ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የመልሱን ጨዋታ የሚያከብድበትን የአቻ ውጤት አስመዘግቧል

በአፍሪካ ቻምቺየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት የዩጋንዳውን ኬሲሲኤን በመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን 0 0 በሆነ ውጤት አጠናቋል።

ልዩ በነበረው የደጋፊዎቻቸው አጀብ ወደ ሜዳ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለአማራ ማሌ የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል በመስጠት ሊጉ ላይ በሚጠቀሙበት የ4-3-3 አሰላለፍ እና እምብዛም ለውጥ ባልታየበት የተጨዋቾች ስብስብ ጨዋታውን ጀምረዋል። እንግዳው ቡድን ኬሲሲኤ ደግሞ ብዙ የተጠበቀው ሻባን ሙሀመድን ተጠባባቂ ወንበር ላይ በማስቀመጥ በሁለት የፊት አጥቂዎች ጥምረት እየተመራ በዝርግ 4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል። 

ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት ፈረሰኞቹ አቡበከር ሳኒ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር አመዝነው ተጋጣሚያቸውን ጫና ውስጥ ለመክተት ሞክረዋል። በዚህ በኩል አቡበከር በመስመር ተከላካዩ ሙስጠፋ ኪዛ እና የመሀል ተከላካዩ ካቩማ ሀቢብ መሀል ሰብሮ ለመግባት ያደርግ የነበረው ጥረት ተጠቃሽ ነው። ሳልሀዲን ባርጌቾ ከማዕዘን ምት የተሻገረን ኳስ ከሳጥን ውስጥ በእግሩ ሞክሮ ተከላካዮች የተደረቡበት እንዲሁም አስቻለው ታመነ ከአበባው ቡታቆ ቅጣት ምት በግንባሩ ሞክሮ ኢላማውን ያልጠበቀበት ሙከራዎች ከጊዮርጊሶች በኩል በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች የተፈጠሩ ዕድሎች ነበሩ።

ሆኖም አስፈሪ ሙከራ የተስተዋለው 8ኛው ደቂቃ ላይ የኬሲሲኤው የፊት አጥቂ ፖውል ሙኩሪዚ ከሙሉአለም መስፍን የቀማውን ኳስ በቀጥታ አክርሮ ሞክሮ ሮበርት ኦዱንካራ ሲያወጣበት ነበር። ፊት መስመር ላይ ሙኩሪዚ በሴካፋ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ግብ ካስቆጠረው ዴሪክ ንሲምባቢ ጋር በሜዳው ቁመት የፈጠረው ጥምረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ሲረብሽ አምሽቷል። በተለይ 16ኛው ደቂቃ ላይ ሙኩሪዚ ከቀኝ መስመር አሳልፎለት ንሲምባቢ ከሳጥን ውስጥ የሞከረውን ኳስ ሮበርት በድጋሜ ሲያድነው 20ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በረዥሙ የተላከን ኳስ ንስምባቢ በተራው በግንባሩ ጨርፎለት ሙኩሩዚ ከሮበት ጋር ተገናኝቶ ከመሞከሩ በፊት አስቻለው ደርሶ አውጥቶበታል። በተቀሩት ደቂቃዎችም ቡድኑ የሚጀምራቸው ማጥቃቶች ከአማካይ ክፍሉ አልፈው ሁለቱ አጥቂዎች ጋር በደረሱ ቁጥር ኬሲሲዎች ጫና ሲፈጥሩ በተደጋጋሚ ይታይ ነበር።

እንደ እንግዳው ቡድን ኢላማቸውን የጠበቁ በርካታ ሙከራዎችን ለማድረግ ያልታደሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 19ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም መስፍን ከማዕዘን ምት በግንባሩ የገጨው ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣ የ27ኛ ደቂቃው የአብዱልከሪም ኒኪማ የርቀት ሙከራም እምብዛም ለግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉኩዋጎ ፈታኝ  አልነበረም። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለቱ መስመሮች የሚከፍቱትን ጥቃት አማካይ መስመራቸውን በአንድነት በሜዳው ስፋት ወደ ግራ እና ቀኝ በማጠጋጋት በአግባቡ መመከት የቻሉት ኬሲሲዎች በሜዳው ቁመት ግን በተከላካይ እና አማካይ መስመራቸው መሀል ክፍተቶችን ሲተው ተስተውለዋል። ሆኖም ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ጋዲሳ መብራቴ እና አብዱልከሪም ኒኪማ አልፎ አልፎ በቦታው በመገኘት ኳስ ሲቀበሉ ቢታዩም ጥቃቱን በአግባቡ አስቀጥለው የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሙሉአለም መስፍንን በታደለ መንገሻ ቀይረው ያስወጡት አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ የተጋጣሚያቸውን ክፍተት ለመጠቀም በቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ ድንቅ አማካይ የቴክኒክ ብቃት ቡድናቸውን መገዝ ያሰቡ ይመስላሉ። ሆኖም ጊዮርጊሶች 49ኛው እና 60ኛው ደቂቃ ላይ በጋዲሳ መብራቴ ከርቀት ካደረጓቸው ሙከራዎች ሌላ ወደ ግብ የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። ከሁሉም በላይ ግን 59ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ እንዲሁም 77ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ አሰፋ ያሻማውን ሳላዲን ሰይድ በግንባራቸው ሳይጠቀሙበት የቀሩባቸው አጋጣሚዎች የሚያስቆጩ ነበሩ። የሳላዲን እና በሀይሉን መግባት ተከትሎ ወደ መስመር የወጣው አማራ ማሌ በመሀል አጥቂነት ከተጫወተበት የመጀመሪያው አጋማሽ የወረደ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ሙሉ ቡድኑም ግብ በማግኘት ጉጉት ውስጥ ሆኖ በተደጋጋሚ ከቅርፁ ሲወጣ ይታይ ነበር። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥርም ቅዱስ ጊዮርጊስ በረዥሙ በሚጣሉ ኳሶች ላይ የተመረኮዘ ሆኖ ታይቷል። ቢሆንም ግን የኬሲሲኤ ተከላካዮች ተሻጋሪ እና ቀጥተኛ ኳሶችን ከግብ ክልላቸው በማራቁ በኩል እምብዛም አልተቸገሩም።

በሁለተኛውም አጋማሽ የተሻሉ ሙከራዎችን ያደረጉት ኬሲሲኤዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በአማካዩ ሙታያባ ሙማሚሩ  ከርቀት ያደረጉት ሙከራ በሮበርት ተመልሷል። እንግዶቹ በእጅጉ ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚ የተፈጠረው ግን የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኪዛ ሙስጠፋ ከረዥም ርቀት ያሻማውን ቅጣት ምት  ዴሪክ ንሲምባቢ በግንባሩ ሞክሮ የግብ አግዳሚው ሲያወጣበት ነበር። ኬሲሲኤዎች ወሳኝ አጥቂያቸው ሻባን መሀመድን ቀይረው ካስገቡ በኃላ የተጨዋቹን ፍጥነት ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይቷል። ይህ ተጨዋች ተቀይሮ ከገባ በኃላ ቢጫ ካርድ የተመለከተው አስቻለው ታመነም ጨዋታው ሊገባደድ አቅራቢያ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲሰራ ቢታይም የቀይ ካርድ ሰለባ ሳይሆን መቅረቱ ለፈረሰኞቹ ትልቅ ዕድል ነበር። በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ያገኟቸውን የቆሙ ኳሶች በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉት የዩጋንዳ ሊግ ሻምፒዮኖቹ ግብ ባያስቆጥሩም ከሜዳቸው ውጪ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግበው ጨዋታውን አገባደዋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *