ብቸኛው የአፋር ክለብ የመፍረስ አደጋ ውስጥ ገብቷል

በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት ከሚደረጉ ውድድሮች በሦስተኛ እርከን የሚገኘው የኢትዮዽያ 1ኛ ሊግ ውድድር ከ50 በላይ ክለቦችን በመያዝ ባልተሟላ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል። በዚህ ውድድር ላይ በምድብ ለ የሚገኘው የአፈሩ የከዳባ እግርኳስ ክለብ እስካሁን 6 ጨዋታዎችን በማድረግ በ4 ጨዋታ የአቻ በ1 ጨዋታ ደግሞ ሽንፈት በማስተናገድ በ1 ጨዋታ ደግሞ ፎርፌ ተሰጥቶበት 4 ነጥብ በመያዝ እየወዳደረ ይገኛል። በዚህ ሁኔታ ክለቡ ባጋጣመው ከፍተኛ የፋይናስ ችግር ምክንያት ያለፈውን አንድ ወር ከማንኛውም ውድድር የራቀ ሲሆን በአሁኑ ሰአት የመፍረስ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ኤፍሬም ሰይድ ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል። አሰልጣኝ ኤፍሬም ስለ ክለቡ አመሰራረት እና ዘንድሮ ስላለበት ሁኔታ ጠቅለል አድርገው ገልፀዋል፡፡

 

ስለ ክለቡ አመሰራረት

ባለፈው ወቅት እዚህ አፋር ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እና ሌሎች የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ወደዚህ በመጡበት ወቅት እንዴት ይህን የሚያህል ግዙፍ ስታድየም ተገንብቶ አንድ በኢትዮዽያ ሊግ ውድድሮች የሚጫወት ክለብ አይኖርም። እኛ በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ እናግዛችኋለን በማለት ከ17 አመት በታች የአፋር ቡድን ውስጥ የሚገኙ 13 ተጨዋቾችን ከአጎራባች ክልል 12 ተጨዋቾችን በማሰባሰብ በአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ከአፋር ወጣቶች ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ክለቡን ተመሰረተ። ጊዚያዊ ቦርድ ተቋቁሞ የክለቡ ገቢ ምንጭ በመሆን አፋር ውሃ ስራዎች እና ከአፋር ዲዛይን እና ቁጥጥር ተቋም ድጋፍ ይደረግለት ነበር።

 

ክለቡ ተቋቁሞ ውድድር ከጀመረ በኋላ ከውድድር የራቀበት ምክንያት

 

በአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ወጣቶች ሚኒስቴር እንዲሁም በሁለቱ ተቋማት ድጋፍ እስከመቼ ይቀጥላል። በማለት የከዳባ ተብሎ ለሚጠራ ጨው አቅራቢ አክስዮን ማህበር በመነጋገር አክስዮን ማህበሩ በአመታዊ ስብሰባው ላይ ክለቡን እንደሚረከቡ አስፈላጊውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሁሉም የአክሲዮን ባለድርሻ አካለት በሙሉ ድምፅ ተስማምተው ክለቡን በባለቤትነት ተረክበዋል።  ለክለቡም የሚያስፈልገው በጀት ካፀደቁ በኋላ ወደ አፈፃፀሙ ለመግባት ሲገባ የባለቤትነት ስሜት በጎደለው መልኩ ከስፖርት ፍላጎት ማጣት የተነሳ የአክሲዮኑ ባለቤቶች ‹‹ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ፈርሷል ይህንንም ክለብ እናፍርሰው። ›› በማለት ይሄው ውድድር ካቆመ ሁለት ወር ሆኖታል፡፡ ለተጨዋቾች ደሞዝም ሆነ ድጋፍ ማድረግ አቁመዋል። ብዙ ማደግ ስለምንፈልግ በእግርኳሱ ችግሮች ሊኖሩ ይችላል ብለን ይሄው እስከ ዛሬ በትዕግስት እየጠበቅን እንገኛለን ።

 

የአፋር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እና እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ስሚያደርጉት እገዛ 

 

እውነት ለመናገር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከጎናችን አሉ። አሁንም በሚቻላቸው መጠን ቡድኑ ወደ ውድድር እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ። የፌዴፌሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆነው አሊሚራህ መሐመድም እንዲሁ ክለቡ ወደ ውድድር እንዲገባ የሚመለከታቸውን አካላት እያነጋገረ ቢገኝም በአክሲዮን ማህበሩ አመራሮች ቸልተኝነት እና የስፖርት ፍላጎት ማጣት ይህ ችግራችን ሊስተካከልልን አልቻለም።

 

በቀጣይ…

 

አፋር በመላው ኢትዮዽያ ላይ ሁለት ተከታታይ አመት አምና እና ካቻምና  ከ15 እና ከ17 አመት በታች ቡድኑ አሸናፊ መሆን ችሏል። ለምድነው እነዚህን ታዳጊዎች በክለብ ደረጃ ተይዘው መዝለቅ የማይቻለው ።  በጣም ብዙ እግርኳሱን ሊደግፉ የሚችሉ ፋብሪካዎች እና ድርጅቶች አሉ ።  እነዚህን አስተባብሮ ቡድኑን መታደግ ያስፈልጋል ። ብዙ መጫወት የሚችሉ አቅም ያላቸው ተጨዋቾ ያሉበት በመሆኑ እንደ ጀማሪነታችን የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የ1ኛ ሊግ የውድድር እና ስነስርአት ኮሚቴ ክለቡን ለማፍረስ ከመጣደፍ እንዲያውም እጃቸውን በማስገባት አመራሮችን በማነጋገር ክለቡ የሚቀጥልበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው።

 

እንደ አፋርባሉ እግርኳስ እምብዛም ባልተስፋፋባቸው ክልሎች የክለቦች ህልው በቶሎ ሲከስም ይስተዋላል፡፡ አምና በአንደኛሊግ ለመወዳደር ተመዝግቦ የነበረው ሰመራ ከተማ ውድድር ሳይጀምር የፈረሰ ሲሆን በኢትዮ ሶማሌ ክልል የሚገኙት ካሊ ጅግጅጋ እና ኢትዮ ሶማሌ ልዩ ፖሊስ ፣ በጋምቤላ ዩኒቲ ጋምቤላ እና ጋምቤላ ከተማ አምና በአንደኛ ሊግ የነበሩ ዘንድሮ ያልተመዘገቡ ቡድኖች ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *