ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቡድኑ አባላት ጋር ተወያይቷል

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ አመራር እና ተጨዋቾቹ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ ውይይት አደረጉ። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር አመት መግቢያ ላይ ካስፈረማቸው ተጨዋቾች አንፃር የተጠበቀው ያህል ውጤታማ መሆንም ሆነ የሚያረካ የጨዋታ እንቅስቃሴ አለማሳየቱን ተከትሎ በደጋፊው ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል። በትናንትናው እለትም ቅሬታው መልኩን ቀይሮ የቡድኑን አባላት እስከመደብደብ እና እስከመዝለፍ  ደርሷል። ይህን ተከትሎም ዛሬ የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ በተጨዋቾቹ ማረፊያ ካምፕ ከቡድኑ አባላት ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን አሉ በሚባሉ ችግሮች ዙሪያ ግልፅ የሆነ ውይይት አድርጓል። በዚህም መሰረት ሁለት ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የክለቡ የፌስቡክ ገፅ ከደቂቃዎች በፊት አስነብቧል። የመጀመሪያው ውስኔ የቡድኑ የልምምድ ቦታ ከአዲስ አበባ ውጪ በዝግ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለተጨዋቾች የማነቃቂያ ሽልማት በየጨዋታዎች ላይ እንደሚንኖር የተገለፀበት ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ከክለቡ ደጋፊዎች ጋር ሌሎች የውውይት መድረኮች እንደሚዘጋጅ ተገልፆ ውይይቱ በጥሩ መንፈስ ተጠናቋል።  

በሊጉ በ22 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ ካደራጋቸው 13 ጨዋታዎች መሀከል አምስቱን ብቻ ያሸነፈ ሲሆን በአንዱ ተሸንፎ በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *