​የአሰልጣኞች ገጽ | የውበቱ አባተ እግርኳሳዊ ሐሳቦች [ ክፍል አንድ ]


የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት የሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን የዚህ ሳምንት ተረኛ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነው።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቅርብ አመታት ከታዩ ውጤታማ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው። በ1990ዎቹ አጋማሽ ከተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ስራ በመግባት በፍጥነት ውጤታማ መሆን ችሏል። በአዳማ ከተማ ፣ ደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አል አህሊ ሸንዲ የሰራው አሰልጣኝ ውበቱ አሁን በሀዋሳ ከተማ ይገኛል። በዛሬው የክፍል አንድ መሰናዷችን አሰልጣኙ በእግርኳስ የተለያዩ ሀሳቦች ዙርያ ያለውን አተያይ ከስራ ልምዱ በመነሳት ያጋራናል።


ሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም 


በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ከሁለት አመት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ | LINK


በ1990ዎቹ አጋማሽ ከተጫዋችነት መገለል በኋላ ወደ ስልጠና ሙያ ስትገባ ስለ እግርኳስና ባጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ አሰልጣኝነት ባህሪያቶች የነበረህ ግንዛቤ ምን ይመስል ነበር?

እግርኳስ መጫወትን ያቆምኩት ድንገት ነው፤ ከሽግግሩ (ከተጫዋችነት ወደ አሰልጣኝነት) በፊት ለተጨማሪ አመታት መጫወት የሚያስችለኝ አቅም ነበረኝ፡፡ በወቅቱ መጫወት ማቆምን የፈለኩበት ዋነኛ ምክንያትም ቀጣይ ሶስትና አራት አመታትን በተጫዋችነት በማሳለፍ አሰልጣኝነትን ለመጀመር የምችልበትን ጊዜ ላለማራዘምና በቶሎ ወደ ስልጠናው አለም የምገባበትን ሁኔታ ይፈጥርልኛል ብዬ በማሰብ ነው፡፡ እየተጫወትኩም ቢሆን ከኳስ ጋር ቅርበት እንዲኖረኝ ያገዘኝ አስተዳደጌና ውሎዬ እንዲሁም የተፈጠሩልኝ አጋጣሚዎች እግርኳስን በተጫዋችነት ደረጃ የመረዳት ጥሩ ሁኔታዎችን ፈጥሮልኛል፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ከአሰልጣኞች ጋር ሁሉ እስካለመስማማት የሚያስደርስ የራሴ የሆነ አመለካከት እንዲኖረኝ አድርጓል፡፡እየተጫወትኩ የመምራት፣ ሌሎች ያላዩትን ተረድቶ እንዲህ ቢሆን የማለት፣ ሀሳብን በነፃነት የመናገርና ግልፅ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጥያቄ የማቅረብ ዝንባሌዎች ነበሩኝ፡፡ እንግዲህ እነዚህን መሰል ባህሪያት አሰልጣኝ ለመሆን ከሚያስፈልጉ ግብአቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አሰልጣኝ ስትሆን ጠያቂ መሆን አለብህ፡፡

በእኛ አገር እግርኳስ ውስጥ በርካታ አመታትን እየተጫወትኩ ስላሳለፍኩ ክለቦቹ የሚመሩበትን መንገድ በጥሩ ሁኔታ ተረድቻለሁ፤ በበርካታ አሰልጣኞች ስር በመሰልጠኔ ሁሉም ጋር የነበረውን የስልጠና ሒደትም አልፌበታለሁ፡፡ የነበርኩበት አካባቢም በአዎንታዊነት የሚጠቀስ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል፡፡ ብዙውን ጊዜ ክለቦችና ብሄራዊ ቡድኖቻችን በአዳማ የዝግጅት ጊዜያቸውን ያሳልፉ ስለነበር በርካታ ነገሮችን የመመልከት እድሎችን ፈጥሮልኛል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎችና ቅርበቶች ሽግግሩ ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን እንድገነዘብ አስችለውኛል፡፡



ወደ አሰልጣኝነት ስትመጣ ቀድሞ በነበረህ የአረዳድ መጠን ምን አይነት ነገሮች ይገጥሙኛል ብለህ ጠበቅህ ነበር? ቀድሞ በነበረህ ግንዛቤና በስራው ላይ በገጠመህ እውነታ መካከል የነበሩት መፋለሶችንስ እንዴት ተቀበልካቸው?

እውነት ለመናገር እንዳሰብኩት ቀላል ሆኖ አልጠበቀኝም፤ ሲጀመርም አቅልዬ አልገባሁበትም፡፡ ስራ ውስጥ ስትገባ ደግሞ አያሌ ነገሮች ስለሚገጥሙህ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ያደርጉብሀል፡፡ በአገራችን በትልቅ ደረጃ አሰልጣኝ ለመሆን መስራት ከባድ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ጥሩ አሰልጣኝ ለመሆን የምትጓዝበት አንድ የተወሰነ መስመር አለመኖሩ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ቦታዎች ዝግ ይደረጋሉ፤ በሙያው አዳዲስ ፊቶች እንዲገኙ ያሉት ፈተናዎች ብዙ ናቸው፡፡ እንደ እኔ አይነት በብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ ትልቅ ስም ያላገኘ ተጫዋችና ድንገት የመጣ ሰው በፕሪምየር ሊጉ በጥቂት አመታት በዋና አሰልጣኝነት ተቀምጦ፣ ተፎካክሮ፣ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ እና ሰብሮ ገብቶ አሰልጣኝ መባል በራሱ ትልቅና ከባድ ነገር ነው፡፡ ያንን ለማለፍ ችያለው፤ ግን እንዲሁ በቀላሉ አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት እንዳውም አዳማ በምክትልነት ስሰራ ‘ለምን አልተወውም?’ ብዬም አስቤ ነበር፡፡ ስብሰባ ላይ 25 ከሚጠጉ ተጫዋቾች 17 የሚሆኑት እኔን ተቃወሙ፡፡ ‘የቡድኑ ችግር መንስኤ ምክትል አሰልጣኙ ነው፡፡’ የሚል ቅሬታ አቀረቡ፡፡ ከተጫዋቾቹ ያልጠበቅሁት አስደንጋጭ ሁኔታ  ነበር፡፡ የአብዛኞቹ አስተያየት እኔ ከነበረኝ አቋም ፍጹም ተቃራኒ ሆነ፡፡ እኔ የማስበውና መሬት ላይ ያለው ነገር አልገጣጠም ስላለኝ ትንሽ ጊዜ ልውሰድና ቀስ ብዬ ብመጣ ይሻላል ስል አሰብኩ፡፡  አጠገቤ ለነበረው እና ጉዳዩ ለሚመለከተው ሰው ‘ይህን ያህል ተጫዋቾች እኔ ላይ እንዲህ አይነት አመለካከት ካላቸው እኔ ወርጄ ሌላ ቦታ ነው መስራት የሚኖርብኝ ፤ ስለዚህ ይቅርብኝ፡፡’ ስለው ‘እንደዛ መሆን የለበትም፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች በህይወትህ የሚገጥሙ ናቸው፤ ልታልፋቸው ይገባል፡፡’ ብሎ መከረኝ፡፡ እነሱንም አስረዳቸው፡፡ ‘ውበቱን እናውቀዋለን፤ እኔ ደግሞ በግሌ የውስጥ እጄን ያህል አውቀዋለሁ፤ ቀጥተኛ ሰው ነው፤ በእርግጥ ያልተለመደ ነገር ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ልትረዱት ይገባል፡፡’ አላቸው፡፡ በፊት ተጫዋቾች የሚያውቁት የምክትል አሰልጣኝ ስራ ኮኖችን መደርደር፣ ቢብስ ማቀበል፣ እየበረገግክና እየተሽቆጠቆጥክ ትዕዛዛትን ማስፈፀም አይነት ስራ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አይደለም አሰልጣኝ ሆኜ ተጫዋች በነበርኩበት ሰዓት እንኳ በማላምንበት ጉዳይ ጥያቄ አነሳ ነበር፤ ስህተትንም ፊትለፊት ነው የምናገረው፤ አግባብ ያልሆኑ ነገሮች ላይም ‘ትክክል አይደለም፡፡’ ለማለት አልሰንፍም፡፡ እነዚህ ባህሪያት ለተጫዋቾቹ ምቾት አልሰጣቸውም፡፡ ከአብዛኛዎቹ ጋር አብሬአቸው ተጫውቻለው፤ በተጫዋችነት ጊዜያችን እያሾፉ የመጫወት እድል የሚሰጣቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ በልምምድ ወቅት እኛ ሜዳ እያካለልን ስንሮጥ ‘ ተው ባክህ በሮጠ አይደለም፡፡’ ሲሉ የኖሩ ናቸው፡፡ እኔ አሰልጣኝ ስሆን ደግሞ መሮጥ እንዳለብህ የማምንና ተግባራዊ እንድታደርግልኝም የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡ እነዚህ ነገሮች እንግዲህ አብረው የሚሄዱ ባለመሆናቸው ነበር ችግሮች የተፈጠሩት፡፡



ታዲያ ይሄን ችግር እንዴት ተወጣኸው? በአዳማ በዋና አሰልጣኝነት እነዚህኑ ከላይ የገለፅካቸው ተጫዋቾች ነው ያሰለጠንከው፡፡ በምክትልነት የተቸገርክበትን ጉዳይ በዋና አሰልጣኝነትህ በምን መልኩ ቀየርከው?

የሚገርመው ከምክትልነት ወደ ዋና ቡድን አሰልጣኝነት ያደኩበት ሽግግር የተከናወነው ከላይ የጠቀስኩት ሁኔታ በገጠመኝ ሰሞን ነው፡፡ በጣም ከባዱ ነገር ያለውም እዚህ ጋር ነበር፡፡ ግምገማው ከተካሄደ ሁለትና ሶስት ቀናት በኋላ ‘አዳማ ከ16 ቡድኖች 15ኛ ደረጃ ላይ ስለተገኘ ቡድኑን በአስቸኳይ እንዲያሻሽሉ!’ የሚል ደብዳቤ ለዋናው አሰልጣኝ ተሰጠ፡፡ ዋና አሰልጣኙ ‘እኔ ይህ ደብዳቤ አይገባኝም፡፡’ ብለው ከስራቸው በራሳቸው ፈቃድ ለቀቁ፡፡

ቡድኑ ልምምዱን መቀጠል ነበረበት፤ ምክትል አሰልጣኙ ደግሞ እኔ ነኝ፡፡ ስብሰባ ተደረገና ለተጫዋቾቹ ተነገራቸው፡፡ ‘ዋና አሰልጣኙ ለጊዜው ከቡድናችን ጋር ስለሌሉ እሳቸው እስኪመጡ ድረስ ከውበቱ ጋር ትሰራላችሁ፡፡’ተባሉ፡፡ ተጫዋቾቹ አሁንም አስተያየት ሰጡ፡፡ ግማሾቹ ‘ውበቱ ወጣት ነው፤ የምንወዳደርበት ፕሪምየር ሊግ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ስለዚህም በሱ ስር ከቀጠልን አደጋ ውስጥ እንገባለን፡፡’አሉ፡፡ሌሎች ደግሞ ‘እንደ ካሳዬ አራጌ እንዳይቸገር በቡድኑ አንጋፋ የተባሉ ተጫዋቾች ስለሚገኙ ከእነርሱ ጋር አብሮ ያሰልጥነን፡፡’ ብለው ጠየቁ፡፡ እነ ፀጋዘአብ አስገዶም፣ ጌታቸው ካሳ(ቡቡ) ፣ታምሩ ያደታና ሌሎችም ትልልቅ ተጫዋቾች በቡድኑ ነበሩ፡፡ ከታምሩ ጋር በኪራይ ቤቶች፣ ከፀጋዘአብ ጋር ደግሞ በጉምሩክ አብረን ስለተጫወትን ጥሩ ወዳጅነት መስርተናል፡፡ ስለዚህ የካበተ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች እንዲረዱኝ ተፈለገ፡፡ ሌሎች ደግሞ ስራንና ቀጥተኛ አካሄዱን በማስቀደም የእኔን መሾም የሚፈልጉም ነበሩ፡፡ በስብሰባው መጨረሻ እኔ እድናገር እድል ተሰጠኝና ‘ምን ይመስልሀል?’ የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ ‘ይሄ እንግዲህ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በአውሮፕላን እየተጓዝን ዋናው አብራሪ ቸግር ቢገጥመው በረራው የሚቀጥለው በረዳት አብራሪው ነው፡፡  ረዳቱ ደግሞ ሌላ ችግር ሲገጥመው ‘እባካችሁ የማብረር ልምድ ያለው ካለ ተብሎ ነው የሚጠየቀው፡፡ ረዳቱ እኔ ነኝ፤ በእኔ መብረር  አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አብሮ መውደቅ ነው፡፡ ግዴላችሁም በቀደመው ስብሰባ ላይ በሰጣችሁት አስተያየት ጫና አይፈጠርባችሁም፡፡ ያ የእናንተ የአተያይ ደረጃና እኔን የተረዳችሁበት መንገድ ነው፡፡’ እውነታውም በስራ ብቻ የምንገናኝ መሆናችን ነው፡፡ እናንተ ትኩረታችሁን ስራችሁ ላይ ብቻ አድርጉና የሚመጣውን ነገር አብረን እናያለን፡፡  ከፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ 16 ቡድኖች መካከል 2ቱ ይወርዳሉ፤ የሌላኛው ወራጅ ቡድን አሰልጣኝ እኔ አይደለሁም፤ ያለሁበት ቡድን ቢወርድም እኔ ስላሰለጠንኩት ላይሆን ይችላልና እንደዚህ አቅልላችሁ ተመልከቱት፤ አዕምሮአችሁን ነፃ አድርጉና ወደ ስራ እንግባ፤ ዋና አሰልጣኙ ሊመለሱ ስለሚችሉም ስራው ተቋርጦ ሊጠብቃቸው አይገባም፡፡’ አልኳቸው ፡፡ ጠንክረን ሰርተን 10ኛ ሆነን ጨረስን፡፡ ተጫዋቾች ይህን ሲያዩ ምልከታቸውን የመቀየር አዝማሚያን አሳዩ፡፡ በዚህ ሁኔታ አጋጣሚውን አሳለፍኩና ከ1998 አጋማሽ ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ ከቡድኑ ጋር ዘለቅሁ፡፡



አዳማ ከተማ 1998 ላይ 10ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ በ1999 ውድድሩ ተቋርጦ ነበር። በ2000 ደግሞ እጅግ ምርጡን ቡድን በአማካይ የጥራት ደረጃ በሚመደቡና ያሬድ ዝናቡን በመሳሰሉ ወጣት ተጫዋቾች አዋቅረህ ሰራህና በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለዋንጫ የሚፎካከር ክለብ አደረግከው፡፡ ስትረከበው ከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበረውን ቡድን በአጭር ጊዜ ከፍታ ላይ ያወጣኸው እንዴት ባለ መንገድ ነው?

ውጤቱ በሒደትና በጠንካራ የቡድን ግንባታ  የመጣ ነው፡፡ በእርግጥ የኔ ብቻ ጥረት ያመጣውም አይደለም፤ አብረውኝ የነበሩት አባላት ድካም ታክሎበታል፡፡ እንደተጠቀሰውም በቡድኑ ገናና ስም የነበራቸው ተጫዋቾች አልነበሩም፡፡ እንዲያውም አብዛኞቹ ከተለያዩ ቡድኖች የተቀነሱና ሌሎች ክለቦች ውስጥ ቦታ ያልተሰጣቸው እንደ ያሬድ ጌታቸው (ከመብራት ሐይል የመጣ)፣ አርማታ (አሁን አሰልጣኝ ሆኗል፡፡) ፣ ዝናቡ አላሮ እና የመሳሰሉት አንጋፋ የነበሩ ቢሆኑም በሌሎች ክለቦች እድል የተነፈጋቸው ነበሩ፡፡ እነ ናሆም (የአስራት ሐይሌ ልጅ)፣ ላቃቸው (የመንግስቱ ወርቁ ልጅ) እና ከከተማዋ የተገኙ ልጆች ነው ቡድኑን የሰሩት፡፡ ሁሉም የቡድኑ ሰው ለአንድ አላማ የተሰለፉበት ጊዜ ነበር፡፡ የአካባቢው ሰው ደግሞ በቡድናችን ላይ ከፍተኛ እምነት ነበረው፡፡ አመራሮችም ጥሩ ያበረታቱናል፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም አካላት ጠንካራ አንድነት ሰፍኖ ነበር፡፡



በአዳማ ፈጣን እድገት ዙሪያ ምላሽህ ባብዛኛው ከባቢያዊውን አዎንታዊ ሚና የሚዳስስ ነው፡፡ ያንተ የጎላ ድርሻስ? 

እኔ በውስጤ በስልጠናው አለም ልተገብራቸው የምፈልጋቸውን ብዙ ሀሳቦች ነበሩኝ፡፡ ጊዜ ሰጥተህ የምትሰራበት ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ነገሮችን የምንገነዘብበት መንገድ አንዱ ካንዱ የሚለያይበትን መስመር ይለያል፡፡ እግርኳስን የምረዳበት አንድ መንገድ አለ፡፡ ያንን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግና ለማሳደግ በብዙ መትጋት አለብን፡፡ ለመማርና ራስን ዝግጁ በማድረግ ረገድ ሁሌም እታትራለሁ፡፡ እግርኳስን በተመለከተም ሁልጊዜ ለማወቅ ነው ጥረት የማደርገው፡፡ ብዙ ጊዜዬን የምሰጠውም ለዚሁ አላማ ነው፡፡ የሀገር ወስጥም ይሁን የውጪውን በመመልከት ለመማር እሞክራለሁ፡፡ በማየት፣ በማንበብና በመወያየት መለወጥ እንደሚቻል አምናለው፡፡ ስለዚህም አሰልጣኝነት ስራ ውስጥ ገብተህ ስኬታማ ለመሆን አስፈላጊ የተባሉትን የግል ጥረቶች በሙሉ ማድረግ ይኖርብሀል፡፡ እኔም በዘላቂነት በዚህ ሒደት ውስጥ ራሴን አስጉዛለው፡፡ ጊዜው የደረሰበት ቴክኖሎጂ ለሁሉም እኩል የመዳረስ ሁኔታን ባያሳይም ራስን በተቻለ አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ እድሎችን ለመጠቀም እሞክራለው፡፡ ባለንበት ቦታ ሆነን የእግርኳስ አተያይና ግንዛቤያችንን ማሳደግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡

ለምሳሌ ፔፕ ጓርዲዮላን እንመልከት፡፡ በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ከአለማችን ትልልቅ አሰልጣኞች አንዱ ሆኗል፡፡ ከሱ ቀድመው የሚታወቁ በርካታ አሰልጣኞች ነበሩ፡፡ በኮርስ ደረጃ ካየን እነሱ የወሰዱትን ነው እሱም የወሰደው፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም UEFA PRO ከወሰደ ሌሎች ብዙ ይህን ሰርተፊኬት ያገኙ አሉ፡፡ስለዚህ ልዩነቱን የፈጠረው እግርኳስን የሚመለከቱበት መንገድ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ከጥረትና ሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ማለቴ ነው፡፡ በእርግጥ ሁሉም እኮ ይጥራሉ፡፡ ነገር ግን አተያይህ አንተን በቶሎ ወደምትፈልግበት አቋራጭ ይወስድሀል ብዬ አስባለሁ፡፡


በትምህርት ከሚገኘው እውቀት ባለፈ ተግባራዊ ልምድ የበለጠ ፋይዳ አይኖረውም? በሰጠኸው ምሳሌ እንኳ ብናነሳ ፔፕ በኮርስ ደረጃ ካገኘው እውቀት በላይ በተጫዋችነት ዘመኑ ያሰለጠኑት እጅግ ሐሳባውያን የሚባሉና እግርኳሱ ላይ የፍልስፍና አብዮት የፈጠሩ ብዙ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ስለ አመለካከቱ የሚያወያያቸው እንኳን ታዋቂ የእግርኳስ ህልዮታውያን ናቸው፡፡

እኔ ይህንን ግላዊ አተያይ አድርጌ ነው የምመለከተው፡፡ ጓርዲዮላን ያሰለጠኑት አሰልጣኞች ያሰለጠኗቸው ሌሎች በርካታ ተጫዋቾች አሉ፡፡ እርሱ የተጫወተባቸው ክለቦችና አገሮች ውስጥ የተጫወቱ ተጫዋቾችም እንዲሁ፡፡ አሰልጥነውም በትንንሽ ዲቪዚዮኖች እንኳ ስኬታማ መሆን አልቻሉም፡፡ ልምድንማ ሁሉም በሙያው ያገኘዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ በልምድ ውስጥ የምታካብተው አረዳድ እና የተለየ ግንዛቤ ነው፡፡ ለምሳሌ አንተ በምትረዳው መጠን ትጽፋለህ፤ እኔና እሱ ደግሞ ያንተን ጽሁፍ አንብበን ሌላ የምንገነዘበው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ፔፕም እንዲሁ እያስተማሩት ከነበሩት ሰዎች ያየው ሌላ ነገር አለ፤ በራሱ ሀሳብ ተግባራዊ የሚደረግ፡፡ ጽፈው ያስተማሩትን በራስ አረዳድ ጽፎ እንደመተግበር ማለት ነው፡፡ እንደተጠቀሰው ግን ልምድ ወይም ተመክሮ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የምትረዳበት ዘዴ ያለው ዋጋም ከፍተኛ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኮርሶች -የሐገር ውስጡም ሆነ እድል ቀንቶህ ውጪ ሀገር ሄደህ የምትማራቸው ጥሩ ናቸው፡፡ ሆኖም እንደ መነሻ ነው መጠቀም ያለብህ፡፡ ቁልፍ አድርገን እናስባቸው፡፡ ቁልፉን ይዘህ ስትቀመጥ ነው ችግሩ፡፡ የመንጃ ፈቃድ ሊኖርህ ይችላል፡፡ ካልነዳህበት ግን ዋጋ የለውም፡፡ የ20 ቀናት፣ የ3 ወርና የ6 ወር ኮርሶች ሊኖሩህ ይችላል፤ አንተ ግን አመቱን ሙሉ በማንበብ፣ ከሙያው ሰዎች ጋር በመወያየትና በሌሎችም ራስን የማሻሻል ጥረት ውስጥ ልትሆን ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት ማንኛውም ሰው የሚፈልግበት መድረስ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡



የምትመርጠው የጨዋታ ዘይቤ ግልፅ እና በየጨዋታዎቹ የማይቀያየር ነው። ይህን ይዞ በመጓዝ እና በውጤታማነት መቀጠል ዙርያ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?  

የምትፈልገውን ነገር በተግባር ለማሳየት በፍላጎትህ መሰረት ለመመልመል ያለው የቴክኒካዊ ተጫዋቾች እጥረት አንደኛው ነው፡፡ ባሰለጠንኩባቸው ክለቦች ሁሉ ይህ ችግር ገጥሞኛል፡፡ አንተ በምትፈልገው ደረጃ ባለክህሎት የሆነ ተጫዋችን ለማግኘት ትቸገራለህ፡፡ ያሉት ተጫዋቾች በኮንትራት ስር ያሉ አልያም ጥሩ ወደሚከፍላቸው ለመሄድ የተዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር ሜዳ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳን ጨምሮ በአገራችን የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሜዳዎች ኳስን በጥሩ ሁኔታ ለመጫወት የሚያስችሉ አይደሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና ተመልካቾች አልታደልንም፡፡ አሁን አሁንማ ተላምደነው ሜዳ ማለት ‘ያለን’ እየመሰለን መጥቷል፡፡ ‘ተጫዋቾች እንዴት አይቀባበሉም?’ ሁሉ ሲባል እየሰማን ነው፡፡ ጥሩ ለሚባል የኳስ ጨዋታ ቅብብሎች ወሳኝ ድርሻ አላቸው፤ የተሻሉ ቅብብሎች ደግሞ አመቺ ሜዳዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ምንም ያህል ባለ ክህሎት ሁን ኳሱ በተደጋጋሚ እየነጠረብህ ስኬታማ ቅብብሎችን ልትከውን አትችልም፡፡ ለምሳሌ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን ውሰድ፡፡ የተጫዋቾቹ የግል ብቃት በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች የሚታወቅ ነው፡፡ እዚህ ባደረጉት እንቅስቃሴ ግን ደክመው ታይተዋል፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም ሜዳው እንዳልተመቻቸው ግልጽ ነበር፡፡ ‘ኧረ እነዚህስ ከኛ ልጆችም አይሻሉም፡፡’ ያሉ ተመልካቾች ነበሩ፡፡ እውነት ከኛ ተጫዋቾች ሳይሻሉ ቀርተው ነው? ናይጄሪያ የመጣ ጊዜም የቡድኑ የመስመር ተከላካይ ታዬ ታይዎ በካታንጋ በኩል ሁለት ጊዜ የተላከለተን ኳስ መቆጣጠር ሲከብደው ተመልክቻለሁ፡፡ ታይዎ ኳስ የመቆጣጠር መሰረታዊ ችግር ኖሮበት ነው? አይደለም ፡፡ የሜዳው አስቸጋሪነት እንጂ፡፡ ሌላኛው ተጠቃሽ ችግር ደግሞ ክለቦች ራሳቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹማ ‘እኛ እንደዚህ አለመድንም፤ መሽከርከሩን ምን አመጣው?’ ብለው የሚጠይቁም አሉ፡፡ ሀሳብህን የሚረዳህ ሰው ታጣለህ፡፡ ሽንፈት ሲከሰት ደግሞ የሚታገስህና በፍላጎትህ እንድትጓዝ የሚፈቅድ አካል አታገኝም፡፡



የኳሱ ተመልካች ጋር ያለው በሒደት ወደ ስኬታማነት ለሚያደርሰው እንቅስቃሴ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ በፍጥነት ጎሎች ተቆጥረውና ውጤት ተገኝቶ ደስታ የሚገኝበትን መንገድ መፈለግ ላይ ትኩረት የማድረግ አዝማሚያ የሚያሳድረው ጫናስ?

ትልቅ ጫና አለው፡፡ ክለቦች ባልኩት ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ አመራሮችም ሆኑ ደጋፊዎች በአጨዋወት ዘይቤህ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳድሩብሀል፡፡ 1ኛው ደቂቃ ላይ ጎል እንድታገባ የሚፈልጉ ሁሉ አሉ እኮ፡፡ ያልጠቀስኩት ሌላኛው ችግር ተጋጣሚዎች ናቸው፡፡ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ያመዘነ ቡድንን ሲገጥሙ ይዘውት የሚመጡት አጨዋወት አካላዊ ፍትጊያ ይበዛዋል፡፡ መከላከል ላይ ማተኮሩ ችግር የለውም፡፡ ዳኛም ብዙ ከለላ ስለማያደርግላቸው ተጫዋቾቹ ይህን አካላዊ ንክኪ ለመጠንቀቅ አጨዋወታቸውን ይቀይራሉ፡፡ አይታችሁ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ 3 በቀይ የሚያስወጡ ጥፋቶችን የፈጸመ ተጫዋቾች ቢጫም ሳያይ ተጫዋቾቼ ብዙ ግጭቶች ተፈጽሞባቸዋል እያነከሱ ሲወጡ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ማቅረብ እችላለሁ፡፡



ከላይ የጠቀስካቸው ችግሮች ስኬታማነትህ ላይ ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ከውጤት ጋር ብቻ በተያያዘ መስፈርት በምትመዘንበት ስራ ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሀሳብና የአጨዋወት ለውጥ እንድታመጣ አልገፋፋህም?

በግልህ እኮ በቸግሮቹ ምክንያት አልፎ አልፎ የሚሰማህ ስሜት ይኖራል፡፡ በመጀመሪያ በተከተልከው አጨዋወት ውጤት ማምጣት ይኖርብሀል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ኳስን መሰረት አድርገህ ስትጫወትም ዝም ብሎ ለመሽከርከር አይደለም፡፡ ጉልበትን ከማባከን ትድናለህ፤ ከግምታዊ አጨዋወት ያስወጣሀል፤ በምታስበው መንገድ እንድትንቀሳቀስ ያስችልሀል፤ ተጋጣሚህ በበርካታ ደቂቃዎች ኳስን ፍለጋ እንዲዳከም ያደርግልሀል፡፡ ተጫዋቾችን ከኳስ ጋር ለ20 ደቂቃዎች ብታደርግና እንዲጫወቱ ብታዝ እንዲሁም ሌሎች ተጫዋቾችን ለ10 ደቂቃዎች እንዲሮጡ ብታደርግ ቀድመው የሚደክሙት ያለ ኳስ ያሉት ናቸው፡፡ ምክንያቱ በኳሱ መዝናናት እና ኳሱን በመፈለግ መካከል ባለው ልዩነት የሚፈጠር ድካም አዕምሯዊ መሆኑ ነው፡፡ የሁሉም ስልቶች መጨረሻው ግን ውጤት ማምጣት ነው፡፡ ቀዳሚው አላማም ጎል ማግባት ነው፡፡ ውጤት ስላላመጣህበት ብቻ ያመንከው ነገር ስህተት ነው ማለት እንዳልሆነ ልታውቅ ይገባል፡፡ የሚረዱህ ሰዎችም የዛኑ ያህል ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ በሀዋሳ በተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ራሱ የኛም ይሁን የተጋጣሚ ደጋፊዎች ጥሩ አስተያየት ይሰጡናል፡፡ ይሄ ደግሞ ያበረታታሀል፡፡ እኔ ይህን አጨዋወት ብቸኛው አማራጭ አድርጌዋለሁ፡፡ ምንአልባት በጥቂት ጨዋታዎች ላይ የተለየ ነገር ይዘህ ልትገባ ትችላለህ፡፡ ከዛ ውጪ ግን መለያዬ የሆነውን ዘይቤ ትቼ በሌላ መንገድ አልቀርብም፡፡ እንደአገርም ችግራችን ብዬ ከምጠቅሳቸው ነገሮች አንዱ ይሄ ነው፡፡ በተለያዩ አለምአቀፍ  ጨዋታዎች አቅማችንን በማያሳየው የማይሳኩ ረጃጅም ቅብብሎች እየተጠቀምንና የአየር ላይ ሽሚያዎች እየተበለጥን የምንወጣባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው፡፡ የያዝናቸውን ተጫዋቾች ማዕከል ያደረጉ ጨዋታዎችን መጫወት ነው ጥቅም አለው ብዬ የማምነው፡፡


ለምትታወቅበት የአጨዋወት አቀራረብ የተጫዋቾች አመላመል ሒደትህ ምን አይነት መስፈርቶች ላይ ይመሰረታል?

ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾችን ለመመልመል በራሱ የምትገደብባቸው ሁኔታዎች ይገጥሙሀል፡፡ የምታሰለጥንበት ክለብ የሚፈልገው ነገር ይኖራል፤ በክለቡ የገንዘብ ቸግር ይገጥምሀል፤ የሊጉ የመተዳደሪያ ስርዓት በራሱ አመቺ ላይሆን ይችላል፡፡ እነዚህና ያልጠቀስኳቸው ነገሮች ተጽእኖ ያሳድሩብሀል፡፡ የሜዳ ውስጥ በሆኑ ጉዳዮች ደግሞ በብዛት የምመርጠው ቴክኒካዊ ለሆኑ ስራዎች አመቺ የሆኑ ተጫዋቾችን ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹን ነገሮች በሙሉ በሒደት የምታሳድጋቸው ስለሆኑ ማለቴ ነው፡፡ በመጀመሪያ የማስቀድመው ኳስ የመቻል ክህሎትን ነው፡፡  ተጫዋቹ የሚመጣው ሌላ ስራን ለመስራት ሳይሆን ኳስን ለመጫወት ነው፡፡ አንዳንዴ በየቦታው ላይ የሚቀመጡ መስፈርቶች ምሉዕ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ተክለ ሰውነትንና ፍጥነትን ብቻ ከተከተልክ አንኳሩን ጉዳይ ልትስትና ወደ ስህተት ልታመራ ትችላለህ፡፡ ችሎታን አሰቀድመህ ታይና የአካል ብቃትና ተክለሰውነትን ጉዳይ ታስከትላለህ፡፡ አካላዊ ጥንካሬ ካላቸው ጥሩ ነው፤ ከሌላቸውም በሒደት እንዲያዳብሩት ታደርጋለህ፡፡ ቴክኒካልና በእግር ኳስ አእምሮአዊ ጉዳዮች ብሩህ የሆነ ሰው ተቀዳሚ ምርጫዬ ነው፡፡ እይታው ጥሩ የሆነና ኳስን አውቆ የሚጫወት ተጫዋች አስቀድማለሁ፡፡ በእርግጥ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ባሰለጠንክባቸው ክለቦች አግኝተሀል ወይ ብለህ ብጠይቀኝ መልሴ ‘አላገኘሁም፡፡’ ይሆናል፡፡ በተቻለ መጠን ግን ያሉኝን ተጫዋቾች እኔ ወደምፈልገው መንገድ ለማምጣት እሞክራለሁ፡፡



ቀጣይ ተጋጣሚ ቡድኖች አጨዋወት ላይ ተመስርተህ የምታሰራው የተለየ ስልጠና አለህ?

ጠላትህን ሳታውቅ እኮ ወደ ውጊያ አታመራም፡፡ይሄ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ዝምብለህ በጨለማ ውስጥ በጀብደኝነት እንደ መሄድ ነው፡፡ በእርግጥ የአገራችን ውድድሮች ቅድመ ግምገማ ለማድረግ ግልጽ የመረጃ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ በስካውቲንግ የአንድ ሳምንት ጨዋታ ላይ ብቻ አይደለም ሀሰሳ የምታከናውነው፡፡ የአንድ ሙሉ አመት ግምገማም ልታካሂድ ትችላለህ፡፡ ከሚከተሉት የአቀራረብ ዘዴ በተጨማሪ ያሏቸውን ተጫዋችች ችሎታን ሁሉ ትገመግማለህ፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ተጋጣሚህን ለማወቅ ትሞክራለህ፡፡ የማገኛቸውን መረጃዎች በደንብ ካየሁ በኋላ በክፍል ውስጥ የተቀረጹ ቪዲዮዎች ካሉ እነሱን በመጠቀም ከሌሉም በሌሎች መረጃዎች ተመስርተን ከተጫዋቾቼ ጋር እወያይበታለሁ፡፡ በተጋጣሚ ጉዳይ ብዙ ጊዜን ማባከን የለብንም፤ ግን ደግሞ ማየትና ማወቅም ይኖርብናል፡፡ ቡናን ስንገጥምም ሆነ ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት የተለያዩ መልኮች ያሏቸው ዝግጅቶች ነው የምናደርገው፡፡ ቀጣይ ተጋጣሚዎቻችንን ማዕከል ሳናደርግ አንሰራም፡፡ በሜዳና ከሜዳ ውጪ ስንጫወት እንኳ የተለያዩ አቀራረቦች ስለሚገጥሙህ የምታደርገው ዝግጅትም እንዲሁ ይለያያል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ስለ ተጋጣሚ ቡድን በጥልቀት ተወያይተንና ከ90% በላይ የሚሆነው ነገር ሁሉ ሜዳ ውስጥ እየተከሰተ ተሸንፈን ስንወጣ ነው፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ‘ባልነገርኳቸው’ ሁሉ ያስብለኛል፡፡ ለምሳሌ በአዳማው (1-0 የተሸነፉበት) ጨዋታ በላፕቶፔ ውስጥ የምታየው የቡድኑን ጠንካራና ደካማ ጎን፣ ወሳኝ ተጫዋቾች ሚና፣ጎል የሚያገኙበትን መንገድ……. የሚያሳዩ ምስሎችንና የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚሁ ሁኔታ ውጤትን ስታጣ እጅጉን ያሳዝንሀል፡፡

ከጨዋታው በኋላ በነበረን ውይይትም ‘የምነግራችሁን ነገር ሞክራችሁት ከአቅም በላይ ከሆነባችሁ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ የማትሞክሩትና የማተገብሩት ከሆነ ግን የኔ ቀድሞ መንገር አስፈላጊነት ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው?’ ስል ጠይቄያቸዋለው፡፡ በእርግጥ ጥሩ ግምገማ ለማድረግ የሚያስችሉ የምስል መረጃዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች የሉም፤ ራሱ ዋናው አሰልጣኝ ነው ስራውን የሚሰራው፡፡ አልፎ አልፎ ፎርማት አዘጋጅተህና ሰዎችን ልከህ የምታገኘው መረጃም በቂ አይሆንም፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ለአሰልጣኙ ግብአቶች ስለሆኑ ወደፊት የአሰልጣኞች አባላት ቁጥር ሲጨምር በጥሩ ሁኔታ እንሰራበታለን ብለን እናስባለን፤ ተስፋም እናደርጋለን፡፡ ባለንና ባቅማችን ግን መሞከራችንን እንቀጥላለን፡፡



ወጥ ያልሆነ አቋም የሚያሳዩና ተገማች ያልሆነ አቀራረብ ያላቸው ቡድኖችን ስካውት ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ ነው? ቅድመ-ግምገማህና ሜዳ ላይ የሚገጥሙ ልዩነቶችንስ በምን መልኩ ታስታርቃቸዋለህ ?

ስካውት ያደረግከው ነገር ሙሉ በሙሉ ሜዳ ላይ እንደማይገጥምህ ቀድመህ መገንዘብ ይኖርብሀል፡፡ ተጋጣሚህ በራሱ እኮ ላንተ ጨዋታ ብቻ የሚቀርብበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከራስህ አንፃር በግምት ደረጃ የምታስባቸው የተጋጣሚ አቀራረቦች ይኖራሉ፡፡ ፍጹም ያላሰብከውና ያልጠበቀው ሆኖ ሲቀርብ ደግሞ እዚያው ሜዳ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እያጤንክ ማስተካከያ እርምጃዎችን ትወስዳለህ፡፡ በጨዋታው ሒደት ከተጋጣሚህ ቡድን ልትጠቀምበት የሚያስችል ክፍተት ካለ-መጠቀም፣ ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርብህ ከሆነም-መጠንቀቅ አለብህ፡፡ ትልቁ ነገር በስካውቲንግ መረጃዎች ጥገኛ አለመሆንና የራስህ ነገሮች ላይ አትኩረህ መስራትህ ነው፡፡



ስለ መርህ እናውራ ፤ በአሰልጣኝነት ሙያህ በመርህ ደረጃ ቅድሚያ የምትሰጠው ምንድነው?

ስነ-ምግባር! የመጀመሪያውም የመጨረሻውም መርሔ ዲሲፕሊን ነው፡፡ ሁሉም ነገር መልካም የሚሆነው ስራህን ስታከብር ነው፡፡ ዲሲፕሊን ማለት እኮ ሌላ ነገር  ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ስለ ቡድን መንፈስ ሲናገሩ ትሰማለህ፡፡ እሱም ቢሆን ስራን የማክበር ማሳያ ነው፡፡ ስራህን ስታከብር-ሰዓትን፣ የቡድን አጋርህን፣ አሰልጣኝህን፣ አለቆችህን፣ ደጋፊንና የተጋጣሚ ቡድንን አጠቃላይ አባላትን ታከብራለህ፡፡ በውጤቱ ደግሞ አንተ በራሱ ትከበርበታለህ፡፡ ስለዚህ እኔ ቅድሚያ የምሰጠው ስራህን እንድታከብር ስለሚያስችል ስነምግባር ነው፡፡


ተጫዋቾችህ በስነምግባር የታነጹ፣ስራቸውን ወዳድና ሙያቸውን አክባሪ እንዲሆኑ የምታደርግበት መንገድስ? ቀድምት አንጋፋ አሰልጣኞችን ባነጋገርንበት ወቅት የአብዛኞቹ ምላሽ <በተጫዋቾች ውስጥ አክብሮታዊ ፍርሀት እንዲያድርባቸው የማድረግ ዝንባሌ> ስነስርዓት በማስጠበቅ ረገድ እንዳገዛቸው አስረድተውናል፡፡ አንተ ደግሞ ከሁለት አመት በፊት በሰጠኸን ቃለ መጠይቅ <ተጫዋቾችን በእውቀት ልቆ በመገኘት እንዲሰሙህ ማድረግ> የሚል ምላሽ ሰጠኸን ነበር፡፡ እስኪ ይህን አብራራልን…

ልክ ነው፤ አሰልጣኝ በመጀመሪያ ደረጃ አርአያ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንተ የማታደርገውን ነገር ተጫዋቾች እንዲያደርጉ መፈለግ አግባብነት የለውም፡፡ እኔ መፈራትን አልፈልግም፤ እንድከበር ግን እሻለው፡፡ መፍራት ብቻውን ግንኙነትን ያራርቃል፤ በማከበር ውስጥ ደግሞ የተሻለ የሚባል መቀራረብ ይፈጠራል፡፡ እንዳልከውም በማክበር ውስጥ መጠነኛ ፍርሀት አለ፡፡ ተጫዋቾችህ እንደ ሰው የሚሳሳቱት ነገር ይኖራል፤ ሳትሰለች ከስህተቶች እንዲማሩ ማድረግም አለብህ፡፡ እኔ ይሄን በማድረጉ በኩል አልሰለችም፡፡ ሆኖም ግን ዝም ብለህ እየመከርክ ብቻ የምትሄድበትን አሰራር የሙጥኝ ማለት የለብህም፤ በቅጣት የሚማሩበት አካሄድ የግድ ከሆነ-ታደርገዋለህ፡፡ ምክንያቱም እውነታው በምክር የሚመለስ አለ፤ በቅጣት የሚስተካከል አለ፤ምንም የማያሻሽለውም እንደዚሁ አለ፡፡ ሁሉንም በአንድ ጊዜ መለወጥ ባትችል ቀስበቀስ በሒደት የሚያስቸግሩትን እያሻሻልክና እየመለስክ ትመጣለህ፡፡ የኔ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው፤ ያን ያህልም ከባድ ነገር አልገጠመኝም፡፡ በዚህ መንገድ ነው እንግዲህ ለመጓዝ የምሞክረው፡፡



የአንተን ሐሳብ በተጫዋቾች ውስጥ ማስረጽ ወይስ ከተጫዋቾቹ ችሎታ ተነስተህ ሀሳብን መወሰን-የትኛውን ታደርጋለህ?

እኔ በማስበው መንገድ እንዲጫወቱልኝ እሻለው፡፡በስሬ ያሉት ተጨዋቾች የምፈልገውን የአጨዋወት ዘይቤ የማይተገብሩልኝ ከሆነ ተጫዋቾቹ በቀላሉ የተሻለ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን ሁኔታ እፈጥራለው፡፡ ለምሳሌ በደደቢት ሳለሁ ታጋይ የሚባል ከታች ጀምሮ አብሮአቸው የመጣ የግራ መስመር ተጫዋችና መንግስቱ (ማሲንቆ) በእኔ ፍልስፍና የሚሄዱ አይመስሉም ነበር፡፡ ሆኖም በክለቡ ቆይታዬ እስከ 21ኛው ሳምንት ድረስ ሁለቱ ተጫዋቾች በከፍተኛ የብቃት ደረጃ ቡድኑን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ባላቸው ችሎታ ለክለባቸው ጥሩ ግልጋሎት እንዲሰጡ ማድረግ ትችላለህ፡፡ ዋናው ነገር የተጫዋቾቹ የማዳመጥና የመቀበል ጉዳይ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ የአጨዋወት ባህሪያቸው ለፍልስፍናህ አመቺ ባይሆን እንኳ በጥረትህ የተሻሉ እንዲሆኑ ታደርጋለህ፡፡ የቡድን ልምምዱ በራሱ ተጫዋቾችን ወደ ሲስተሙ እንዲያዘነብሉ ይገፋፋቸዋል፡፡ አላስፈላጊ የሆኑ በጣም ረጃጅም ቅብብሎችን እየከወነ የሚያስቸግርህን ተጫዋች በጠባብ የሜዳ ክፍል ላይ ወስነኸው ረጃጅሙን ኳስ የት ያደርገዋል? መፍትሔ መፈለግ ይጀምራል፤ ቀድሞ የሚቀበለውን ተጫዋች ርቀት ማየት ይለምዳል፤ አቋቋሙን ያያል፤ የመጀመሪያ የኳስ ንክኪውን ያስተካክላል፤ ስለዚህ ተገቢውን ልኬት የጠበቀ ቅብብል እንዲያደርግ ታግዘዋለህ፡፡ በዚህ ዘዴ ተጫዋቾች በመጠኑም ቢሆን ወደምትፈልገው ደረጃ ያድጉልሀል፡፡ እኔ ውስጥ ያለው ሐሳብ  ተጫዋቾች ጋር እንደደረሰና በተግባር ለማሳየት ያላቸውን ፍላጎት መረዳት እፈልጋለሁ፡፡ የማስበውም እኔ የምፈልገውን ሐሳብ በእኔ ደረጃ የመገንዘብ ሁኔታ ባይኖር እንኳ የመተግበር አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ ነው፡፡



ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ከተላመዱት የመጫወቻ ቦታቸው ውጪ ባሉ ሌሎች ሚናዎች ሲመደቡ በምን ሁኔታ ነው የሚቀበሉት? አረዳዳቸውን እንዲያስተካክሉስ ምን አይነት ድጋፍ ይደረግላቸዋል? የሚና ለውጡ የሚያስገኘው ጥቅምስ?

የሚገርመው አይደለም አዲስ ሚና ፎርሜሽኖች እንኳ ሲቀያየሩ ተጫዋቾች ይታወካሉ፤ ደስተኞች አይሆኑም፤ ውጤት ከተበላሸም መንስኤውን ከፎርሜሽኑ መለወጥ ጋር ያያይዙታል፡፡ ይህ ሁኔታ በ2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቡና አጋጥሞኛል፡፡ ከእኔ በፊት በሁለት አጥቂ 4-4-2ን ነበር የሚጠቀሙት፤ እኔ ደግሞ በሶስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች መስራት ፈለግኩ፡፡ ተክሉን ከፊት አጥቂነት ወደ መስመር አጥቂነት ለወጥኩት፤ በጣም ተጨናነቀ፤ ጎሎችን ከመስመር እየተነሳ የሚያስቆጥርም አልመስልህ አለው፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ልምምዶቹ ሶስትና አራት ቦታ ተከፋፍለው በየመጫወቻ ክፍሉ እንዲሰሩ በማድረግ የ11-ለ11 መልክ እየሰጠናቸው፣ ተግባራዊ የድግግሞሽ ልምምዶች(drills) እያደረግን፣ የእያንዳንዱ ተጫዋች ሚናንና እንቅስቃሴያዊ ቦታ አያያዝን በተመለከተ (ለምሳሌ የፊት አጥቂ ሆኖ ጀርባውን ለቡድን አጋሮች የመስጠት ባህሪ ያለው ተጫዋች ይቸገራል፡፡) የክፍል ወስጥ ትምህርቶችን በመስጠት እንዲረዱኝ ለማድረግ እጥራለሁ፡፡ የመሀል ተከላካዮችንም የቦታ አያያዝ በተጋጣሚ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ተመስርቼ መሆን ያለበትን አሳያለሁ፡፡ በሒደት ይቀበሉሀል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ግን በከፍተኛው ትቸገራለህ፡፡ በሁሉም ቡድኖች የሚገጥምህ ችግር ነው፡፡  አንዳንዱ ቦታውን ወይም አዲሱ ሚናውን ይጠላዋል፤ብቃቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድርበት የሚመስለውም አለ፤ ስለዚህ የማሳመን ስራ መስራት አለብህ፡፡ እየተላመዱት ሲሄዱም ይረዱታል፡፡ በቡናም ሆነ በሀዋሳ ብዙ ጎሎችን አስቆጥረናል፤ እጥፍ የሚሆን ጊዜ ደግሞ የተጋጣሚን ጎል በአደገኛ ሙከራዎች ፈትነን ስተናል፡፡ በጨዋታ እስከ 16 እና 17 የሚደርሱ ሙከራዎችን የምናደርግበት ጊዜም አለ፡፡ ፍሬው ሰለሞንን እናንሳ፡- ባለፈው አመት ለአዋሳ ከአጥቂ ጀርባና ከመስመር አጥቂነት እየተነሳ ወደ 10 ጎሎች አስቆጥሯል፤ የዛኑ ያህልም አምክኗል፤ ለጎል የሚሆኑ ቅብብሎችንም ፈጽሟል፡፡ በመጀመሪያ ግን ፍጹም አልመሰለውም ነበር፡፡ ጋዲሳም እንዲሁ ሚናው ሲሰጠው አልተመቸውም ነበር፡፡ ኋላ ግን እየተላመደው ጥሩ ብቃቱን ማሳየት ቻለ፡፡


በአገራችን ተጫዋቾች በቡድናቸው ካላቸው ተለምዶአዊ ሐላፊነት ውጪ ሌላ ሚና ሲሰጣቸው በሚያሳዩት አንፃራዊ ብቃት ላይ በመመርኮዝ የሁለገብነት ስያሜ ይቸራቸዋል፡፡ ባንተ ሀሳብ በእግርኳስ የተጫዋቾች ሁለገብነት መመዘኛ መስፈርቱ ምንድን ነው? ሁለገብነትን ተንትንልን

በዘመናዊው እግርኳስ ስለ “Versatality Role” የምናወራ ከሆነ በተፈጥሮአቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን የሚመለከት ሐሳብ ነው፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾችን ከመደበኛ ቦታቸው ውጪ ምንም አይነት ተደራቢ ሚና ልታስሞክረው አትችልም፡፡ ሐላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችሉ ብዙ ልጆች አታገኝም፡፡ በግሌ ሚናው ከትምህርትና ስልጠና ጋር የሚያያዝ አይመስለኝም፡፡ በተፈጥሮ የትኛውም ቦታ ላይ ብታሰልፈው ጥሩ የሚጫወትና ተመጣጣኝ ብቃት የሚያሳይን ተጫዋች ባህሪ ያሳያል ብዬ አስባለው፡፡ በቀደመው ዘመን እግርኳሳችን ውስጥ ደርሼበት የተመለከትኩት ንጉሴ ገብሬ ተከላካይ ቦታ አልፎአልም አጥቂ ሆኖ በጥሩ ብቃት ሲጫወት አስታውሳለሁ፡፡ አዳነ ግርማን ብንወስድም በሀዋሳ ተከላካይ የነበረ ተጫዋች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የመሀል አማካይ፣ ከአጥቂ ጀርባ የሚሰለፍ የማጥቃት አማካይና አጥቂ ሆኖ ሲጫወት እንመለከታለን፡፡ ይህንን ለአዳነ ማንም አስተምሮት አይመስለኝም፡፡ የነዚህን አይነት ተጫዋቾች ሚና የማያይዘው ከተፈጥሮ ችሎታ ጋር ነው፡፡



የሁለገብነት ፅንሰ ሀሳብን በተሳሳተ መንገድ በመተግበር ምክንያት ተጫዋቾች የሚመክኑበት አሉታዊ ሒደት ላይስ ምን ትላለህ?

የሚባክኑበትና ካንዱም የሜዳ ላይ ሚና ሳይሆኑ የሚቀሩበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ እንደ ተጫዋቾቹ ሁኔታ ይወሰናል፡፡ አሰልጣኞች በቡድናቸው ውስጥ ክፍተት አለ ባሉበት ቦታ ሁሉ ያስቧቸዋል፡፡ በሒደቱ ተጎጂዎቹ የሚሆኑት ተጫዋቾቹ ናቸው፤ አሰልጣኙ ክፍተቱን በመድፈን በኩል ጊዜያዊ ጥቅም ሊያገኝ ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ እንደዚህ አይነት ልጆች ለቡድን መስዋዕት ነው የሚሆኑት፡፡ አንዳንዶች በየትኛውም ቦታ ላይ ተጫውተው ውጤታማ የሚሆኑ አሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ቦታ ላይ የሚጫወቱ በተመሳሳይ የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን ስታገኝ አንደኛውን በሌላ ሚና የምትጠቀምበትን ውሳኔ የምታሳልፍበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡



‘ሁለገብ ነው፡፡’ ብሎ ከመወሰን በፊት እምቅ ክህሎትን በመረዳት ረገድስ ሊኖር ስለሚገባ ምልከታ ምን የምትለን ይኖራል? አንዳንድ ተጫዋቾች አሰልጣኝ አሊያም ደግሞ ክለብ ሲቀይሩ በነባር ቦታቸውና ሚናቸው የብቃት ከፍታን ወይም ዝቅታን ያሳያሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በተለየ የሜዳ ውስጥ ሀላፊነት የተሻለ ሲያበረክቱ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ያሬድ ዝናቡ ባንተ የአዳማ ቡድን ውስጥ ተከላካይ ነበር፤ ጊዮርጊስ ሲገባ ደግሞ አማካይ ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ ያለህ ሐሳብስ?

ያሬድ በጣም ብዙ አይነት ብቃት የነበረው ልጅ ነው፡፡ በተከላካይ ዲፓርትመንት እንኳ በግራው በኩል በመስመር ተከላካይነትና በግራ የመሐል ተከላካይነት እንዳልከውም በ”ስኪመርነት” በጣም ጥሩ ይጫወት ነበር፡፡ የሱ ለረጅም ጊዜ በብቃቱ ከፍታ አለመዝለቅ ከሁለገብነት ሚናው ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ ከጤንነት ሁኔታው ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ አስፈላጊ የማይመስሉ የቦታ ቅይይሮች የሚደረጉባቸው ተጫዋቾችን ትመለከታለህ፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የምንተስኖት አዳነን ሁኔታ ማንሳት እንችላለን፡፡ ጥሩ የመሀል ሜዳ አማካይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የመሀል ተከላካይነት ብቃት ሊኖረው ይችልም ይሆናል፤ ግን ደግሞ ከአማካይነቱ በላቀ በተከላካይነቱ የበለጠ ያበረክታል ብዬ ለመናገር  እርግጠኝነት  አይሰማኝም፤ ጥርጣሬ ያድርብኛል፡፡ በተለይ በትልቅ ደረጃ ባሉ ክለቦች በምትፈልገው ቦታ ላይ የሚጫወት ተገቢውን ተጫዋች የማግኘት እድልህ ከፍ ያለ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ካልተቸገርክ በስተቀር ተጫዋቾችን በየቦታቸው  ማሰለፍ ጥሩ ብቃታቸውን እንዲያሳዩ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ከአጨዋወት ባህሪ ጋር በተያያዘ አጥቂን ወደ ተከላካይ፣ ተከላካይን ደግሞ ወደ አጥቂነት በማሸጋሸግ ጉዳይ ላይ እርግጠኝነት ያልታከለበት ውሳኔ ማሳለፍ ለተጫዋቾቹ ጥሩ አይሆንም ብዬ ነው የማስበው፡፡


በልምምድ ወቅት በምታየው የተሻለ የተመሳሳይ ሚና ባለቤት ተጫዋቾች ብቃት ምክንያት እነዛን ተጫዋቾች የግድ ቋሚ 11 ውስጥ ለማካተት በሚል የምታደርገው የፎርሜሽን ለውጥ አልያም ከቦታው ውጪ የማሰለፍ አማራጭን ትጠቀማለህ ? (ለምሳሌ ሁሉንም አጥቂዎች ቋሚ አድርጎ ለአንደኛው የአማካይነት ሚና መስጠት)

እንደነዚህ አይነት ጉዳዮች ውጤት ልታመጣ የምትችልባቸውን መንገዶች ስታስብ የሚመጣልህ የመፍትሔ ሀሳብ ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ እንደተጠቀሰው ከፎርሜሽኖች ለውጥ አንስቶ በተለያዩ የመጫወቻው ክፍሎች የተጫዋቾቸን ቁጥር የማሸጋሸግ ስራ ልትሰራ ትችላለህ፡፡ ነገርግን ሁሉም ጥሩ ስለተንቀሳቀሱ እኩል የመሰለፍ እድል ማግኘት አለባቸው ብዬ አላስብም፡፡ የመሀል አማካይ እያለኝም አጥቂው እንዲገባና የአማካይነት ሚና ይዞ እንዲጫወት የማድረግ ሐሳብ በፍፁም የለኝም፡፡ አሰልጣኝ ሆነህ ሁሉንም አይደለም ሁለት ሰው ማስደሰት አትችልም፡፡ ሰው ለማስደሰት ብለህ አይደለም ስራህን የምትሰራው፤ ውሳኔህ ላያስደስታቸው ይችላል፤ ግን ማክበር አለባቸው፡፡ ሁሉም አጥቂዎች ወይም አማካዮች ጥሩ ላይ መሆናቸው መልካም ነገር ነው፤ ግን ደግሞ ሁሉም መጫወት አይችሉም፡፡ ሁኔታው የቡድን መንፈስን ይረብሻል፤የቡድኑን ቅርጽም እንድትቀይር ትገደዳለህ፡፡ውጤታማ ስለማያደርግም ጉዳቱ እያመዘነ ይሄዳል፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *