ አይነት መንገድ ከሚመጣ ገንዘብ በልመና የሚገኝ ይሻላል፡፡

ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈውን ብሔራዊ ቡድን የመያዝ እድል ነበረኝ። ቡድኑን ብይዘው ስኬታማ አድርጌው ተሸላሚ፣ በየቦታው የምጠራና የሚጨበጨብልኝ ሰው እሆን ነበር፡፡


የእግርኳስ አስተዳደርንና የአመራሮቹ እግርኳሳዊ እውቀት አናሳነት በመስኩ እያመጣ ያለውን ችግር እንዴት ያዩታል?

እግርኳስን ለማሳደግ ትልቅ ሐላፊነት ከሚወስዱ አካላት መካከል የአስተዳደር ስራ አንደኛው ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች የስፖርት፣ የህግ፣ የአመራርና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያላቸው እውቀት ለቦታቸው የሚበቃ መሆን አለበት፡፡ በአስተዳደር ሐላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የሰፖርት ቋንቋን የሚገነዘቡና የሚናገሩ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የክለብ አመራሮች በአሰልጣኞች ላይ እንደፈለጉ የመሆን እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ ባይገባቸው እንኳ ስልጠናውን በደምብ በማየት አስተዳደራዊ ክትትል ማድረግ አለባቸው፡፡ የሚጠይቁ፣ የሚያዩ፣ የሚመረምሩና ባላቸው እውቀት ተመስርተው ቀናና ጥሩ አስተያየትን የሚቸሩ ቢሆኑ መልካም ይሆናል፡፡ ለአሰልጣኞች ስኬትን በፍጥነት መቀዳጀት ከባድ ሐላፊነት እንደሆነ የሚገነዘቡ እና ውጤት የሒደትና የረጅም ጊዜ ስራ መሆኑን የሚረዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አመራሮች ስራቸውን መውደድና ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የፌዴሬሽኑን ህግና ደንብ የማያገላብጡ፣ ሜዳ የማይገቡ፣ ምንም ባላዩት ነገር ላይ አስተያየት የሚሰጡ፣ ከሬዲዮ በሰሙት መረጃ ብቻ ትችት የሚያቀርቡ የክለብ አስተዳደሮች ስትመለከት ትገረማለህ፡፡

በአንድ ወቅት ያጋጠመኝ ደግሞ አስቂኝም አሳዛኝም ነው፡፡ ‘የተስፋ ቡድን እናቋቁም፡፡’ ብዬ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ከአመራር አባላት አንዱ ‘ሰባት ተጫዋቾች አይበቁህም?’ በማለት ጠየቀኝ፡፡ ታዲያ ከዚህ አይነቱ በአንድ ቡድን ውስጥ እንኳ ስንት ተጫዋቾች እንደሚያስፈልጉ ከማያውቅ የክለብ አስተዳደር ምን እናተርፋለን? እንደነዚህ አይነቶቹ አመራሮች ከተለያዩ የስራ መስኮች ተመርጠው ይመጡና ያለምንም እግርኳሳዊ እውቀት ዋናው የአመራር ቦታ ላይ ይመደባሉ፡፡ በምን አይነት ቋንቋስ ነው ከእነርሱ ጋር የምትግባባው? ትልቁ የእግርኳሳችን ድክመት ማሳያ ነው፡፡ እንደ መፍትሄ የስፖርት አስተዳደር ኮርሶችን በመስጠትና በሴሚናሮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል መሞከር ይቻላል፡፡ አመራሮች ራሳቸውም ለተሾሙበት ቦታ ብቁ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት የሚተጉ ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ሐላፊነቱን ሲረከቡም ስራውን ወደውትና አምነውበት ሊገቡ ይገባል፡፡ የእግርኳስ ቤተሰቡም ለአበል፣ ለሽርሽርና ለውጪ አገር ጉብኝቶች በሀላፊነት ቦታ ላይ የሚቀመጡ አስተዳደሮች እግርኳሳችን ውስጥ እንዳይኖሩ የበኩሉን ለመወጣት መጣር አለበት፡፡ ሙያውን ለተገቢው ሙያተኛ፣ ለሚያውቁና በፍቅር ለሚሰራ እንስጥ፡፡ የእግርኳሱ ተርሚኖሎጂ (ተገቢው የሙያው ቋንቋ ትርጉም) የሚገባቸውን ሰዎች እናምጣ፡፡ በተለመደው አሰራር እውቀቱ የሌላቸው ሰዎች የምትናገራቸውና በእነሱ ትዕዛዝ መሠረት የማትጓዝ ከሆነ ውጤት ባጣህ ቅጽበት ሊያጠቁህ ነው የሚሞክሩት፡፡ ከአሰልጣኙ ውጪ ተጫዋቾችን በመሰብሰብ አሰልጣኙን የሚሰልል ኮሚቴ ለእግርኳሱ የሚፈይደው ምንድን ነው? በተቀያሪ ተጫዋቾች ሊያስገመግሙህ ይሞክራሉ፡፡ የተጫዋቾች አስተያየትን በመቀበል የምትሰጠው ብያኔስ ምንያህል ፍትሀዊ ነው? በዚህ መንገድ እየሰሩ ያሉት አመራሮች ለእግርኳሱ ትልቅ ችግር እየሆኑ ይገኛሉ፡፡


ለአሰልጣኞች ስራ ፈታኝ ከሆኑት መካከል የበላይ አካለት ጣልቃ-ገብነት ጉዳይን እንዴት ይመለከቱታል?

ስራችንን በጣም ያከብድብናል፡፡ ደግነቱ እኔን እንደዚህ አይነት ችግር ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ያልመረጥኩትና ያልፈለኩት ተጫዋች  አይገባም፡፡ ሲያመጡብኝም አልቀበልም፡፡ የምመርጠው ተጫዋቾች ቡድኔን ውጤታማ የሚያደርግ፣ ካሉት ነባር ተጫዋቾች ጋር ተግባብቶና ተዋህዶ የሚሰራ፣ ለረጅም ጊዜ ቡድኑን የሚያገለግል መሆኑን አምኜበትና እድሜውን፣ ጤናውንና የብቃት ደረጃውን ገምግሜ ነው ወደ ቡድኔ የምቀላቅለው፡፡ በአብዛኛው ከአስተዳዳሪዎች ጋር የሚያቃቅረኝም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን ”ሀላፊው እኔ ነኝ፤ ስራውን ለእኔ ተዉት፡፡” የምል ሰው ነኝ፡፡ “አሰልጣኙ እኔ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ የአስተዳደር ሰዎች ናችሁ፤ ጣልቃ መግባት የለባችሁም፡፡” በማለት እስከ መጨረሻው እታገላለሁ፡፡ ከመድን የወጣሁበት ዋነኛ ምክንያትም “እኔ ያመጣኋቸውን ተጫዋቾች ተቀበሉ፡፡” በሚል ክርክር በተደረሰ አለመስማማት ነው፡፡

እንደስልጠናው ሁሉ በእግርኳሱ አልፈው ለአስተዳደሩ ስራም የሚሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢረዱና ድጋፍ ቢደረግላቸው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አስባለሁ፡፡


ለግማሽ ምዕተ አመት በተጠጋ የአሰልጣኝነት ህይወትዎ በመቆጨት ደረጃ የሚጠቅሷቸው ከንካኝ አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?

ከ31 አመት በኋላ የተሳተፍንበት የአፍሪካ ዋንጫን ውድድር ሳስብ የምትቆጨኝ ነገር አለች፡፡ ምክንያቱም የሚከተለው ታሪክ ነው፡፡ ለውድድሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ፌዴሬሽኑ አሰልጣኞች ለመቅጠር ሲፈልግ በመጀመሪያ ያነጋገረው እኔን ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሲሳይ፣ አቶ አበራ እና አቶ አፈወርቅ ሆነው ስታዲየም በምትገኘው ታችኛዋ አዳራሽ አወያዩኝ፡፡ “በአገሪቱ ካሉ አንጋፋ (ሲኒየር) አሰልጥኞች ዋናው አንተ በመሆንህ እድሉን ቅድሚያ አንተ ውሰድ፡፡” አሉኝ፡፡ ፈቃደኛ ነኝ፤ ጥሪያችሁንም አክብሬ መጥቻለው፤ ሆኖም ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስሆን የሚከፈለኝ 1,350 ብር ነው፡፡ ያን ሁሉ ብሄራዊ ውጤት ያመጣሁት በዚህ ደመወዝ ነው፡፡ ስለዚህ ባለፈው የአላሙዲ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ የሴካፋ ውድድር አሸንፌ ስመጣ በማግስቱ የደመወዝ ጭማሪ አድርጉልኝ ብዬ በደብዳቤ አሳውቄያለው፤ አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጣችሁኝም ስራውን አልፈልግም፤ ብዬ ትቼ ወጥቻለሁ፡፡ ይህን ታውቃላችሁ፤ ትረዱትማላችሁ፡፡ የBBC ጋዜጠኞች ጠይቀውኝም ይህን መልስ ነው የሰጠኋቸው፡፡ ለውጪ አሰልጣኞች መኪና አዘጋጅታችሁ፣ ከ300,000-350,000 ብር ትከፍላላችሁ፡፡ ግድየለም የእኔ ይነስና በወር 100,000 ብር ክፈሉኝ፤ የሁለት አመት ኮንትራት ይቅረብልኝ፤ በዋና አሰልጣኝነት ልስራ አልኳቸው፡፡  “ጥሩ እንግዲህ እኛ የመጣነው ስራ አስኪያጅ ኮሚቴው ‘አናግሩት’ ብሎ ልኮን ነው፤ ያንተን ሐሳብ ለኮሚቴው እናቀርባለን፡፡” የሚል መልስ ሰጡኝ፡፡ ከዚያ በኋላም ሰውነት ቢሻውና ወርቁ ደርገባ ተጠሩና የስራ ልምዳቸውን አቀረቡ፤ በነጻ እንደሚያገለግሉም ያሳወቁ ይመስለኛል፡፡ ኋላ ቤቴ ቁጭ ብዬ በቴሌቪዥን ” ከቀረቡት አሰልጣኞች ውስጥ አወዳድረን አቶ ሰውነት ቢሻውን መርጠን አሳልፈናል፡፡” የሚል መግለጫ አየሁ፡፡ እኔ በመጀመሪያ ስጠራኮ ምርጫ ተብዬ አልነበረም፤ ሲቪዬንም ይዤ አልቀረብኩም፡፡  ታዲያ ይህንን ነው ምርጫ ያሉት? ከዚያም ለጸሀፊው አቶ አሸናፊ ደውዬ ‘በምን መስፈርት ነው አወዳድረን መረጥን የምትሉት?’ ብዬ ጠየቅሁ፡፡ “ኧረ እኔ የማውቀው ነገር የለም፡፡” አለኝ፡፡ የአቶ አፈወርቅ ስልክ ተዘግቷል፤ ፕሮፌሰር ሲሳይም ምንም እንደማያውቅ ገለጸለኝ፤ አቶ አበራ ደግሞ መረጃው እንደሌለው አሳወቀኝ፡፡ ‘እንግዲህ እናንተ ካላወቃችሁ ውሳኔውን ያስተላለፈው ሳጥናኤል ይሆናል፡፡’ ብዬ ስልኩን ዘጋሁት፡፡ አቶ ሰውነትም በፈረንጁ አሰልጣኝ ስር በምክትልነት፣ በመቀጠልም በዋና አሰልጣኝነት ሰርቶ ትልቅ ውጤት አመጣ፡፡ እኔ በጊዜው ‘በነፃ አሊያም በትንሽ ደመወዝ እሰራለው፤ እናንተ በፈለጋችሁትና ባላችሁት መንገድም አገለግላለሁ፡፡’ብዬ ብናገር ኖሮ እርግጠኛ ነኝ እኔኑ ይመርጡኝ ነበር፡፡ ለረጅም ዘመን የሰራሁት በዋና አሰልጣኝነት ነው፤ ስለሆነም ለስሜና ለክብሬ ስል ራሴን ዝቅ ማድረግ አልፈለኩም፤ ይህን ውሳኔዬንም እንደ ሞኝነት አልቆጥረውም፡፡ ራስን የማስከበር ምልከታ ነው ብዬ አምናለው፡፡ አልፎ አልፎ ግን የመቆጨት ስሜት እንደምትፈጥርብኝ አውቃለሁ፡፡ እኔም ቡድኑን ብይዘው ስኬታማ አድርጌው <ተሸላሚ፣ በየቦታው የምጠራና የሚጨበጨብልኝ ሰው> እሆን ነበር፡፡

በአሰልጣኝነት ጊዜዬ ብዙ መከራ በማሳለፍ ከዛ የበለጠ ውጤት አምጥቻለው፡፡ በአፍሪካ የኢቦላ በሽታ በተስፋፋበት ወቅት በ5 ቀናት ዝግጅት “ብሄራዊ ቡድኑን ይዘህ ተጓዝ፡፡” ተብዬ ሄጄ 3ኛ ደረጃ በማግኘት የነሀስ ሜዳልያ አምጥቼያለው፡፡ በዚህ የሴካፋ ውድድር ወቅት አዘጋጆቹ አንድ ሆቴል ውስጥ አስቀመጡን፤ ኮሚቴዎቹ እዳ ስለነበረባቸው የሆቴሉ ሒሳብ ክፍል በየቀኑ ክፍያ ይቀበላቸዋል፡፡በአንደኛው ቀን እኔ ልጆቼን የማሟሟቅ ልምምድ አሰርቼ ስመለስ የሆቴሉ ሰዎች እቃዎቻችንን ከየክፍሎቻችን አውጥተው ደጅ አስቀምጠው ጠበቁን፤ ለካ ኮሚቴዎቹ በተከታታይ የሁለት ቀን ሒሳብ ሳይከፍሉ ቆይተዋል፡፡ ተደውሎ የአዘጋጅ ኮሚቴው ጸሀፊ መጣና ሌላ ደረጃውን ያልጠበቀ ሆቴል ተፈልጎ ተገኘልን፤ ሆቴሉ ከታች የምሽት መጨፈሪያና መዝናኛ ባር ሲሆን ከላይ ደግሞ መኝታቤት ሆኖ በአጠቃላይ ለበሽታ የሚያጋልጥ ከባቢ ነበር፡፡ ተጫዋቾቼ ዳቦና ሚሪንዳ በልተው ውለው፤ የደረጃ ጨዋታ አድርገውና የነሀስ ሜዳሊያ ይዘን ስንመጣ የተቀበለን አንድ ሰው አቶ ይስሀቅ ነበር፡፡

ሌላኛው አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የወደቅንበት አጋጣሚ የተፈጠረው ደግሞ በላይቤሪያ ነው፡፡ በወቅቱ ሙሉ በሙሉ ጦርነት ውስጥ ነበር የገባነው፡፡ ከዚህ ስንሄድ ፌዴሬሽኑ ብቻ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት አያውቅም፡፡ ጋና ደርሰን ከአክራ አውሮፕላኑ ወደ ጊኒ በረራ ሲጀምር ይመስለኛል መሄዳችንም ይፋ የሆነው፤ ጊኒ ስንደርስ ከባድ ጦርነት ጠበቀን፡፡ በጂፕና በወታደሮች ታጅበን ወደ ተዘጋጀልን ሆቴል ተወሰድን፡፡ ስንደርስ የሆቴሉ በሮች በሙሉ ታሽገው በሰንሰለት ታስረዋል፡፡ የሆቴሉ ሊባኖሳዊ ባለቤት ካለበት ቦታ ተፈልጎ መጣና በሮቹን ከፈታቸው፡፡ ግድግዳዎቹ በጥይትየወንፊት ያህል ተበሳስተዋል፡፡ ሶስት የምግብ ሰራተኞች ምግብ ሰርተውልን በልተን አደርን፡፡ የአካባቢው ነዋሪ በሙሉ በስደት ላይ ነበር፡፡ ዋናው የመጫወቻ ስታዲየም የስደተኞች ማረፊያ ሆኖ በሰዎች ተሞላ፡፡ ተጫዋቾቼም “እንዴት ነው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምንጫወተው?” ብለው በጥያቄ ወጠሩኝ፡፡ እንዲያውም “ከስደተኞቹ ጋር መቀላቀል ይኖርብናል፡፡” ብለው ሞገቱኝ፡፡ ‘አይሆንም፤ ከሞትንም የምንሞተው እዚሁ ነው፤ በማናውቀው አገር ወዴት ነው ስደት የምንወጣው?’ ብዬ በሮቹን ዘጋግቼ ቁልፎቹን ያዝኩ፡፡ ከጊኒ ቢሳው የተመደበው ኮሚሽነር በማግስቱ መጥቶ አየን፡፡ በእንግሊዘኛ ‘ሜዳው በስደተኞች ስለተሞላ ጨዋታውን አትጫወቱም፤ ነገ ወደ አገራችሁ ትሄዳላችሁ፡፡’ ሲል የሚጠብቁን ወታደሮችና አዛዦቻቸው ጥለውን ሄዱ፡፡ ከ 2 ሰዓታት በኋላ ደግሞ መጥቶ ‘ትጫወታላችሁ’ ብሎ ነገረን፡፡ በዚህኛው አዲስ ውሳኔ ያለጠባቂ የባዶ ቤት ሰንሰለቱን አጠባብቀን ቁጭ አልን፡፡ በዚህ ጊዜ ቤቱ ወስጥ ሆነን ስናወራ በሆቴሉ ዳር የሚያልፍ ስደተኛ አማርኛችንን ሰምቶ ከውጪ ወደ ግድግዳው ተጠግቶ ”ኢትዮጵያዊ ናችሁ?’ ብሎ ጠየቀን፡፡ ‘ወደ ስደት እየሄድኩ ስለሆነ ኑ አብራችሁኝ እንሂድ፡፡” አለን፡፡ ወደ ሆቴሉ ውስጥ አስገባነውና ‘እኛ ኳስ ለመጫወት ነው የመጣነው ብለን ስልክ ካለው እንድንጠቀምበት ጠየቅነው፡፡ ወዲያው ሰጠንና ወደ ኢትዮጵያ ዶክተር አሸብር ዘንድ ደወልን፡፡ ሆኖም ስልኩ ለረጅም ጊዜ ቢጠራም ቁጥሩ ለዶክተር አሸብር አዲስ አይነት ስለሆነበት ይመስለኛል አይነሳም፡፡ ከዚያ ወደ ቤቴ ደወልንና ባለቤቴን አገኘናት፡፡ ‘ያለንበትን ሁኔታ በመረዳት ከማለቃችን በፊት አንድ ነገር ይፍጠሩ’ ብዬ ነገርኳት፡፡ እሷም ወዲያውኑ ደውላ መረጃውን አሳወቀቻቸውና በስንት መከራ ከዶክተሩ ጋር ተገናኘን፡፡ ያለውን ነገር በሙሉ ነገርናቸው፤ በማግስቱም ተደዋወልን፡፡ ‘መልሼ እደውላለው’ ብሎንም በኔትወርክ ችግር የስልክ ግንኙነቱም ሳይሳካ ቀረ፡፡ በድጋሚ ኮሚሽነሩ ከወታደሮቹ ጋር መጣና ጨዋታውን እንደምናደርግ አስረግጦ ነግሮን ጥበቃው ተጠናከረልን፡፡ ከዚያም በጂፕ ታጅበን ወደ ትንሽ የትምህርት ቤት ሜዳ አመራን፡፡ ሜዳውን ካሳየን በኋላ መጫወት እንዳለብንና አለበለዚያ ሐላፊነት እንደማይወስድ አስረዳን፡፡ ስለዚህም እኛ መጫወቱን መርጠን በኋላ ሪፖርት ለማድረግ ተስማማን፡፡ በጨዋታው የተጋጣሚያችን ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ከሜዳ እየወጡና እየገቡ እንደፈለጉ መጫወት ጀመሩ፡፡ ከኔ ልጆች አቤጋና አንተነህ ፈለቀ ለጎልነት የቀረቡ እድሎችን አመከኑ፡፡ ከመስመር ውጪ በረጅሙ የተላከን ኳስ በመጠቀም በጭንቅላት ጎል አገቡብን፡፡  ተጫዋቾቼ በጎሉ ውሳኔ ኢ-ፍትሀዊነት ጉዳይ (የተሻማው ኳስ ከመስመር ውጪ ነበር፡፡) ብዙ ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም፡፡ 1-0 ተሸነፍን፡፡ በወቅቱ የነጥብ ልዩነት ነበረን፡፡ ጊኒዎች 9 ነጥብ ነበራቸው፡፡ የእኛን ሁኔታ የሰሙት ጊኒዎች ለካፍ አመልክተው በላይቤሪያ አንጫወትም ብለው ደብዳቤ ላኩ፡፡ በገለልተኛ ሜዳ አክራ ላይ እንዲጫወቱ ተደረገና አሸንፈው ለአፍሪካ ዋንጫ አለፉ፡፡ ከላይቤሪያ ጋር በገለልተኛ ሜዳ ብንጫወት በጥሩ ሁኔታ አሸንፈናቸው የማለፍ እድላችንን የተሻለ እናደርግ ነበር፡፡ ለአገራችን ያሳየነው መስዋዕትነት የመክፈል ድፍረታችን ቢያስደስተኝም ጥሩ በሚባል ስብስብ ያመጣነው ውጤት እጅጉን የምቆጭበት አጋጣሚ ፈጥሮብኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *