” በሀዋሳ ከተማ በጣም ደስተኛ ነኝ ” ታፈሰ ሰለሞን

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ በእለተ ሐሙስ ሀዋሳ ከተማ የአምናውን ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 4-1 በሆነ ውጤት ሲረታ በጨዋታው ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ታፈሰ ሰለሞን ሁለት ጎሎችንም በስሙ አስመዝግቧል። የቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኒያላ አማካይ ዬለፉትን ሶስት የውድድር ዘመናት በሀዋሳ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል። ታፈሰ ስለወቅታዊ ድንቅ አቋሙ እና ስለ ግለ ባህሪው እና ስለወደፊት እቅዶቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርጓል፡፡

ዘንድሮ በየጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረግክ ትገኛለህ። ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠማችሁበት ጨዋታ ላይም ልዩነት ፈጣሪ ነበርክ። በአጠቃላይ ስለጨዋታው ምን ትላለህ ?

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ከውጤት ጋር የታገዘም ነበር። ጨዋታውን ትኩረት ሰጥተነው ነበር ፤ ምክንያቱም ያለንበት ደረጃ እና ውጤት ጥሩ ስላልነበር እና ጫናዎች ስለነበሩብን እንዲሁም ተጋጣሚያችን ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመሆኑ በደንብ ነበር ስንሰራ የነበረው። እንደታየው ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። ለኔም ጥሩ መሆን ጓደኞቼ ናቸው ምክንያቶቹ።

በጨዋታው ያስቆጠርካቸው ጎሎች በጣም አስገራሚ እና በራስ መተማመንህን ያየንባቸው ነበሩ። ችሎታህን አውጥተህ የተጫወትክበትን መንገድ ግለፅልን ?

መጀመሪያ ተናግሬዋለው። አንደኛ የቡድን ጓደኞቼ የነበራቸው መንፈስ ደስ ይል ነበር። ከጨዋታው በፊት በነበረን ስብሰባም ስንነጋገር የነበረው ይሄንን ነው። ግለኝነት ቡድናችን ውስጥ ነበር። አሁን ግን እንደ አንድ ሆነን ተባብረን ነበር። ጊዮርጊስንም እንደጠበቅነው አላገኘነውም። ስብስቡ ከእኛ ጋር አይገናኝም ፤ ያሉት ተጫዋቾች አቅምም ይታወቃል። አግዝፈንም አይተን ነበር ግን ሜዳ ላይ ስታይ በተለይ 15 እና 20 ደቂቃ ጫን ሰንልባቸው ብትንትን አሉ። በተለይ ጎሎች እየገቡ በመጡ ቁጥር አንደኛ የነሱ ድክመት ነው ትልቁ እና ዋናው ግን በቡድናችን ውስጥ የነበረው መንፈስ እንደትልቅ ነገር እሱ ይመስለኛል የረዳን ፡፡

ቡድኑ በተከታታይ ከውጤት እየራቀ ነበር። በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረጋችሁም ነጥብ ትጥላላችሁ። ያለፉትን ጨዋታዎች እንዴት ትገልፃቸዋለህ ?

በጣም ነው የሚያስቆጨው። አስታውሳለሁ ከመቐለ ጨዋታ በኃላ ነው ቡድናችን የተረበሸው። ያን ጊዜ አቻ ወጥተን ነበር። በእግር ኳስ ሁሉም ውጤቶች የሚጠበቁ ናቸው ፤ ከዛች አቻ በኃላ ግን ሁሉ ነገራችን ተዘበራረቀ። ማገገምም አልቻልንም ነበር። ይህን ጨዋታ እናሸንፋለን እያልን እንጠባበቅ ነበር። ነገር ግን በሁሉም ጨዋታ ነጥብ እየጣልን መጥተናል። የቡናን እና የጊዮርጊስን ጨዋታ ግን ትኩረት በመስጠት ነው የተጫወትነው። ከቡናው ጨዋታን ከሜዳ ውጭ አቻ ይዘን ስንመለስ የጊዮርጊስ ጨዋታ ደግሞ ያለንን አሟጠን በመጫወት አሸንፈን ወጥተናል።
በሜዳ ውስጥ በምታደርገው አዝናኝ እንቅስቃሴ ሁሉም ተመልካች ሲደሰት እና ቡድኑንም ባንተ ምርጥ ብቃት ይዘህ ስትወጣ እናያለን። ከሜዳ ውጭ ያለብህ ግለ ባህሪ ግን ጥያቄ ይነሳበታል። እነኚህ ያልተገቡ ባህሪዎች በእግርኳስ ህይወትህ ላይ ተፅእኖ አይፈጥሩብህም? በብሔራዊ ቡድንም ካንተ ያነሱ ተጫዋቾች ሲጫወቱ አንተ እድል አለማግኘትህ ካለህ የባህሪ ችግር እና ከአሰልጣኝ ጋር ባለመግባባትህ ምክንያት የመጣ ነው ሲባል ይሰማል..

ጥሩ ጥያቄ ነው። ከዚህ በፊት ስፖርተኛም እንደመሆኔ መጠን ወጣትነት በውስጤ ነበር ፤ በቃ እዝናና ነበር። ሆኖም በሂደት ህይወት ራሱ ያስተምርሀል። አሁን ላይ እናንተ ሚዲያ ስለሆናችሁ ለመዋሸት ሳይሆን በርግጠኝነት የምናገረው አሁን ላይ ራሴን እጠብቃለሁ። በርግጥ አሁንም እዝናናለሁ ፤ አልዝናናም ማለት አልችልም። እንደዚህ ቀደሙ ባይሆንም በልክና በመጠኑ እዝናናለሁ። በተለይ ጨዋታወች ሲደርሱ ራሴን በጣም መጠበቅ ጀምሬያለሁ። በዚህ ሰአት ልቅ የሆነ ነገር አላደርግም። በእድሜዬም እየበሰልኩ ስሄድ ነገሮችን ማሰብ ጀምሬያለሁ። አሁን ለምሳሌ ኢንተርቪው በምትሰራኝ ሰአት እንኳን ኖርማል ነኝ። ሲቀጥል እንደሌላው ቀን እንደዚህ ቀለል ያለ ልብስ ለብሼ አልመጣም። ከዚህ ነገር እንድወጣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስተዋጽኦ ነበረው። እርሱን በሚገባ ማመስገን እፈልጋለሁ። አንድ ሰሞን ጥሩ አልነበርኩም ፤ እየተዝናናሁ እና እየጠጣሁ ነበር ኳስን እጫወት የነበረው። ኳሱ እየከበደኝ እና እንደፈለግኩ መጫወት አቃተኝ። በነዛ ወቅቶች ውበቱ አይዞህ ይለኛል። ከዛ ነገር አሁን ላይ ወደዚህ መምጣት ሊቸግር ይችላል። ሁሌም ግን ይረዳኝ ነበር። አምኖ ያሰልፈኝም ነበር፡፡

በብሔራዊ ቡድን ቆይታህ በአንተ የአጨዋወት ባህርይ ደስተኛ ያልሆኑ አሰልጣኞች ነበሩ። በዚህ ጉዳይ ላይ አንተ ምን ትላለህ?

እኔ ኳስን ይዤ መጫወትን ነው የምፈልገው። በጨዋታውም ላይ ( ከጊዮርጊስ ጋር ) ስንጫወት አሰልጣኝ ውበቱ በተደጋጋሚ ኳስ ይዘን እንድንጫወት ነበር የሚነግረን። ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ መሀል ላይ ስንጫወት አልነበረም ፤ ዳር እና ዳር ወጥተን ነበር ስንጫወት የነበው። እኔም ኳስን ድሪብል እያደረጉ መጫወትን ነው የምወደው። ይህን ስል ግለሰቦች ያስፈልጋሉ። አሁን እኔ ብሔራዊ ቡድን በነበርኩበት ወቅት በቅርቡ በአሸናፊ ጊዜ እሱን መተቸቴ ሳይሆን ያየሁትን ነው። ሰው ስታልፍ አይወድም። ቆመህ ረጅም ኳስ እንድትጫወት ነው የሚፈልገው። የኔ ባህርይ ደግሞ ኳስ ይዞ መጫወትን ፣ ረጅም መምታት ሳይሆን ሰው እየቀነሱ መጫወት ነው። ከብሔራዊ ቡድንም በወቅቱ ስቀነስ አልተመቸኝም። በዲሲፕሊን ነው። ሆቴል ግባ ስባል የማየው ነገር ስላልተመቸኝ ባለመግባቴ እንጂ በሌላ አልነበረም። እንዳንዴ የምታየው ነገር ደስ አይልም ፤ የሚያነሳሳ አሰልጣኝ ካልሆነ ምንም ማድረግ አትችልም። ስለዚህ ኳስ ይዞ መጫወት የሚችል ቡድን በጣም በጣም ደስ ይለኛል። ያም ይጠቅመናል ብዬ አስባለሁ ፡፡

ቀጣይ እቅድህ ምንድነው ?

ዘንድሮ ዝግጅት ስንጀምር ቻምፒዮን ለመሆን አቅደን ነበር። አሁንም እቅዳችንን አልተውንም። በሁለተኛው ዙር በተከታታይ በሜዳችን ጨዋታ ይኖረናል። ቢያንስ ከነሱ ጨዋታዎች ነጥብ ከያዝን መሪው ደደቢት ላይ እንደርሳለን። 29 ነጥብ ነው ያላቸው መድረስ ይቻላል።

ከዚህ በፊት ሱዳን የመጫወት እድል አግኝቼ በራሴ ችግር ሳልጫወት ቀርቻለሁ። አሁን ላይ እንደዛ አይነት እድል ባገኝ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ያን ያህል አልጓጓም። አሁን ላይ ባለሁበት ሀዋሳ ከተማ በጣም ደስተኛ ነኝ። ወጥቶ ለመጫወትም ብዙም አላስብም። እኛ ሀገር እንዲህ የተሻለ ነገር ስታሳይ ብዙ ጊዜ ለምን ወጥተህ አትጫወትም ይባላል። ሆኖም ከሀዋሳ ጋር በመሆን ጥሩ ነገር የምናመጣ ይመስለኛል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በተለይ ከሜዳ ውጪ ያለውን ደካማ ሪከርድ በሁለተኛው ዙር ለማሻሻል ያላችሁ እቅድ ምን ይመስላል ?

ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይ ብዙ ጊዜ እንቸገራለን። እኛ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ስለምንጫወት ብዙ ጊዜ ኳስ አይበላሽብንም ፤ እንደፈለግን መጫወት እንችላለን።ኳስን በብዛት ለመቀባበልም ምቹ ነው። ወደ ሌላ ሜዳ ስንሄድ ግን የሜዳው ችግር እና ሌሎች ተጎዳኝ ነገሮች እንደፈለግን እንድንሆን አያደርገንም። በጣም የሜዳ ችግር አለ። ሀገር ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጭ ጥሩ ሜዳ ያለው የተወሰኑ ክልሎች ላይ ነው። ለዛም ይመስለኛል ቡድኖች ቶሎ በሚፈልጉት መንገድ ተጫውተው ግብ ያስቆጥሩብናል። እሱ ላይም ቢሆን ተነጋግረናል። በቀጣይ ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ላይ ከቻልን አሸንፎ ለመውጣት ካልቻልን ግን አስጠብቆ ለመውጣት እንጥራለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *