የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ዘመን አጋማሽ ግምገማ ዛሬ ተካሂዷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ውድድር ዘመን አጋማሽ ሪፖርት እና ግምገማ ዛሬ በጁፒትር ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በተደረገው ግምገማ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ በስተቀር ሁሉም የሊጉ ክለቦች ተሳትፈዋል፡፡

በግምገማው ላይ እንደቀደምት አመታት ሁሉ ክለቦች የዳኝነት እና የፀጥታ ችግሮችን ያነሱ ሲሆን በጨዋታ ዳኞችን እና ታዛቢዎች ድክመት ላይ ሰፋ ያለ ግዜ ወስደው ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ተመልክተናል፡፡ ግምገማው እግርኳሱን ሊያሳድጉ የሚችሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ያልቀረበት መሆኑንም ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡ ፌድሬሽኑ በበኩሉ አንዳንድ የተነሱትን ችግሮች በማረም ለሁለተኛው የውድድር አጋማሽ እንደሚቀርብ ገልፆ ክለቦች እራሳቸው እንዲፈትሹ እና እንዲመረምሩ ከመግለፅ አልተቆጠበም፡፡ በዳኝነት ምደባ ዙሪያም ክለቦች ያላቸውን ቅራኔ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሊግ ኮሚቴው ከዳኞች ኮሚቴ ጋር በጋር ተባብሮ በመስራት የዳኞችን ምደባ በጥንቃቄ እንደሚያከናውን ቃል ገብቷል፡፡

የፕሪምየር ሊጉ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት መጨረሻ እንዲጀመሩ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም እንደወላይታ ድቻ፣ ወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር ያሉ ክለቦች ካለው ወቅታዊ ሁኔታ እና የጨዋታ መደራረብ አንፃር ሊጉ እንዲራዘመው በጠየቁት መሰረት በአንድ ሳምንት ተሸጋግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዋንጫ እጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ከተካሄደ በኃላም ግምገማው ተጠናቋል፡፡

(ስለ ጥሎ ማለፉ ከቆይታ በኋላ ይዘን እንቀርባለን)

Leave a Reply