​ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮዽያ ቡና ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቦሌ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ሜዳ 04:00 ላይ ሊደረግ ፕሮግራም የወጣለት ቢሆንም የፀጥታ አካላት በሰአቱ ባለመገኘታቸው የጨዋታው ኮሚሽነር ጨዋታው እንደማይደረግ መወሰናቸውን ተከትሎ 40 ደቂቃ ከዘገየ በኋላ በሜዳው ላይ የነበሩትን የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎችን በማስወጣት ጨዋታው መካሄድ ችሏል።

በዋናዎቹ ቡድኖች መካከል የሚታየው የአልሸነፍ ባይነት ፣ የደርቢነት ስሜት በታዳጊዎቹ ላይ ተጋብቶ ጠንካራ የመሸናነፍ ፉክክር በተመለከትንበት በዚህ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ የመጠናናት እንቅስቃሴ እያደረጉ ለጎል የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ያለ ጎል እረፍት ሊወጡ ችለዋል ።
የተሻለ የጎል ሙከራ እና ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት ሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎል በማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰዱት ፈረሰኞቹ ነበሩ ከመአዘን ምት የተሻገርውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲተፋው ከኳሱ ቅርብ ርቀት የነበረው ተከላካዩ አማኑኤል ተፍኬ ባስቆጠራት ጎል መምራት ጀመሩ።  በዚህ በታዳጊ እድሚያቸው ኳስን የሚቆጣጠሩበት መንገድ ፣ ቦታ አይቶ ለቡድን አጋራቸው ኳስ የሚሰጡበት ሁኔታ በሁለቱም ቡድኖች የተመለከትነው እጅግ አስገራዊ እንቅስቃሴ ሲሆን ፈረሰኞቹ ሄኖክ ፍቅሬ ከርቀት ባስቆጠረው ጎል 2 – 0 መምራት ችለዋል።

ጨዋታው ቀጥሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል ፍ/ቅ/ምት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ኢትዮዽያ ቡናዎች ሁለት ጎል ተቆጥሮባቸው ቢመሩም ጥሩ መንቀሳቀስ በአጥቂው ተገኝ ዘውዱ  አማካኝነት ጎል አስቆጥረዋል።  በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮዽያ ቡናዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በታዳጊዎቹ ፈረሰኞች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።

በጨዋታው ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ፀጋዬ መላኩ ፣ ከኢትዮዽያ ቡና አምበሉ ፍራኦል ደምሴ በግላቸው በሚያደርጉት መልካም እንቅስቃሴ ለወደፊቱ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን መመልከት ችለናል።


የ6ኛ ሳምንት ውጤቶች

ምድብ ሀ

ዕሁድ የካቲት 18 ቀን 2010

መከላከያ 0-0 ሲዳማ ቡና

ማራቶን  1-1 አዳማ ከተማ

ኤሌክትሪክ 1-1 ሀዋሳ ከተማ

ምድብ ለ

እሁድ የካቲት 18 ቀን 2010

ወላይታ ዲቻ ከ መድን (ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል)
ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 ኢትዮጵያ ቡና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *