​የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

በሳምንቱ መጨረሻ ከአንድ መርሀ ግብር በቀር ጨዋታዎች አይኖሩም

በርካታ ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሉት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በዚህ ሳምንት መደበኛውን 14ኛ ሳምንት) መርሀ ግብር በማዘግየት ተስተካካዮቹን እንደሚያካሂድ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በወቅታዊ አለመረጋጋቶች ምክንያት በሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታዎችን እንደማይደረጉ ታውቋል።

በዚህ ሳምንት (እሁድ የካቲት 11) የሚደረገው ብቸኛ ጨዋታ በአውስኮድ እና ባህርዳር ከተማ መካከል የሚደረገው የባህርዳር ደርቢ ነው። ይህ ጨዋታ ጥር 12 ሊካሄድ መርሀ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም የባህርዳር ስታድየም በቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ድግስ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩ የሚታወስ ነው።

የቅጣት መረጃዎች

– ስልጤ ወራቤ ከ ሀምበሪቾ ካደረጉት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ከደጋፊዎች በተወረወሩ ድንጋዮች ረዳት ዳኛው በቀለ ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። ዳኛው ወራቤ ሆስፒታል ህክምና ተደርጎላቸው ማገገም የቻሉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ስልጤ ወራቤን 150ሺህ ብር እና ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን ከ150 ኪሜ ርቀት እንዲያደርግ ውሳኔ ተላልፎበታል።

– የሱሉልታ ከተማ ከ ሽረ እንደስላሴ ባደረጉት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በተነሳ ረብሻ ጨዋታው ለደቂቃዎች መቋረጡ የሚታወስ ነው። በዚህም ሱልልታ ከተማ 80ሺህ ብር ቅጣት እና ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን ከ150 ኪሜ ርቀት እንዲያደርግ ውሳኔ ተላልፎበታል።

– የሽረ እንደስላሴ ህክምና ባለሞያ የሆኑት አቶ ሚካኤል ከነቀምት ቡድናቸው ከነቀምት ጋር ባደረጉት ጨዋታ የዕለቱ ዳኛን በመሳደባቸው 5 ጨዋታ ሲቀጡ  የኢኮስኮ ቡድን መሪ ሙልጌታ አሰፋ በተመሳሳይ ድርጊት የ5 ጨዋታ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

                     ተዋወቁት

ሙሉ ስም – ኢብሳ በፍቃዱ

የሚጫወትበት ቦታ – አጥቂ

ክለብ – ሀዲያ ሆሳዕና

የቀድሞ ክለቦች – መቱ ከተማ እና ነቀምት ከተማ

በመቱ ከተማ የተወለደው ኢብሳ በፍቃዱ የእግርኳስ ህይወቱን መቱ ከተማ ፕሮጀከት ውስጥ የጀመረ ሲሆን በአንደኛ ሊጉ ክለብ መቱ ከተማ 1 ዓመት ከተጫወተ በኃላ ወደ ነቀምት ከተማ አምርቶ ለ3 ዓመት ያህል ቆይታ አድርጓል። በክረምቱ ቁልፍ ተጫዋቾቹን የሸኘው ሀዲያ ሆሳዕና ቀጣዩ የኢብሳ ማረፍያ ነበር።

ኢብሳ የሆሳዕናውን ክለብ በተቀላቀለበት የመጀመርያው አመት ውጤታማ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን በቡድኑ ደስተኛ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። ” ሀድያ ሆሳዕና ከመጣው ጀምሮ በእግር ኳስ ህይወቴ ትልቅ ለውጥ እያመጣው ነው። ከዚህም በላይ ጠንካራ መሆን እፈልጋለሁ። ”

12ኛው ሳምንት ቡድኑ ድሬዳዋ ፖሊስን 3-0 ሲረታ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሐት-ትሪክ የሰራ ሲሆን 8 ጎሎችን በስሙ በማስመዝገብ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል። በግብ አስቆጣሪነቱ በመቀጠልም በኮከብነት ስለማጠናቀቅ ያልማል። ” እግር ኳስ ጠንካራ ሰራተኛነትን ይፈልጋል። ይህን (ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን) በዚህ አመት ለማሳካትም ጠንክሬ እስራለው። ” ብሏል።

ጌታቸው ዳዊት ወደ አክሱም

ባለፈው ሳምንት ዋና አሰልጣኙ ሲሳይ አብርሀምን ያሰናበተው አክሱም ከተማ በምክትል አሰልጣኝ ልዑል ዮሐንስ እየተመራ በቡራዩ ከተማ በሜዳው 2-1 መሸነፉ የሚታወስ ነው። ክለቡ ትላንት አመሻሽ ላይ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አስታውቋል። የቀድሞ የመቐለ ፣ ወልዋሎ እና ደደቢት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የከፍተኛ ሊግ ልምዳቸው ቡድናቸውን እንደያሻሽለው አክሱሞች ተስፋ አድርገዋል።

የጌታሁን ገብረጊዮርጊስ ስንብት 

ዘነድሮ ከአንደኛ ሊግ ያደገው ደሴ ከተማ በሊጉ ማድረግ ከሚገባው ጨዋታ ግማሹን ብቻ ቢያደርግም የቡድኑ አቋም ያላስደሰታቸው የክለቡ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ጌታሁን ገብረጊዮርገስ ላይ ተቃውመሸቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። አሰልጣኙም የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን ትላንት የደሴ ከተማ ስፖርት ክለብ የቦርድ አባላቶች ተስብስበው ያስገቡትን የመልቀቂያ ወረቀት በአዎንታ ተቀብለዋል፡፡ ምክትል አሰልጣኙ ቴዎድሮስ ቀነኒ ቡድኑን በጊዜያዊነት እንዲረከብ የተወሰነ ሲሆን በቀጣይም በቡድኑ የዲስፕሊን እና የቴክኒክ ስራዎች ላይ አቅጣጭ አስቀምጦ እንዳለፈ የደሴ ከተማ ስፖርት ቡድን የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *