​አጥናፉ አለሙ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለ2019 የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ከቡሩንዲ ጋር ያደርጋል። በመጋቢት ወር መጨረሻ ለሚደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ዝግጅት ይረዳ ዘንድም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአሰልጣኞች ቅጥር አከናውኗል።

የብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኞነት ለመያዝ ሁለት አሰልጣኞች ቀርበው እንደነበር የታወቀ ሲሆን አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ባለፈው የማጣርያ ወቅት ቡድኑን ይዘውት የነበረው እና በቅርቡ ከጅማ አባ ቡናተለያዩት ግርማ ሐብተዮሀንስን በመብለጥ በዋና አሰልጣኝነት መሾማቸው ተነግሯል። አሰልጣኝ አጥናፉ በ2017 የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የተሳተፈውን ቡድን በመያዝ መልካም ጉዞ ሲያደርጉ በረዳትነት አብረዋቸው የሰሩት ረዳት አሰልጣኙ ጣሰው እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ አዳሙ ኑመሮ በ20 አመት በታች ቡድንም አብረዋቸው ይቀጥላሉ።

ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በ2017 ዛምቢያ ባስተናገደችው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማለፍ ሳይችል በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ተሸንፎ መውደቁ ይታወሳል። በቅደመ ማጣሪያው ሶማሊያን 4-1 በአጠቃላይ ውጤት ቢያሸንፍም በጋና በድምር ውጤት 5-2 ተሸንፎ ከማጣሪያው ውጪ ሆኗል። ኢትዮጵያ በ2001 ራሷ ባስተናገደችው ውድድር ከተሳተፈች በኋላም በድጋሚ በዚህ ውድድር አልታየችም።

ኢትዮጵያ በቅድመ ማጣርያው ከቡሩንዲ የምታደርገው ጨዋታ ከመጋቢት 21-23 ባሉት ቀናት ሲደረግ በቅርብ ቀናት በአዲስ አበባ ዝግጅት እንደሚጀመር ታውቋል። የተጫዋቾች ጥሪ ከወዲሁ መጀመሩም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *