የሶከር ኢትዮጵያ የጥር – የካቲት ወር ምርጦች 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር አመት የመጀመሪያ ምዕራፍ ነገ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ይጠናቀቃል። ሶከር ኢትዮጵያም በአንደኛው ዙር የመጨረሻዎቹ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎች እና የተስተካካይ መርሀ ግብሮች የተስተናገዱባቸውን የጥር እና የካቲት ወራትን ማዕከል በማድረግ ምርጦቿን በዚህ መልኩ ይፋ አድርጋለች።

​የወሩ ኮከብ ተጨዋች – ከንዓን ማርክነህ

በግል ክህሎት የበለፀጉ ተጨዋቾች ችግር የሌለበት አዳማ ከተማ ያለፉትን ሁለት ወራት መልካም የሚባል ውጤት እያስመዘገበ ሲዘልቅ መሀል ሜዳ ላይ ጎላ ብሎ የሚታየው ከንዓን ማርክነህ ዋና ተዋናይ ነበር። ከንዓን የአማካይ ክፍሉ ዋነኛ መሰረት በመሆን የቡድኑን የኳስ ፍሰት ባለው ተሰጥኦ ከማቀላጠፍ ባለፈ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በሚደርስባቸው አጋጣሚዎች የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ግቦችን በማስቆጠር የመጀመሪያውን ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች በስኬት አገባዷል። ከንዓን በአምስቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ሁለት ደሞ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ ያሳየው ብቃት እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን ነበር።

የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ – ገብረ መድህን ኃይሌ

ከደብዛዛ ጅማሮ በኃላ በታህሳስ ወር ሶስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ በአስገራሚ ሁኔታ ደረጃውን ያሻሻለው ጅማ አባጅፋር የተጨዋቾቹ የማሸነፍ ስነልቦና ከፍ ያለበትን ጊዜ አሳልፎ ነበር። ሆኖም ወሩ ሲገባደድ በቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰበት የ 3-0 ሽንፈት እና የኦኪኪ አፎላቢ ጉዳት የክለቡን ቀጣይ ጉዛ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር። በጥር እና የካቲት ወር በተደረጉ ቀጣዮቹ አምስት ጨዋታዎች ግን አሰልጣኝ ገብረ መድህን የተጨዋቾች ቦታ ሽግሽግ በምድረግ እና የወሳኙ አጥቂያቸውን ክፍተት በመሙላት እንዲሁም የተጨዋቾችን የአሸናፊነት መንፈስ በመመለስ ዳግም ወደ ውጤታማነት መልሰውታል። በመሆኑም ጅማ አባ ጅፋር  ከቀጣይ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሶስቱን በማሸነፍ እና በሁለቱ ነጥብ በመጋራት ያለሽንፈት ወሮቹን ጨርሶ ከታች በመጣበት አመት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የመጀመሪያውን ዙር እንዲያገባድድ ሆኗል።

የወሩ ምርጥ 11

ግብ ጠባቂ

ፍሊፔ ኦቮኖ (መቐለ ከተማ)

ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው የቀድሞው የኦርላይንዶ ፓይሬትስ ግብ ጠባቂ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር በበርካታ ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት የወጣ ተጨዋች ነው። በተለይ ቡድኑ በጥር እና የካቲት ወር ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ተቆጥረውበት በአራቱ መረቡን ሳይሰደፍር መውጣት መቻሉ በምርጫው ውስጥ እንዲካተት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

ሌሎች ምርጥ አቋም ያሳዩ ግብ ጠባቂዎች፡ ዳንኤል አጃዬ (ጅማ አባ ጅፋር) ፣ ጃኮ ፔንዜ (አዳማ ከተማ) ፣ ወንድወሰን ገረመው (ወላይታ ድቻ)

ተከላካዮች

ኄኖክ አዱኛ (ጅማ አባ ጅፋር)

በአሁኑ ወቅት በሊጋችን የሚገኝ ቁጥር አንድ የመስመር ተከላካይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኄኖክ ከመከላከል ሃላፊነቱ በተጨማሪ በማጥቃት ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ እጅግ የጎላ ነው። በዚህም ሁለቱን ወራት አንድም ሽንፈት ሳይገጥመው ባጠናቀቀው ጅማ አባ ጅፋር ውስጥ የነበረውን ከፍተኛ ሃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በቦታው ተመራጭ አድርገነዋል።

መሣይ ጳውሎስ (ሀዋሳ ከተማ)

ብስለትን በሚጠይቀው የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ እያንፀባረቀ የመጣው መሣይ ገና በለጋ እድሜው በቦታው ከተለያዩ ተጨዋቾች ጋር በመጣመር ቡድኑን በቋሚነት በማገልገል ላይ ይገኛል። ሃዋሳ ከተማ በጥር እና የካቲት ወር አንድ ሽንፈት ብቻ አስተናግዶ ደረጃውን ሲያሻሽል እንደ ኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በከፍተኛ የተቃራኒ ደጋፊ ፊት በታዳጊ እድሜው በእርጋታ ቡድኑን በመምራት የብዙዎች አይን ማረፊያ መሆን ችሏል።

ምኞት ደበበ (አዳማ ከተማ)

ባለፉት ወራት በሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ኮከቦች ምርጫ በተደጋጋሚ በተጠባባቂነት ሲያዝ የቆየው ምኞት አሁን የመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት አቋሙ የመጀመሪያ ተመራጭ አድርጎታል። በእነዚህ ጊዜያት አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠመው አዳማ ከተማ በተከላካይ ክፍሉ ጉዳት ሲደራረብበት ከሙጂብ ቃሲም ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ሱሊማን ሰሚድ ጋር በተለያዩ ጨዋታዎች በመጣመር ግዙፉ የመሀል ተከላካይ ምኞት ደበበ ድንቅ ሆኖ መሰንበት ችሏል።

አንተነህ ገብረ ክርስቶስ (መቐለ ከተማ)

መቐለ ከተማ ክስተት ሆኖ ብቅ ያለበትን የውድድር አመት እያሳለፈ ሲገኝ እንደ አንተነህ አይነት ልምድ ያለው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ያስፈልገው ነበር። የቡድኑ ውጤታማነት ከፍ ብሎ በታየባቸው ሁለቱ ወራት እምብዛም በማጥቃቱ ላይ ሲሳተፍ የማይታየው የግራ መስመር ተከላካዩ የቀድሞው የንግድ ባንክ ተጨዋች በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ለኃላ መስመር ጥንካሬው ትልቅ አስተዋፅኦን ከማበርከቱ ባለፈ በወልድያው ጨዋታ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠር መቐለዎች ሶስት ነጥብ እንዲያሳኩ አድርጓል።

ሌሎች ምርጥ አቋም ያሳዩ ተከላካዮች ፡  ፍቃዱ ደነቀ (መቐለ ከተማ) ፣ እሸቱ መና (ወላይታ ድቻ) ፣ ሚካኤል አናን (ሲዳማ ቡና) ፣ አዲስአለም ተስፋዬ (ሀዋሳ ከተማ)

አማካዮች

ኢስማኤል ሳንጋሪ (አዳማ ከተማ)

የታላቁ የኮትዲቫር ክለብ አሴክ ሚሞሳ ውጤት የሆነው የተከላካይ አማካዩ አዳማ ከተማን ከተቀላቀለበት የውድድሩ አመት መጀመሪያ ጀምሮ በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል። ብዙም አካላዊ ፍልሚያዎች ላይ ሳይሳተፍ ኳስ የሚነጥቀው ኢስማኤል በተለይ በሁለቱ ወራት እንደ ኢትዮጵያዊ ተጨዋች ሆኖ ቡድኑን በሜዳ ላይ በመምራት እና ለተከላካይ መስመሩ በቂ ሽፋን የመስጠት ሃላፊነቱን በሚገባ በመወጣት ከፊቱ ያሉ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ተጨዋቾች ምቾት ተሰምቷቸው በነፃነት በማጥቃቱ ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል።

የአብስራ ተስፋዬ (ደደቢት)

ደደቢት ተከታታይ ጨዋታዎችን ካሸነፈበት የታህሳስ ወር በኃላ መሪነቱን ባይነጠቅም በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የስኬት ፍጥነቱ ቀንሷል። ሆኖም የቡድኑ የመሀል ሜዳ ፈርጥ ታዳጊው የአብስራ አሁንም በድንቅ አቋሙ ገፍቶበታል። በሁሉም ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በመካተትም ቦታውን ማስከበሩን ያሳየበትን ሁለት ወራት አሳልፏል። ለጌታነህ ከበደ ጎል አመቻችቶ ካቀለበት የወልዋሎው ጨዋታ እስከ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ዝናባማ ፍልሚያ ድረስ የየአብስራ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ሚዛናዊነት ያልተለየው እና ታክቲካዊ ብስለቱንም ጭምር በሚገባ ያሳየ ነበር።

ከንዓን ማርክነህ (አዳማ ከተማ)

ቁመተ መለሎው የአጥቂ አማካይ አዲስ አበባ ከተማን ከለቀቀ በኃላ በአዳማ ለመደላደል ጊዜ ቢፈጅበትም በጥር እና የካቲት በተደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ግን በሊጉ ከሱ በላይ ጎልቶ የወጣ ተጨዋች ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥም ከፊት አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ጋር የፈጠረው አስገራሚ ጥምረት ለተጋጣሚ ቡድኖች ስጋት ሆኖ ሰንብቷል። በጥር እና የካቲት ወር በተደረጉ ጨዋታዎች ራሱ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች እና በፈጠራቸው የመጨረሻ አጋጣሚዎች የተቆጠሩት ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ግቦች የወሩን ስኬቱን ከፍ አድርገውታል።

ዮናስ ገረመው (ጅማ አባ ጅፋር)

ጅማ አባ ጅፋር ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ካሸነፈው የሊጉ መሪ ጋር ሲገናኝ ማንም ጨዋታው ቀላል ይሆንለታል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ሆኖም ቡድኑ ጨዋታውን ያሸነፈበትን ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረው ዮናስ ኮከብ ሆኖ በማርፈድ ጅማን ባለድል አድርጓል። ዮናስ በቀጣይ ጨዋታዎችም የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ በማገልገል በሚቆጠሩ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆኑ ገፍቶበታል። ጅማ አባጅፋር 11 ነጥቦችን በሰበሰበባቸው አምስቱ ጨዋታዎችም የአጥቂ አማካዩ ከፍተኛ አገልግሎት ከስኬቱ ሚስጥሮች አንዱ ነበር።

ሌሎች ምርጥ አቋም ያሳዩ አማካዮች ፡ አብዱልሰመድ ዓሊ (ወላይታ ድቻ) ፣ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ) ፣  አሚኑ ነስሩ (ጅማ አባ ጅፋር) ፣ በረከት ደስታ (አዳማ ከተማ) ፣ ሙሉአለም ረጋሳ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ኤፍሬም አሻሞ (ደደቢት) ፣ ተክሉ ታፈሰ (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)

አጥቂዎች

ዳዋ ሆቴሳ (አዳማ ከተማ)

የፊት መስመሩ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳቶች እየገጠሙት ግብ ማስቆጠር ፈተና ሆኖበት ለቆየው አዳማ ከተማ ባለፉት ሁለት ወራት መልስ የሰጠው የዳዋ ሆቴሳ አስደናቂ ብቃት ነበር። በአምስቱ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ዳዋ ሆቴሳ ከኳስ ውጪ ባለው እንቅስቃሴም የአዳማ ከተማ የፊት መስመር እጅግ አስፈሪ እንዲሆን አድርጓል። በጣሙን እየተሻሻለ በመጣው የተጨዋቹ የቅጣት ምት ክህሎት ምክንያትም በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ዙሪያ በአዳማ ተጨዋቾች ላይ ጥፋት በተሰራ ቁጥር ተጋጣሚን የሚያስጨንቅ እየሆነ መጥቷል።

አማኑኤል ገ/ሚካኤል (መቐለ ከተማ)

አማኑኤል በቀኝ መስመር አማካይነት እና በፊት አጥቂነት መቐለ ከተማን እያገለገለ ይገኛል። ሆኖም ሁለቱም ቦታዎች ላይ ሆኖ የሚያሳየው እንቅስቃሴ ከታታሪነቱ እና ከፍጥነቱ ጋር ተዳምሮ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት መቋጫ እንዲሆን አስችሎታል። የአምናው የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ተጨዋች በኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ሁለት ግቦችን ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ለጋናዊው አጥቂ ጋይሳ አፖንግ መሻሻልም የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው።

ሌሎች ምርጥ አቋም ያሳዩ አጥቂዎች ፡ አንዷለም ንጉሴ (ወልዲያ) ፣ ተመስገን ካስትሮ (አርባምንጭ ከተማ) ፣ ምንይሉ ወንድሙ (መከላከያ) ፣ ዳግም በቀለ (ወላይታ ድቻ) ፣ አትራም ኩዋሜ (ድሬደዋ ከተማ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *