መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገበት የኢትዮጵያ ዋንጫ ድልድል ዛሬ ተከናውኗል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ የውድድር ዘመን አጋማሽ ግምገማ እና ሪፖርት በዛሬው እለት በጀፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ሲከናወን የኢትዮጵያ ዋንጫ እጣ ማውጣትም ተከናውኗል፡፡ ለአመታት ለውጦች አንዲያስተናግድ ሲጠበቅበት ባለበት ሲቀጥል የቆየው ውድድሩ ዘንድሮም በመጠነኛ ማሻሻያ እንዲቀጥል ተወስኗል።

የእጣ ማውጣት ስነስርዓቱ ከመካሄዱ በፊት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኢ/ር ጌታቸው የማነብርሃን ውድድሩ  ከሌላው ጊዜ በተለየ ፎርማት እንዲካሄድ የተለያዩ አማራጮችን ለክለብ ተወካዮች አቅርበዋል፡፡  የመጀመርያው ክለቦቹ በያሉበት ክልል እርሰስ በእርስ ጨዋታ አድርገው አሸናፊ ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜ እንዲሸጋገሩ እና በሚወጣው እጣ መሰረት ጨዋታ እንዲያደርጉ የቀረበ ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባ እና ደቡብ ሁለት ቡድን ሲያሳልፉ ከቀሪዎቹ ( ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ድሬዳዋ) አንድ አንድ ቡድን እንዲያሳልፉ የታቀደ ነበር፡፡ ሌላው የተሳው ሀሳብ ከመጀመርያው በሚመሳሰል መልኩ በየክልላቸው ጨዋታ አድርገው ከእያንዳንዳንዱ አንድ ክለብ እንዲያልፍ ፤ ከሚያልፉት 6 ክለቦች መካከል የአአ እና ደቡብ ክለቦች በርካታ ጨዋታ የሚጫወቱ በመሆናቸው በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ሲያልፉ ሌሎቹ እርስ በእርስ ተጫውተው አሸናፊዎቹ ወደ ግማሽ ፍፃሜ እንዲያልፉ የቀረበ ነበር፡፡

ሆኖም ሀሳቦቹ በአመዛኞቹ ክለቦች ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡ ይልቁንም በቀደመው አካሄድ መሠረት ውድድሩ የሚቀጥል ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉበት አሰራር ግን የሚቀር ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት በእጣ ቀዳሚ የሚሆነው ቡድን በሜዳው ጨዋታውን ሲያደርግ ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በመለያ ምቶች አላፊው የሚለይ ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ከተካሄዱ በኋላ የሚያልፉ ቡድኖች የቀደመ ጨዋታቸውን (መጀመርያው ዙር) በሜዳቸው ካደረጉ በተቃራኒው ከሜዳቸው ውጪ እንዲያደርጉ ፣ ከሜዳቸው ውጪ ካደረገዉ ደግሞ በሜዳቸው እንዲያከናውኑ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ሁለቱም ተጋጣሚዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ከሆኑ ግን በእጣ የሚለይ ይሆናል፡፡

ውድድሩ ዘንድሮም በፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተገድቦ ይካሄዳል

የየሀገራቱ እግርኳስ ማህበራት ዋንጫዎች (ጥሎ ማለፍ ውድድሮች) በሊግ ውድድር ከሚሳተፉ ቡድኖች አልፎ ከሊግ ውጪ የሚገኙ ክለቦችን ያሳትፋል፡፡ እንደ እንግሊዝ እና የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበሩ የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ ከዋናው የጥሎ ማለፍ ውድድር በተጨማሪ በሊግ ክለቦች ብቻ የተገደቡ ውድድሮችን ያካሂዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ከሚሌንየሙ ወዲህ የኢትዮጵያ ዋንጫ በፕሪምየር ሊጉ ክቦች የተገደበ ሲሆን በጥቂት አጋጣሚዎች ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ውጪ የሚገኙ ጥቂት ክለቦች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ውድድር በፕሪምየር ሊግ ክለቦች ብቻ መገደቡ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሱበት ቢያደርግም ለውጦች ግን አልታዩበትም፡፡

በዛሬው የግምገማ መድረክ ኢ/ር ጌታቸው ከፕሪምየር ሊጉ ውጪ የሚገኙ ክለቦች በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቢቀርብም የአዎንታ ምላሾች ባለመገኘታቸው በፕሪምየር ሊግ ክለቦች ብቻ እንዲከናወን እንደተደረገ ቢገልፁም ፌዴሬሽኑ አስገዳጅ ሁኔታ ከማስቀመጥ ይልቅ ክለቦች ውድድሩ ላይ እንደማይሳተፉ በመግለፃቸው ብቻ ምላሻቸውን ተቀብሎ በሊጉ ክቦች ብቻ እንዲከናው መወሰኑ አስገራሚ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *