​ሪፖርት | በዝናብ የታጀበው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር እጅግ ተጠባቂ በነበረውና የሊጉን መሪ ደደቢትን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ጋር የነበረውን የስድስት ነጥብ ልዩነት የማጥበብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ሲቀር ደደቢትም መሪነቱን የሚያሰፋበትት አጋጣሚ አምክኗል።

ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 1ለ1 ከተለያየው ቋሚ 11 ስብስብ ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ከጉዳት የተመለሰውን አስቻለው ታመነን በደጉ ደበበ ምትክ ሲያስገቡ በአማካይ ስፍራ ላይ አዳነ ግርማን አስወጥተው ምንተስኖት አዳነን እንዲሁም በአጥቂ ስፍራ ላይ አሜ መሀመድን አስወጥተው ኢብራሂማ ፎፋናን በማስገባት በሚታወቁበት የ4-3-3 አሰላለፍ ቀርበዋል፡፡ በአንፃሩ ደደቢቶች መከላከያን 4ለ0 ከረታው ቡድን ውስጥ አማካይ ስፍራ ላይ ፋሲካ አስፋውን በአቤል እንዳለን በመተትካ በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርፅ ወደ ጨዋታው ቀርበዋል፡፡
ሚስማር ተራ እየተባለ የሚጠራው የአዲስ አበባ ስታዲየም የተመልካቾች መቀመጫ ክፍል መያዝ ከሚችለው መጠን ወደ ግማሽ የሚጠጋው ክፍል ለደህንነት ሲባል ከተመልካቾች ነፃ እንዲሆን ተደርጓል። ከጨዋታው መጀመር አንስቶ በስታድየሙ የጣለው እጅግ ከፍተኛ ዝናብ የጨዋታው መንፈስ ላይ አሉታዊ የሆነ ተፅዕኖ ማሳረፉን በግልጽ ለማስተዋል ተችሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ፈጠን ባለ አጨዋወት ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች  የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ለማድረግ የፈጀባቸው ሶስት ደቂቃዎችን ብቻ ነበር። ኢብራሂም ፎፋና ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወደ ውጪ የወጣችበት ሙከራ ተጠቃሽ ነበረች፡፡ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ከሙሉአለም መስፍን ፊት በግራና ቀኝ የተሰለፉት አብዱልከሪም ኒኪማና ምንተስኖት አዳነ ከወትሮው በተለየ ኳስ በደደቢት ተጫዋቾች እግር ስር በምትሆንበት ቅፅበት ከሶስቱ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች በቅርብ ርቀት በመሆን የደደቢት ተጫዋቾችን  ክፍተት እና ጊዜ በማሳጣት ስህተቶችን እንዲሰሩ እና ኳሶችን በረዣዥሙ በፍጥነት እንዲመቱ በማስገደድ በኩል በአንጻራዊነት ጥሩ ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ አስራት መገርሳ በግሩም ሁኔታ አሳልፎለት ኤፍሬም አሻሞ ከሮበርት ኦዶንካራ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ በደደቢቶች በኩል እጅግ በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

ሁለቱ የደደቢት የመስመር አጥቂዎች ሽመክት ጉግሳና ኤፍሬም አሻሞ ወደ መሀል አጥብበው ለመጫወት በሞከረቧቸው የተወሰኑ የመጀመሪያው 45 ደቂቃ የጨዋታ ሂደቶች ውስጥ መሀል ሜዳ ላይ የሚኖራቸውን የቁጥር ብልጫ በመጠቀም በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይነት ወስደው መጫወት ቢችሉም የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን ግን ወደ ግብ ሙከራ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ጨዋታው እየጣለ በነበረው ከፍተኛ ዝናብ የተነሳ የመጫወቻ ሜዳው እጅግ በመጨቅየቱ የነሳ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኳስን ለማንሸራሸር ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት እጅግ ፈተኝ አድርጎባቸው ኳሱን ከተከላካይ መስመር በረዣዥሙ ወደ ፊት እንዲጥሉ ተገደው ነበር፡፡ በ15ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከደደቢት የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ የሞከራት እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሜ ተጨዋቹ ከግራ መስመር ሲያሻማ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ የሞከራት እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ ሌሎች በፈረሰኞቹ በኩል የተደረጉ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ በቅዱስ ጊዮርጊሶች የበላይነት በደደቢት የሜዳ ክፍል ላይ አጋድሎ የተደረገ ነበር። ከመጀመሪያው በተለየም ደደቢቶች ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ሲከላከል የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተት ለመጠቀም በማሰብ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ በ48ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እንዳለ በተከላካዮች አናት ላይ ያሳለፈለትን ኳስ አቤል ያለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጠቅሞ ሞክሮ በግቡ አናት የላካት ኳስ የቡድኑን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ማሳያ ነበረች፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ ከወትሮው በተለየ ሁለቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆኑት አስቻለው ታመነና ሰልሀዲን በርጌች ፈጣኑን የደደቢት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ለማቆም በከፍተኛ ሁኔታ ሀይልን ቀላቅለው ሲጫወቱ ለመመልከት ችለናል፡፡

በሌላ በኩል ከመስመር በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶችን ግብ ለማስቆጠር ያሰቡ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዳነ ግርማን ፣ ሲይዶ ኬይታን እንዲሁም በሀይሉ አሰፋን በማስገባት በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ያረጉት ጥረት በጣም ደካማ የሚባል ነበር፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው በሀይሉ አሰፋ በቀኝ መስመር በኩል ወደ ደደቢት የግብ ክልል እየነዳ ለመግባት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ከደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሊመንት አዞንቶ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሲወድቅ ጨዋታውን የመሩት አልቢትር ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሜ ንጉሴ በአስገራሚ ሁኔታ በቅድሚያ ወደ ፍፁም ቅጣት ቢጠቁሙም በሰከንዶች ልዩነት ውሳኔያቸውን በመሻር የማእዘን ምት ለቅዱስ ጊዮርጊስ መስጠታቸው በስታዲየሙ የታደሙትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን በእጅጉ ያስቆጣ አጋጣሚ ነበር፡፡ 

በርካታ ጉሽሚያዎችና ፍትጊያዎች በቀጠለው ጨዋታ በ74ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ የተከላካይ አማካይ አስራት መገርሳ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ተገዷል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጥተኛ አጨዋወት በርካታ ኳሶችን ወደ ደደቢት የግብ ክልል በተደጋጋሚ ቢያደርሱም የደደቢት የመከላከል አደረጃጀት የሚቀመስ አልሆነም፡፡በዚህ መሰረት ጨዋታው 0ለ0 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢት ነጥቡን ወደ 29 ከፍ አድርጎ አሁንም በሊጉ አናት ላይ ሲገኝ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግም በ23ነጥብ አዳማ ከተማን በግብ ክፍያ በመብለጥ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ፋሲል ተካልኝ – የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ

ወደ ሜዳ የገባነው ለማሸነፍ እንጂ አቻ ለመውጣት አልነበረም ፤ ሜዳ ላይ ተጫዋቾችን የሚችሉትን ያህል ሰጥተው ተጫውተዋል፡፡ በጨዋታው ይገባን የነበረውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳኛው በቅድሚያ ከሰጠ በኃላ ለምን ሀሳቡን እንደቀየረ አልገባኝም፡፡

ጌቱ ተሾመ – የደደቢት ምክትል አሰልጣኝ 

በአጠቃላይ ከሜዳው ጭቃማነት የተነሳ እንደከዚህ ቀደሞቹ ጥሩ መንቀሳቀስ ባንችልም ከሞላ ጎደል በውጤቱ አልተከፋንም ፤ በጨዋታው አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ በመወገዱ በተወሰነ መልኩ ክፍተቶች ተፈጠሩብን እንጂ ጨዋታውን ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡

በቅጣት ላይ የሚገኙት የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ