​ከፍተኛ ሊግ | ቡራዩ ነጥብ ሲጥል ለገጣፎ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊገ ዛሬ በተካሄዱ የምድብ ሀ ተስተካካይ ጨዋታዎች መሪው ቡራዩ ከተማ ከፌዴራል አቻ ሲለያይ ለገጣፎ ወደ ወልዲያ አምርቶ ወሎ ኮምቦልቻን አሸንፏል። 

ቡራዩ ላይ በተደረገው የቡራዩ እና ፌዴራል ፖሊስ ጨዋታ ባለሜዳዋቹ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መቅረብ የቻሉት ጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች በኢሳያስ ታደሠ ሙከራ ነበር።  ቡራዩዎች ኳስን ከራሱ የግብ ክልል ጀምሮ በመመስረት ወደ ተጋጣሚ ክልል ለመድርስ የሚያደርጉት ሙከራ በ8ኛው ደቂቃ ፍሬ ሊያፈራ በተቃረበበት ወቅት በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ደብሳ ሮባ ከአምበሉ አቡበከር ደሰላኝ የተቀበለውን ኳስ ወደግብ ለወጠው ሲባል በግቡ አግዳሚ በስተግራ በኩል ስቶታል። በ11ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኢሳያስ ታደሰ ላይ ጥፍት የተፈፀመ ቢሆንም የፌደራል ፖሊስ ተጫዋቾች ቀደም ተብሎ ሙጂሃይድ መሀመድ መሀል ሜዳ ላይ ኳስን በእጅ ነክቷል በሚል ከዳኛው ጋር ለተወሰነ ደቂቃ ውዝግብ ውስጥ የገቡ የነበረ ቢሆንም የዕለቱ ዳኛ የማስጠንቀቂያ ካርድ በመስጠት ጨዋታውን ለማረጋጋት ሞክረዋል። ከዚህ በኃላም በድጋሚ ጎል የማስቆጠር ዕድል ያገኘው ደብሳ ሮባ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

 

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ቡራዩ ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ ፊት ቢጠጉም ይህን ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀ ሲሆን ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ፌደራሎች በረዣዥም ኳሶች አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ለማጥቃት ወደ ፊት በሚሳቡበት ጊዜ ሳስቶ የሚታየው የቡራዩ ከተማዎች ተከላካይ ክፍል ለአደጋ ተጋልጦ የዋለበትም አጋጣሚ ተይቷል። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዋች በጫና ውስጥ የነበሩት ፌደራል ፖሊሶች በመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራቸው 22ኛው ደቂቃ ላይ ቻላቸው ቤዛ ከቀኝ መስመር የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከዚህ ውጪ ፌደራል ፖሊሶች በሊቁ አልታየ እና በሣሙኤል ብርሀኔ ያደረጓቸው ሌሎች ሙከራዎችም ተጠቃሾች ናቸው።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ በርካታ ክሰተቶችን አስተናግዶ አልፏል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ ኢሳይያስ ታደሰ በግንባሩ በመግጨት ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያውን ሙከራ ሲያደርግ በ50ኛ ደቂቃ ሊቁ አልታየ ለልይህ ገብረ መስቀል አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ልይህ ሳይጠቀምባት ቀርቷል። በ65ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳሙኤል ብርሃኑ ከግብ ክልል ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሊቁ አልታየ ወደ ጎልነት ለውጦ እንግዶቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ሆኖም ፌዴራሎች መሪ መሆን የቻሉት ለ6 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ71ኛው ደቂቃ ኢሳይያስ ታደሰ በአወዛጋቢ ሁኔታ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብነት ለውጦ ቡራዩን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የፌዴራል ፖሊስ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን የዕለቱን ዳኛ በመክበብ ያሰሙ ሲሆን ውዝግቡም ለተወሰነ ደቂቃ ዘልቆ በመጨረሻም በክስተቱ አላስፈላጊ ንግግር ሲናገር በነበረው አምበሉ ደሳለኝ ቡርጆ አማካይነት ክስ አስይዘዋል።

ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ ቡራዩ ከተማዎች ሶስት ነጥብ ይዘው ለመወረጣት ጥረተ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በተለይ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ኢሳይያስ ታደሰ በግንባሩ የገጨውን ኳስ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት ሚልዮን ደርሶ ቢመታውም ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች። ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ባኋላ የፌዴራል ፖሊስ ድንበሩ መርጋ ግብግብ የፈጠረ ሲሆን በተጫዋቾች ግልገላ ነገሮች ሊበርዱ ችለዋል።

ወሎ ኮምቦልቻ አንድ ጨዋታ በሜዳው እንዳያደርግ በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት ወደ ወልዲያ በማቅናት በመሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ስታድየም ለገጣፎ ለገዳዲን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል። የለገጣፎን ብቸኛ የድል ጎል ጌታነህ ደጀኔ ሲያስቆጥር የወሎ ኮምቦልቻው ሄኖክ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *