ሶከር ታክቲክ | ፎርሜሽን

ሶከር-ታክቲክ ከዘመናዊ እግርኳስ መሰረታዊያን የሚመደበው እና ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት በእግርኳሱ አለም ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው ታክቲክን የምናስተናግድበት አምድ ነው። በዚህ አምድ የመጀመርያ በሆነው ክፍል ስር የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን (ፎርሜሽን) በጥልቀት እናቀርባለን።

1)የእግርኳስ ፎርሜሽኖች ምንነት

ፎርሜሽኖች በጨዋታ ወቅት ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚኖራቸውን እንቅስቃሴያዊ የቦታ አያያዝ ያሳያሉ፡፡ አሰልጣኞች ተጫዋቾቻቸው በተደራጀ መንገድ ስፍራቸውን እንዲጠብቁና በሜዳው የተለያዩ ክፍሎች የሚኖራቸውን ሚና በጥሩ ሁኔታ እንዲያውቁ የሚያደርጉበት እቅድ-ተኮር ምስሎች ናቸው፡፡ በእግርኳስ፦ ፎርሜሽኖች የተለያየ መልክ የሚያሳዩ እንዲሁም በማጥቃትና መከላከል ሒደት ውስጥ ተቀያያሪ ቅርጽን የሚያመለክቱ አደራደሮች ሆነው ይገኛሉ፡፡
በዘመናዊ እግርኳስ ተጫዋቾች በአንድ የሜዳ ክፍል ውስጥ እንዲንቀሳቀሱና የተወሰነ ተግባር ብቻ እንዲከውኑ አይጠበቅባቸውም፡፡ ይህ ጥብቅ የተጫዋቾች የሜዳ ውስጥ አደራደርን የሚመለከተው (Rigid Formation) ስርዓት በእንቅስቃሴያዊ የቦታ አያያዝና አጠባበቅ (Fluid Positioning ) እየተተካ ተጫዋቾች ከአንድ በላይ በሆነ የጨዋታ ምልልሳዊ ሒደት (cyclical process) ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው፡፡

ፎርሜሽኖች ሜዳ ላይ በሚገኙት ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪ መሰረት ሊለዋወጡ እና ከተጫዋቾቹ ጋር እንዲስማሙ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌም በ4-4-2 ከሁለቱ አጥቂዎች አንዱ ወደ ኋላ አፈግፍጎ የአማካይ ክፍሉን ቢቀላቀል መነሻ ቅርጹ ወደ 4-5-1 ይለወጣል፡፡ ከ4-3-3ም አንደኛው አማካይ(በተለይም ከሁለቱ የ”8″ ቁጥር ሚና ካላቸው ተጫዋቾች/shuttlers/ አንዱ) በሜዳው ስፋት ከሁለቱ የመስመር አጥቂዎች መሀል ተገኝቶ ብቸኛው የመሀል አጥቂ በሜዳው ቁመት ትንሽ ርቀት ወደ ፊት ቢጠጋ 4-2-3-1ን እናገኛለን፡፡ በ4-2-3-1 እና በ4-2-1-3 መካከል ያለውን ልዩነትም እንዲሁ ብናይ በ4-2-3-1 ቅርጽ ከአጥቂው ጀርባ ካሉት ሶስት የማጥቃት አማካዮች የመሀለኛው ጥቂት ወደ ኋላ ቢመለስና ሁለቱ የመስመር የማጥቃት አማካዮች ወደ ፊት ቢጠጉ 4-2-1-3ን ይሰጠናል፡፡

እንደሚታወቀው የመስመር አማካዮችም ሆኑ የመስመር አጥቂዎች የተጋጣሚዎቻቸው መስመር ተከላካዮች ስጋት በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ በሜዳው ቁመት ያለው ቦታቸው መደበኛና በተደጋጋሚ የማይቀያየር ሆኖ የሚገኝበት እድል ሰፊ በመሆኑ ተጫዋቾቹ በፎርሜሽኖች ቅርጽ አጠባበቅ ላይ የሚኖራቸው ተለምዷዊነት (Regularity) ከሌሎች ሚና-ተግባሪ ተጫዋቾች የበለጠ ነው፡፡

2)ፎርሜሽኖችና አነባበባቸው

አንድ ቡድን የሚጫወትበትን ወይም አዘወትሮ የሚጠቀምበትን የፎርሜሽን አይነት በጥልቀት አጢኖ ለመረዳት የተጫዋቾቹን የአጨዋወት ባህሪና መደበኛ የመጫወቻ ቦታ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

የፎርሜሽን መልክን የሚወክሉ አደራደሮች የሚፃፉት የሜዳውን ቁመት በመጠቀም ከተከላካይ መስመር ጀምሮ ያሉት ተጫዋቾች በሜዳው ወርድ ከቀኝ ወደ ግራ ወይም ከግራ ወደ ቀኝ በሚንቀሳቀሱበት መስመር መሰረት ነው፡፡በሜዳው ቁመት የሚገኙ የስፋት መስመሮች (Horizontal Lines) ፎርሜሽኖች ምን ያህል የጎንዮሽ መስመር (Band) ብዛት እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም ባለሶስት መደብ የሆኑትና እንደ 4-4-2፣4-3-3፣3-5-2፣3-4-3፣……የመሳሰሉት እንዲሁም ባለ አራት መደብ የሆኑትና እንደ 4-4-1-1፣4-1-3-2፣ 4-2-2-2፣4-2-3-1፣3-3-1-3 የመሳሰሉት የአግድሞሽ ድርድሮችን /ላልቶ ይነበብ/ ቁጥር ይገልጻሉ፡፡ በስፋት መስመሮቹ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ተጫዋቾች መጠን ደግሞ በእያንዳንዱ የመጫወቻ ክፍሎች ተሳታፊ የሆኑ ተጫዋቾችን የሚና አይነት (Roles) ያሳየናል፡፡ ብዙውን ጊዜ የፎርሜሽኖች መሰረታዊ የመነሻ ቅርጽ ማሳያዎች የመሀል ተከላካዮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ይህም ተጫዋቾቹ በጨዋታው ተሳትፎ የሚያደርጉበት የጨዋታ ሒደት ከሌሎቹ ተጫዋቾች አንፃር አነስተኛ በመሆኑ የመጣ ነው፡፡እንደሚታወቀው የመሀል ተከላካዮች በመደበኛነት አመዛኙን ጊዜ ይበልጥ በመከላከሉ ላይ ስለሚሰሩ በቦታቸው ላይ በቋሚነት መገኘታቸው የፎርሜሽኖችን የንባብ ጅማሮ እነርሱን መሰረት ያደረገ እንዲሆን አስችሏል፡፡

በተሻለ ደረጃ የቡድኖች መነሻ አደራደሮችን ለመገንዘብ በጨዋታ የመከላከል ሒደት (Defending-Phase) ተጫዋቾች በእንቅስቃሴ ላይ የሚኖራቸውን አንፃራዊ መገኛ (Relative Positioning) በትኩረት መመልከት ይገባል፡፡ አነባበባቸውን በተመለከተም ብዙውን ጊዜ አሻሚ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ይከሰታሉ፡፡ በተለይም ተጫዋቾች በተለያዩ የጨዋታ ሒደቶች (Phases of Play) ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ሁኔታ የቡድኖችን ጠቅላይና ወካይ-ቅርጽ በቀላሉ ለመለየት እንዳይቻል ያደርጋል፡፡በሜዳው ቁመት በተጫዋቾች መካከል የሚኖረውን ርቀት አስመልክቶ ሁሉን አስማሚ መመዘኛ መስፈርት (Standard) ባለመኖሩም 4-4-2 የ4-4-1-1ን ቅርጽን እንዲይዝ ከሁለቱ አጥቂዎች አንደኛው ወደ ኋላ ምን ያህል ርቀት ማፈግፈግ ይኖርበታል? 4-4-1-1 ወደ 4-2-3-1 እንዲቀየርስ የመስመር አማካዮቹ ከነበሩበት አንፃራዊ የመነሻ ቦታ ወደ ፊት ምን ያህል መጠጋት ይጠበቅባቸዋል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ተገቢም አጥጋቢም ምላሽ ሳያገኙ ይታለፋሉ፡፡

የፎርሜሽኖችን ስያሜዎች ስናነሳም ለምሳሌ 4-1-3-2 ስንል ቅርጹ ያለውን የመነሻ ምልክት ለማስቀመጥ እንጂ በጨዋታው ሙሉ የእንቅስቃሴ ቅይይሮች የሚኖረውን መልክ አለመወከሉን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ በምስል-ከሳች መሳሪያዎች (በቪዲዮ) የምንመለከተውን ጨዋታ የተወሰነ ሰዓት ላይ አቁመን ሜዳ ውስጥ የሚታየውን የተጫዋችቾ እንቅስቃሴያዊ ቦታ አያያዝ ብንቃኝ 4-1-3-2 የነበረው መነሻ ፎርሜሽን 3-2-3-1-1፣3-1-5-1፣5-1-2-2፣4-4-1-1……….ሆኖ ልናገኘው እንችላለን፡፡ ይህ ሲባል የመነሻ ቅርፁን ስያሜ 4-1-2-3 ማለታችን በተለያየ አሰያየም የሚታዩትን የሚዋልሉ ግርድፍ አደራደሮችን ጠቅልለን የምንወክልበትን መደበኛ ወይም ተለምዷዊ የተሻለ መንገድ አገኘን ማለት ይሆናል፡፡

4-1-3-2ን ወይም 4-2-1-3ን እንደ 4-2-1-2-1 ለማንበብ መሞከር ደግሞ ቀላል ቁጥራዊ ምልክትን በመስጠት የተለመደውን መንገድ ስቶ ወደ ባለ-አምስት ረድፍ (5th-Band) ውስብስብ ወደ ሆነ ቅርጽ ያመራናል፡፡

3)ፎርሜሽኖችና የተመዛዛኝነት ወይም የተመጣጣኝነት (Symmetry) ባህሪ

ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ውጪ በተለይም ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት በወረቀትና በተለያዩ የምስል ማስፈሪያ ገጾች ላይ ፎርሜሽኖች በይዘታቸው ተመዛዛኝ አልያም በቅርጽ ተመጣጣኝ (Symmetrical) መስለው ይታያሉ፡፡ ቀድሞ በሚታይ መልካቸው መደበኛ ወይም በወጥነት የተገደቡ ባህሪያትን የሚያሳዩ ሆነውም ይገኛሉ፡፡ ተመልካቾችም በአብዛኛው በበርካታ ምስሎች የሚገለፁትን አደራደሮች የምንረዳው ተጫዋቾች ወጥ የቦታ አያያዝ ተከትለው የሚቆሙበትን መነሻ መዋቅሮች ወስደን ነው፡፡

በመጀመሪያ የኢ-ተመዛዛኝነት (Asymmetry) ፅንሰ-ሐሳብ በአንድ ቡድን የአጨዋወት ባህሪ ላይ በሜዳው በሚገኙ ክፍሎች በተለይም በሁለቱም መስመሮች እኩል የሆነ ጥንካሬና ትኩረት ሳይደረግ ሲቀር የሚነሳ በመሆኑ ፎርሜሽኖች በራሳቸው የሚያመጡት መልክ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡

ቡድኖች በተለያዩ ምክንያቶች የኢ-ተመዛዛኝነት ባህሪያትን ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ በአንደኛው መስመር በሚጫወተው ተጫዋች የተሻለ የግል ብቃት ምክንያት የአጨዋወት አቀራረብን በእርሱ ላይ በመመስረት፣ የተጋጣሚ ቡድንን ደካማና ጠንካራ ጎን በማጤን በዚያ መስመር ላይ በመዘጋጀት እና በሌሎችም ምክንያቶች በእግርኳስ ታክቲክ ውስጥ ኢ-ተመዛዛኝነት (Asymmetry) ቦታ ሲያገኝ እናያለን፡፡ በእርግጥም ተጫዋቾች በሚጫወቱባቸው ቦታዎች ፍሰቱን የጠበቀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲችሉ የቅርጾች ተመዛዛኝ (Symmetrical) መሆን አስፈላጊ አይደለም፡፡ አንዳንድ አሰልጣኞች ይበልጥ ትኩረት የሚሰጡትም ተመጣጣኝ ቅርጹን የጠበቀው የማጥቃት ክፍል ወደ ተጋጣሚ ሜዳ መግባቱን ሳይሆን በሚዛናዊነት የማጥቃት ሒደቱ ከተፈለገበት ግብ መድረሱን ነው፡፡ ኢ-ተመዛዛኝነትን የበለጠ ለመገንዘብም በቀጥታ የመነሻ ፎርሜሽኖችን ከመመልከት ይልቅ በጨዋታ ሒደት ዋነኛ ምዕራፎች የሆኑትን በተለይም የመከላከልና የማጥቃት ሒደት ላይ ተጫዋቾች የሚኖራቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴያዊ የቡድን ቅርጽ፣ የተናጠል የተጫዋቾች ቦታ አጠቃቀም እና አቋቋም ማየት አለብን፡፡ በማጥቃት የጨዋታ ሒደት ግልጽ የሆነ ኢ-ተመዛዛኝ የአጨዋወት ስርአትን በሜዳው ቁመት በሁለቱም መስመሮች በሚሰለፉት የተለያዩ ሚና ተግባሪ ግን ደግሞ በተመሳሳይ የመጫወቻ ክፍል (Department) ውስጥ የሚካተቱ ተጫዋቾች አማካኝነት ልናይ እንችላለን፡፡ ለምሳሌም በግራው መስመር ተለምዶአዊ/መስመሩን ተጠግቶ የበለጠ የሜዳ ስፋትን ጥቅም እያስገኘ የሚጫወት የመስመር አማካይ በሌላኛው የቀኙ መስመር ደግሞ ባለፉት አስር አመታት በይበልጥ እየታወቀ በመጣው የተገለበጠ አማካይ (ተለምዷዊ ባልሆነው መስመር እየተሰለፈ ወደ መሀለኛው የሜዳ ክፍል የሚገባና በተፈጥሮ የግራ እግር ተጫዋች ሆኖ በቀኙ፣ ቀኝ ሆኖም በግራው የሚሰለፍ የአማካይ ተጫዋች/Inverted Winger) ቢሰለፉ ግልጽ ሆኖ የሚታይ የኢ-ተመዛዛኝነትን ምስል ልናስተውል እንችላለን፡፡ ተጫዋቾቹ በመነሻነት የሚጠቀሙት ቦታ የተለያየ ከመሆኑ ባለፈ በጨዋታው ከኳስ ጋርና ያለኳስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ ባልሆነ ቦታው የተሰለፈው አማካይ በማጥቃት እንቅስቃሴ ከመስመር እየተነሳ ወደ ተጋጣሚ ጎል ክልል የመድረስ ተግባርን ሲያሳይ በተለመደው ስፍራው የሚጫወተው አማካይ ደግሞ ወደ መስመር በመጠጋት ለመጫወት የሚያደርገው ዝንባሌ ወይም የአጨዋወት ምርጫ ኢ-ተመዛዛኝነቱን አጉልቶ ለማሳየት ያስችላል።

ከተጫዋቾቹ የሚና አተገባበርና ቦታ አጠባበቅ በተጨማሪ ታክቲካዊ በሆኑ የአጨዋወት መንገዶቸም የኢ-ተመጣጣኝነት ጉዳይ ይነሳል፡፡ ተጋጣሚን ተጭኖ በመጫወት ዘዴ የሚፋለም ቡድንን የመከላከል አደረጃጀት ብንቃኝ በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች በባለጋራ ላይ ግፊት ወይም ጫናን በማሳደር ለመጫወት ከፍተኛ ውህደት ማስፈለጉ እሙን ነው፡፡ ይህ ውህደት ደግሞ በሜዳው ስፋትም ይሁን ርዝመት ተጫዋቾች በሚኖራቸው የቦታ፣ የቁጥርና የቅርጽ ተመጣጣኝነት አንፃር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ይህም የኢ-ተመዛዛኝነት ሐሳብ ለበርካታ የአቀራረብ አማራጮች አመቺ መሆኑን ያመላክታል፡፡ በመሰረታዊነት ኢ-ተመዛዛኝ ቅርጽ ኖሯቸው የሚፈጠሩ ፎርሜሽኖች ባይኖሩም የአሰልጣኞች ፍልስፍና፣ የተጫዋቾች አጨዋወት ስልትና የሚና አተገባበር፣ በጨዋታ ወቅት የሚታዩ ታክቲካዊ ማሻሻያዎችና ሌሎች በርካታ ነገሮች በፎርሜሽኖች ውስጥ ኢ-ተመዛዛኝነትን ያመጣሉ፡፡ በመነሻነት በምስል ራስን ያለመድገም ባህሪን (Asymmetry) የሚያሳዩ ፎርሜሽኖችም አሉ፤ በተለይ ሁለት የፊት መስመር ተሰላፊዎችን የሚጠቀሙት፡፡ አንደኛው ወደ ፊት ተጠግቶ ሌላኛው ደግሞ በመጠነኛ የኋላ ርቀት አፍግፍጎ የተደራቢ አጥቂነት ወይም የአጥቂ-አማካይነት ሚናን ሲተገብር የመልክ ተመሳሳይነት አይታይም፡፡

ጆናታን ዊልሰን ከዚህ ጉዳይ ጋር አያይዞ በሚሰጠው አስተያየት “በዘመናዊ እግርኳስ 4-2-3-1 የሚጫወት አንድ ቡድን የግድ በሁለቱም መስመሮች የመስመር አማካዮች ሊኖሩት ይገባል ብሎ ሙግት መግጠም ጋሪው ፈረሱን እንዲጎትተው የመፍቀድ ያህል ነው፡፡” ሲል የቡድኖች ሚዛናዊነት ከቅርጾች መስተካከል በላይ ዋጋ አለው ሲል ያስረዳል፡፡

በእግርኳስ ጨዋታ በሜዳ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ተመዛዛኝ ያለመሆን (Asymmetry) ጉዳይ ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ የነበረና የተለመደ ነው፡፡ በፎርሜሽኖች ታሪክ መጀመሪያ ላይ ከሚጠቀሰው የ1-2-7 ፎርሜሽን በኋላ ጥቅም ላይ የዋለው 2-2-6 ነበር፡፡ በመቀጠልም በዘገምተኛ ለውጥ በአውሮፓ 2-3-5 እየተተገበረ ሲመጣ በቅርጾች ውስጥ የሚታይ ተመዛዛኝነት (Symmetry) ስር ሰደደ፡፡ በእርግጥም በሒደት በፎርሜሽኖች የታሪክ እድገት ሽግሽጎችና መሻሻሎች ሲፈጠሩ ጋዜጦች ፎርሜሽኖችን የሚያቀርቡበትን ዘዴ ለመቀየስ ሲባል ተመዛዛኝነት (Symmetry) እየጎለበተና እየታወቀ ሄደ፡፡ ቀስበቀስም WM (2-3-5/3-2-2-3) በአውሮፓ እግርኳስ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ተሰራጨ፡፡ ለበርካታ ቀጣይ አመታትም በተለያዩ ቡድኖች ተቀዳሚ ተመራጭነትን አገኘ፡፡

በዘመናዊ እግርኳስ በመስመሮች ተመዛዛኝ ያለመሆን ባህሪ (Asymmetrical Behavior) በፎርሜሽኖች ውስጥ አዘወትሮ የሚታይ ሁኔታ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጠን አጋጣሚ የተፈጠረው 2-3-5 በብራዚል ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ በኋላ ነው፡፡

“በፈጠራ ክህሎት የታደለ የግራ እግር ተጫዋች በሜዳው ቁመት ከግራው መስመር ወደ ውስጥ ገባ ብሎ መጫወቱ (Inside-Left) በሌላኛው መስመር ከሚሰለፈው ተጫዋች (Inside-Right) በላቀ የማጥቃት ሚና ተሳትፎ ማድረጉ “10 ቁጥር” ከ “8 ቁጥር” የበለጠ የአጥቂ አማካይነት/ጨዋታ አቀጣጣይነት (Attacking Midfielder/Playmaker) ሚና ኖረው፡፡” የሚለው ህልዮትም ሀሳቡን ያጠናክራል፡፡ በየጊዜው የሚፈጠሩ የአጨዋወት ስልቶችም ለዚህ ሁኔታ የራሳቸውን ተጽዕኖ አሳርፈዋል፡፡ ለምሳሌም ካቴናቺዮ የተባለውና በጥብቅ የመከላከል ስርዓት የሚታወቀው አጨዋወት ተመዛዛኝነትን (Symmetry) በእንጭጩ ማስቀረቱ እና ኢ-ተመዛዛኝነትን በእግርኳስ አመቺና ይበልጥ ተግባራዊ የሚደረግ ቅርጽ እንዲሆን እንዳስቻለም በተለያዩ የታክቲክ ታሪክ ላይ የተጻፉ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የአደራደሮች ተመጣጣኝነት/ተመዛዛኝነት ከቡድን ሚዛን መጠበቅ ጋር ተቀራራቢ የመሆን ሒደትን አለማሳየቱ የAsymmetryን ፋይዳ የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ Symmetry ቡድኖች ተገማች ያልሆኑና ያለመዱት አይነት ችግሮች እንዲያጋጥሟቸው ከማድረጉም በላይ የተጫዋቾችን የተናጠል የአጨዋወት ባህሪ በቀላሉ የሚለይ ያደርጋል፡፡ እንግሊዛውያኖች የለመዱት ተጫዋቾችን በሚጫወቱበት ቦታ የመሰየም ስርዓት (Positional Nomenclature) በቦታው የሚጫወቱ የተለያየ የአጨዋወት ባህሪን የሚያሳዩ ተጫዋቾችን እና ሚናን በአንድ ስያሜ ስር የማድረግ ችግርን ያስከትላል፡፡ ይህም ተጫዋቾች በተለምዷዊው ቦታቸው ብቻ መጫወት አለባቸው የሚለውን ቀኖናዊ መርህ (Dogmatic Principle) ጥያቄ እንዲነሳበት ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ ሲሆኑ ቦታዎች ግን ቋሚ ናቸውና፡፡ በሌሎች አገሮች፤ በተለይም በአርጀንቲናና ጣልያን የአሰያየም ባህሎች ተጫዋቾች በተለየና በተነጠለ ሚናቸው የሚታወቁበትን ሁኔታና ስም ማግኘታቸው በርካታና የተወሳሰቡ ታክቲካዊ ስራዎችን በመስራት በተለያዩ የፎርሜሽን ቅርጾች ተገማች ባልሆነ አቀራረብ የመገኘት እድልን ይሰጣል፡፡ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድም ቢሆን በፎርሜሽኖች ውስጥ ከመዋቅር ተመሳስሎ ይልቅ ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን(Balanced Team) በተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር የቅርጽ ተመጣጣኝነትን (Symmetrical Shape) ከመስራት የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡ በጥንቱ ዘመን በእግርኳስ ቡድኖችና በሚጠቀሙባቸው ፎርሜሽኖች ውስጥ ያለው ተፈጥሮአዊ ልማድ ተመዛዛኝነትን ያማከለ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህልም በ4-3-3 ቅርጽ ተከላካይ አማካዩ ከኋላው በመስመር ተከላካዮቹ ፣ በእርሱ መገኛ አካባቢ በሆነው የመሀል ክፍል በሁለቱ የ”8-ቁጥር ሚና ተጫዋቾች” (shutlers) እና ከፊቱ ደግሞ ከመስመር በሚነሱት አጥቂዎች አማካኝነት የትይዩ ተመዛዛኝነት (Parallel Symmetry) ይሰራለታል፡፡ በዝርጉ 4-4-2ም ቢሆን ሁለቱ የመሀል አማካዮች በመስመሮች በሚሰለፉት ተከላካዮች፣ አማካዮችና አጥቂዎች (ሁለቱ አጥቂዎች በሜዳው ስፋት በአንድ መስመር የሚንቀሳቀሱና ወደ መስመር አዘንብለው የሚጫወቱ ከሆነ) ተመዛዛኝነትን የሚያሳይ ቅርጽ ይሆናል፡፡ ፎርሜሽኖች በመሰረታዊነት አጠቃላይ የሜዳ ላይ የተጫዋቾች አደራደርን በቁጥራዊ ቅርጽ ማሳያ ቀላል ምስሎች አድርገው ማሳየታቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

የዘላቂነት እና ሁሌም በቋሚነት የሚኖሩ መዋቅሮች ባህሪያትን ያሳዩና የሚያሳዩም አይደሉም፡፡ ይህም እውነታ ዘመናዊ እግርኳስን ከቅርጾች ተመጣጣኝነትም በበለጠ በቡድን ሚዛናዊ መሆን ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል፡፡ በዚህም መሰረት በተለይም በእንግሊዛውያኑ እግርኳሳዊ አስተሳሰብና አስተምህሮ መሰረት ለብዙ አመታት በአንደኛው የሜዳ ቁመት የጎንዮሽ መስመር ጠንከር ያለ የማጥቃት ሒደት ካለ በሌላኛው መስመር ደግሞ በመከላከሉ ረገድ እንዲሁ ሚዛናዊ የሚያደርግ የተሻለ ስራ ይሰራ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላም ሚዛናዊነት ማስገኛ መንገዶች በአንደኛው የሜዳ መስመር ብቻ ላይ ትኩረት ይሰጣቸው ጀመር፡፡ በመስመሮችም ሆነ በሌሎች የሜዳ ክፍሎች የማጥቃት ዝንባሌ የሚያሳዩ ተጫዋቾች በመከላከሉ በተሻለ ብቃት በሚጫወቱ ተጫዋቾች መታገዝ ጀመሩ፡፡ በመቀጠልም በሚዛናዊነት ላይ የቁጥር ብልጫ ጥቅምን የሚያስገኝ አሰራር ተፈጠረ፡፡ ተጫዋቾች በራሳቸው የሁለት ብቃት ባለቤት ሆነው ሚዛናዊነትን እንዲላበሱና በተለያዩ የጨዋታ ሒደቶች ውስጥ የበኩላቸውን የሚወጡበት መንገድ ተገኘ፡፡ ይህም በሚዛናዊነት (Balance) ማዕቀፍ ውስጥ የሚቀመጠውና በብራዚላውያኑ እንደተጀመረ የሚነገረው የ(Asymmetry) ጽንሰ-ሐሳብ በዘመናዊ እግርኳስ የተጫዋቾችን ሚናም (Players Roles) ሆነ የቅርጽ ሚዛናዊነትን (Symmetry) የሚያስከነዳ ፋይዳ እንዲኖረው አደረገ፡፡

4) የፎርሜሽኖች ፋይዳ

ታዋቂው የእግርኳስ ታክቲክና ታሪክ ጸሀፊ እንግሊዛዊው ጆናታን ዊልሰን ስለ ፎርሜሽኖች ሲናገር “የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደሮች ጠቃሚ ናቸው፤ ሆኖም ግን በተብራራና ግልጽ በሆነ መንገድ የማይተነተኑና የግርድፍ ትርጉም ባለቤት (Crude) ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እግርኳስን ጥልቀት ባለው አረዳድ ለመገንዘብ እና ለመመልከት እንደ መነሻ መረጃ በመሆን ስለ ቅርጽ አጠቃላይ መልክ የሚናገሩ መሳሪያዎች እንጂ ለቡድኖች በከፍተኛ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑና ሁሉን አሳኪ የሚባሉ መፍትሄዎች አይደሉም፡፡ ግልጋሎታቸውም ጨዋታውን ከሚጫወቱት ተጫዋቾች በላቀ ስለ ጨዋታ የታክቲክ ትንታኔ ለሚሰጡት ባለሙያዎች ያመዝናል፡፡” ይላል፡፡

አንዳንድ የእግርኳስ ባለሙያዎችና ተንታኞች ደግሞ ፎርሜሽኖች በእግርኳሱ ውስጥ ያላቸው ዋጋ እምብዛም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የቀድሞው የሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንድ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና አሰልጣኝ ጆን ጊልስ በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን የእግርኳስ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ በሰጠው አስተያየትም “እግርኳስ የቅርጾችና የመዋቅሮች ጉዳይ ሳይሆን በተጫዋቾች ወቅታዊ ብቃት የሚወሰን ነው፡፡” በማለት ሚናቸው ያን ያህል እንዳልሆነ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡

ፎርሜሽኖች የቡድን የሜዳ ውስጥ የመነሻ አደራደርን ከማመልከት ውጪ ፋይዳቸው እምብዛም እንደሆነ የሚገልጹ ባለሙያዎች ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩ “አንድ ቡድን በጨዋታ የሚኖረውን አጠቃላይ መዋቅራዊ መልክና በተጫዋቾች መካከል የሚኖረውን የእርስበርስ ግንኙነቶች የሚያሳዩ ሲሆን ጨዋታውን የሚወስኑት ግን ተጫዋቾች ውህደት ባለው መግባባት የሚፈጥሩት መስተጋብር (Coherence) ነው፡፡”ይላሉ፡፡

ስላቨን ቢሊች የክሮሺያን ብሔራዊ ቡድን በሚያሰለጥንበት ወቅት ታክቲካዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በሌላ አቅጣጫ እያስኬደ በዘመናዊ እግርኳስ በተጫዋቾች አስተዋፅኦ ከፍተኛ እድገት ምክንያት የታክቲክና ፎርሜሽኖች ሚና እየወረደ ስለመምጣቱ ይሞግታል፡፡ ያም ሆኖ ጠቀሜታቸው በተጫዋቾች የጎላ ድርሻ መሸፈኑን እንጂ ሙሉ በሙሉ አለመክሰሙንም ለማስረዳት ይጥራል፡፡ ይልቁንም ቡድን መገንባት የሚቻለው ለተጫዋቾቹ የሚሆን ቦታዎችን አዘጋጅቶ ክፍተቶቹን በተገቢው ተጫዋቾች ከመሙላትም ይበልጥ ጥሩ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በመሰብሰብ ተከታታይና ዘላቂ የቡድን ጥንካሬን አልያም መለያ ባህሪን ማጎናፀፍና ውጤታማ እንዲሆኑ በማስቻል እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ይህን ሀሳብ ብዙዎች አጠንክረው ቢያስተጋቡትም ጆናታን ዊልሰን ግን ” ክርክሩ ታክቲክ እግርኳስ ውስጥ ያለውን ዋጋ በመጠኑም ቢሆን የሻረ እንዲመስል ያደርገዋል፡፡ እንዲህ አይነት ድምዳሜዎች ላይ መድረስ ፎርሜሽኖች፣ታክቲክና ሌሎች ከቡድን የአቀራረብ ቅርጽ ጋር የተገናኙ ነገሮች በእግርኳሱ ያላቸውን ተፅዕኖ ካለመረዳት ጋር በተያያዘ ተጫዋቾች ከታክቲካዊ አውታር ማዕቀፍ ውጪ የሆኑና የተነጣጠሉ ናቸው ብለን እንድናስብ ያስገድደናል፡፡ የትኛውም የእግርኳስ ጨዋታ ያለ ተጫዋቾች እና ታክቲክ ውህደት ሊከናወን አይችልም፡፡ የሚሆን ወይም የሚሞከርም አይደለም፡፡ በቡድን ውስጥ ከአንድ ተጫዋች በላይ የመኖሩን ያህል የርስበርስ ግንኙነቶችም የግድ ይሆናሉ፡፡ ምንም ትንሽ የሀሳብና የመስተጋብር ልውውጥ ይደረግ ታክቲካዊ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን በሜዳ ውስጥ የተጫዋቾችን ስርጭት የሚያመለክተው ፎርሜሽን ከተጫዋቾቹ የበለጠ ሚዛን አለው ማለት አይደለም፡፡” በማለት የራሱን ምልከታ ያስቀምጣል፡፡

ዘወትር ስለ ፎርሜሽኖች እንደሚነገረው አደራደሮች ግርድፍና ዘለቄታዊ ፍቺ የሌላቸው መለያዎች ወይም ማሳያዎች ቢሆኑም እንደ ሰፊ ገላጭ ወይም ማብራሪያ ንድፍ ያገለግላሉ፡፡

እግርኳስ የቡድን ጨዋታ መሆኑ ግልጽ ነው፤ቡድን የጋራ ለሆነ አላማ እንደ አንድ መዋሀድና ታክቲካዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይም የበቃ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህም ልዩነትን ፈጥሮ ሌላኛው በዚህ መንገድ ከማይጓዝ ቡድን አንፃር ብልጫን ያስገኛል፡፡ፎርሜሽኖች በራሳቸው ስኬት ማምጫ መንገዶች ባይሆኑም በአግባቡ የተሰራባቸው መዋቅራዊ አደራደሮች ውጤታማ ለመሆን የሚደረጉ ጥረቶችን ከፍ ለማድረግና እድሎችን ለመጠቀም ያግዛሉ፡፡ አንዳንዴም በቡድን ውስጥ በሚገኙ የተጫዋቾች ደካማና ጠንካራ ጎኖች ተመስርተው ቡድኖች የሚጠቀሙባቸውን ፎርሜሽኖች ይወስናሉ፡፡ ተጫዋቾች በፎርሜሽኖች ውስጥ በሚሰጣቸው የመጫወቻ ቦታ ላይ ተደላድለው ለመግባትና ለመላመድ ጊዜን ይፈልጋሉ፡፡ አሰልጣኞች ቡድናቸው በሚፈልጉት መንገድ እንዲጫወትላቸው፣ ተጫዋቾችም በተገቢውና ለቡድናቸው ምርጡን በሚያበረክቱባቸው ቦታዎች እንዲሰለፉ ፎርሜሽኖች መነሻ ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ተጫዋቾች በቡድን ውስጥ የሚኖራቸውን ጥብቅ የሆነ የቦታ አያያዝ እንዲሁም ቴክኒካዊ የተናጠል ብቃትና ታክቲካዊ ግንዛቤ በውህደቱና ቡድን በመገንባቱ ረገድ ያለውን ጉልህ ድርሻም ሆነ አሉታዊ ሚና ለመረዳት የፎርሜሽኖች ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ የኮከቡንና በቸልተኝነት ዝቅ ያለ ግምት የሚሰጠውን (underrated) ተጫዋቾች ሚዛናዊነትንም ለማስተዋል ያግዛሉ፡፡ ከጥብቅ የቦታ አጠባበቅ ስርዓት አንፃር በየትኛው ቦታ ላይ ችግር እንዳለና ችግሩ እንደቡድን የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማሳየት ያስችላሉ፡፡ በጨዋታ የሚታዩ ጥቃቅን ግን ደግሞ ጥርቅም ሲሉ ገዘፍ ያለ ዋጋ የሚኖራቸውን ዝርዝሮችን እየተረዳን እግርኳስን እንድንቃኝ ያደርጉናል፡፡

5)ፎርሜሽኖችና የመዋለል ሒደታቸው

ፎርሜሽኖች በእንቅስቃሴያዊ ሒደት ውስጥ የመዋለል አዝማሚያን ያሳያሉ፡፡ ስለዚህም አንድ ቡድን በመነሻነት የጀመረበት ፎርሜሽን በሙሉ የጨዋታው ጊዜ የሚታይ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በጨዋታው ላይ በሚኖሩት ምልልሳዊ ሒደቶች (Cycles) ውስጥ ዋላይ(Fluid) ወይም በየጊዜው ተቀያያሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ የውቡ እግርኳስ መገለጫም ይኸው የማያቋርጥ እንቅስቃሴያዊ ፍሰትና መዋለል ውስጥ ተጫዋቾች የሚያሳዩት የቦታ አያያዝ አቋም (Positioning Discipline) ነው፡፡

እጅግ በጣም በዘመነው የእግርኳስ ደረጃ የጨዋታ ፍሰትና ፍጥነት ተደጋጋፊ ውህደትን ያሳያሉ፡፡ ይህም ሁኔታ ተጫዋቾች የሚንቀሳቀሱባቸው አመዛኝ የሜዳ ክፍሎች እና ታክቲካዊ ጉዳዮች መሰረታዊና ተወራራሽ ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ የቀድሞ በመስመሮች የተገደበ የተጫዋቾች እንቅስቃሴን የሚያሳዩ ፎርሜሽኖችም (Rigid Formations) በነበራቸው የቦታ ውስንነት ምክንያት አዲስ የተለጣጭነት መልክን (Elasticity Behavior) እያሳዩ የመዋለል ፀባይን ተላብሰዋል፡፡

ወጥ ባልሆነ አደራደሮች የሚጫወቱ ቡድኖች ደግሞ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ተገማችነት ለመቀነስና ተጋጣሚን ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ለመቅረብ ብዙውን ጊዜ በተለይም በማጥቃት የጨዋታ ምዕራፍ ላይ ከሁለት ፎርሜሽኖች ውህደት የተገኘ ቅርጽን (Hybrid Formation) ይጠቀማሉ፡፡

6)ፎርሜሽኖችና ከአጨዋወት ዘይቤ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው?

በቀደመው ዘመን እግርኳስ ፎርሜሽኖች የአንድ ቡድን አጨዋወት ዘይቤን (Playing Style) ወይም ሐሳብን (Idea) አመላካች ሆነው ይታዩ ነበር፡፡ በየጊዜው በሚፈጠሩ ታክቲካዊ መሻሻሎች ምክንያት የሚመጡ የአጨዋወት ስልቶች ከተለያዩ የፎርሜሽን አይነቶች ጋር የመዋሀድ ሁኔታን አሳይተዋል፡፡ በተለምዶ ብዙውን ጊዜ ፎርሜሽኖች የአንድን ቡድን መሰረታዊ የአጨዋወት ስልት ያሳያሉ ይባላል፡፡ ሆኖም በዘመናዊ እግርኳስ ታክቲካዊ እይታ ውስጥ እውነታው ከዚህ የራቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እርግጥ ከማራኪ አጨዋወት ፍልስፍና ጋር በተገናኘ የተመረጡ ፎርሜሽኖችን አዘወትሮ የመጠቀም እና ሌሎች የተወሰኑ ፎርሜሽኖችን ደግሞ ውበት ለሌለውና መከላከል ላይ ያመዝናል ተብሎ ለሚጠቀስ የጨዋታ አቀራረብ መተግበሪያ የሚያገለግሉ በማድረግና የዓሉታዊነት ገፅታን በማላበስ ብዙም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የማድረግ አዝማሚያዎች ይታያሉ፡፡ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ያመዘነው አጨዋወት ከ 4-3-3 ጋር፣ በጥብቅ የመከላከል ስርዓት ላይ ያተኮረውም ከ 5-3-2፣ 4-5-1፣ 5-4-1……… ጋር፣ ቀጥተኛውና ረጃጅም ቅብብሎች ላይ የተመሰረተው ደግሞ ከ ጥብቁ 4-4-2 ጋር የተቆራኙ የአጨዋወት ስልቶቾ ነበሩ፡፡ ፎርሜሽኖችና የአጨዋወት አቀራረብ ፍልስፍናዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ሁሉም የጨዋታ ፍልስፍና ዘይቤዎች በተለያዩ ፎርሜሽኖች ውስጥ መተግበር ይችላሉ፡፡ አንድ የአጨዋወት ዘይቤ በተወሰነ ፎርሜሽን ውስጥ ተስማሚ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ባለመደረጉ እና ውጤታማ ባለመሆኑ ምክንያት ብቻ የስልቱን ጠቃሚነት አይቀንሰውም፡፡ ስለዚህም የአንድን የአጨዋወት ዘይቤ ስኬትና ውድቀት ቡድኑ በሚጠቀምበት ፎርሜሽን ላይ ጥገኛ ማድረግ የስህተት ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡

7) ተመሳሳይ ፎርሜሽኖችና የአተገባበር ልዩነቶች

በ <The Tomkins Times> ድረ ገጽ የእግርኳስ ታክቲካዊ ጉዳዮችን በጥልቀትና በከፍተኛ የልህቀት ደረጃ የሚዳስሰው ሚሃይል ቭላዲሚሮቭ “የእግርኳስ ታክቲክ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችም ሆኑ የጨዋታ ቀጥታ ስርጭት አስተላላፊዎች ፎርሜሽኖችን የሚያቀርቡበት መንገድ በጣም ቀላልና የወጥነት መልክ የሚያሳዩ አድርገው ነው፡፡” ይላል፡፡ ሁለት ቡድኖች ተመሳሳይ ፎርሜሽኖችን ተጠቅመው ነገርግን የተለያየ መልክ ሊኖራቸው እንደሚችልም ይናገራል፡፡ ቡድኖቹ በአጨዋወት ሒደት ላይ በሚያሳዩት የተጫዋቾች ሚና ትግበራ ስርዓት፣በሚሰጡት ትኩረትና በሚኖራቸው የመከላከል እና የማጥቃት አቀራረብ ልዩነት ሊያሳዩ የሚችሉበት አዝማሚያ ስለመኖሩም አበክሮ ያስረዳል ፡፡ “ተመሳሳይ መነሻ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ወይም ቅርጽ ኖሯቸው የተለያየ አቀራረብን የሚያስከትሉ ፎርሜሽኖች በጨዋታ ሒደት የተለያየ እንቅስቃሴያዊ መልክ ይኖራቸዋል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳትም ሁለት ቡድኖች ዝርጉን 4-4-2 ይጠቀማሉ እንበል፡፡ አንደኛው ቡድን በጨዋታው የማጥቃት ሒደት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ሲከተል 4-2-2-2ን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ሌላኛው ቡድን ደግሞ በመልሶ ማጥቃት አተገባበር የ4-2-4 ወይም 4-0-6 አደራደር ሊያሳይ ይችላል። በመከላከል ሂደትም እንዲሁ ቡድኖቹ በሚተገብሩት ተቀዳሚ የመከላከል ስልት መሰረት የመጀመሪያው ቡድን ከኳስ ውጪ በ4-2-3-1፣ 4-5-1 እና ሌሎች የሚዋልሉ መዋቅሮች የመከላከያ አደረጃጀቱን አጠናክሮ ልንመለከት እንችላለን፡፡ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ተጋጣሚው ላይ ከፍተኛ ግፊት እየፈጠረ በ4-1-4-1፣ 4-4-1-1ና መሰል ሌሎች ፎርሜሽኖች ይቀርብ ይሆናል፡፡” በማለት ያብራራል፡፡ ይህም በዘመናዊ እግርኳስ በተጫዋቾች የሚዋልል እንቅስቃሴ፣ ዘወትር በሚኖር ቅይይር እንዲሁም በሁሉም የጨዋታ ሒደቶች በሚታዩ የተለያዩ የትግበራ መንገዶች አማካኝነት በሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜ ቡድኖች የሚያሳዩትን የፎርሜሽኖች ህብር (Combinations of Formation) ያመለክታል፡፡ በጨዋታ የቅድመ-ምስል ምልከታ ወቅት የፎርሜሽኖች ይዘት ወጥና ቋሚ መልክ ቢኖረውም በእንቅስቃሴያዊ ሒደትና በጨዋታ ምልልሶች ጊዜያት ደግሞ የመዋለል ባህሪን ያሳያል፡፡ ፎርሜሽኖች ቅርጻቸውን በተደጋጋሚ የመቀያየር (morphing) ባህሪ ጅምር መዋቅሩ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ (lopsided) ሲሆን ይጎለብታል፡፡ በሜዳው ቁመት የተጣመመ 4-2-3-1ን የሚተገብር ቡድን ሲከላከል የጠራና በግልጽ የሚታይ 4-3-3 ሆኖ በማጥቃት ሒደት ደግሞ 4-2-4 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን ልናስተውል እንችላለን፡፡

8)የፎርሜሽኖች የእርስበእርስ ግንኙነት

በእግርኳስ በመርህ ደረጃ በቋሚነት የሚቀመጥና አንዱ ፎርሜሽን ከሌላው የተሻለ እንደሆነ የሚነገርበትን መሰረታዊ ሀሳብ የሚሰጥ እውነታ አልተገኘም፡፡

ፎርሜሽኖች እርስ በእርሳቸው ሲገናኙ ወይም አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ሲነፃፀሩ ሁሌም ትኩረት የሚደረግባቸው ተለምዶአዊና ተገማች ነጥቦች ይነሳሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰውም <በ4-3-3 ፎርሜሽን የሚጠቀም ቡድን 4-4-2 ፎርሜሽንን ከሚመርጥ ባላጋራ ላይ በመሀል ክፍሉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሚያስገኝለትን ሁኔታ በአማካይ ተጫዋቾች የቁጥር ብልጫ ይወስዳል፡፡ በተቃራኒው ባለ 4-4-2 ፎርሜሽን ተጠቃሚው ቡድን ደግሞ ከሜዳው የስፋት መስመሮች (wide areas) በማጥቃት እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት መሰንዘር ይችላል፡፡> የሚለው መርህ መሰል ምልከታ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን እነዚህ ድምዳሜዎች በደፈናው የሚጠቀሱና እንደ አስተያየት የሚያገለግሉ ሀሳቦች ብቻ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም በእግርኳስ ምስጋና ለጥልቅ እይታ ባለቤቶችና ህልዮታውያን የታክቲክ አብዮተኛ አሰልጣኞች ይግባና በየጊዜው ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄ እየተገኘለት ከላይ የተጠቀሰውን አይነት በግልጽ የሚታወቁ የፎርሜሽን ጽንሰ-ሐሳባዊ ህጸፃች በእንቅስቃሴያዊና ተግባራዊ ስልቶች እየተፈቱ ይገኛሉ፡፡ 4-4-2ም በተለያዩ ሌሎች ዝርያ ፎርሜሽኖች አማካኝነት ጥቅም ላይ እየዋለና እያደገ ሄዶ የመርህ ያህል የሚታወቀውን ከሁለት በላይ ተጫዋቾችን በመሀለኛው የሜዳ ክፍል የማሰለፍ ዕድል ያለው ፎርሜሽን በመሀል ክፍል የሚደርስበትን የቁጥር ብልጫና የሚከተልበትን መዘዝ በሌሎች ታክቲካዊ ሽግሽጎች ሊያካክሳቸው ችሏል፡፡ አንደኛ ተደርጎ የተወሰደው መፍትሄ ደግሞ በ4-4-2 ፎርሜሽን የመሃል ሜዳ አማካይ ተጫዋቾች በሜዳው ስፋት የሚኖራቸው ጥግግት (Horizontal Compactness) ነው፡፡

9)ፎርሜሽኖች በራሳቸው ታክቲክ ናቸው?

ፎርሜሽኖች ታክቲክ መተግበሪያ መሳሪያዎች እንጂ በራሳቸው ታክቲክ አይደሉም፡፡

ስኮትላንዳዊው የእግርኳስ ጸሀፊና ጋዜጣኛ ግርሐም ሀንተር “ብዙ ሰዎች በፎርሜሽኖችና በታክቲካዊ ሁነቶች ዙሪያ ሲወያዩና ሐሳብ ሲሰጡ አስተውያለው፡፡ ሆኖም በረጅሙ የስራ ልምዴ ከተጫዋቾችም ሆነ ከአሰልጣኞች የተማርኩት ሁሉም ፎርሜሽኖች አሰልጣኞች የጨዋታ ታክቲክ እቅድን የሚነድፉባቸው መሰረታዊ የመነሻ ቅርጾች መሆናቸውን ነው፡፡” ይላል፡፡ “ፎርሜሽኖች የተለዋዋጭነት መልክን የተላበሱ፣ በአንድ ቡድን ውስጥ ለሚገኙ ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪ ተስማሚ የሆኑ፣ ሊተገበር ለተፈለገው ታክቲክና ለተጋጣሚ ቡድን የአቀራረብ ዘይቤ በልክ የተሰፉ መሆን (ምክንያቱም አሰልጣኞች የተቃራኒ ቡድን ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ) ይኖርባቸዋል፡፡” በማለትም ያክላል፡፡ እግርኳስ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ሲያስረዳም ” ሰዎች በፎርሜሽኖች ውስጥ ስለሚገኙት ቁጥሮች በማውሳት ሁሉንም ዋጋ ለቡድኖች ቅርጽ የመስጠት ዝንባሌን ያሳያሉ፤ ሆኖም እግርኳስ የፎርሜሽኖች፣ የተጫዋቾች ብቃትና የታክቲክ ህብር ውጤት ነው፡፡” የሚል ድምዳሜን ይሰጣል፡፡

በእርግጥም ከጨዋታ ቀድሞ በሚወጡ የቋሚ ተሰላፊዎች ዝርዝር መረጃዎች መሰረት የቡድኖችን ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የተጫዋቾችን የተናጠል ክህሎት በምን መልኩ እንዲቀናጅ ማድረግ እንደሚቻል፣ ከተጋጣሚው ቡድን አንጻር ሊሳኩ የሚችሉና የማይችሉ ጥምረቶችንና የውህደት ጥንካሬዎችን በቅድመ ግምት ደረጃ ምናባዊ ስዕል ለማስቀመጥ እንችላለን፡፡ በተለይም የተለመደ፣ ወጥና ቋሚ አሰላለፍን የሚጠቀሙ አሰልጣኞች በተመራጭ የአጨዋወት መንገዳቸው ላይ ግምታዊ ምልከታ እንዲኖረን ከማድረግ የዘለለ ቡድናቸው ጨዋታ እንዲጀምርበት የሚወስኑት ፎርሜሽን አጠቃላይ ታክቲኩን የመግለጽ አቅም የለውም፡፡ ተገማች ያልሆነና በየጊዜው የሚቀያየር አቀራረብን የሚያዘወትሩ ቡድኖች ደግሞ በቋሚ ተሰላፊዎቹ ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪና ችሎታ ብቻ ተመርኩዞ መነሻ ፎርሜሽኖች የሚሰጡን ጅምር የእንቅስቃሴ ስዕሎች የጨዋታውን ሙሉ ጊዜ መልክ የማሳየትና ያለማሳየት አዝማሚያ ሊኖራቸው እንደሚችል ልንገነዘብ ይገባል፡፡ የአንድን ቡድን አጠቃላይ ገጽታ ለመረዳት በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የቡድኖቹን ቅርጽ አጠባበቅ፣የመከላከል አደረጃጀት እና የማጥቃት እንቅስቃሴያዊ ሒደት በጥንቃቄ ማስተዋል ይሻል፡፡

10)ፎርሜሽኖች የሙሉ ቡድንን ቅርጽ የመወከል አቅም አላቸው?

ከጥቂት አስርት አመታት ወዲህ ከእግርኳስ መሰረታውያን መካከል ለታክቲክ የተሰጠው ቦታ እጅጉን እየገዘፈ መጥቷል፡፡ በፎርሜሽኖች ዙሪያ የሚደረጉ ክርክሮችና ውይይቶችም እንዲሁ ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በተለምዶ የተወሰኑ ፎርሜሽኖች በተለይም 4-4-2 የተጫዋቾችን የቦታ አያያዝና አጠቃቀም በተገቢ አኳኋንና በተሻለ ትክክለኛነት እንደሚወከል ይነገርለት ነበር፡፡ ሆኖም በ<Planet Football> የእግርኳስ ጸሀፊ የሆነው ማርክ ሆልምስ “በዘመናዊ እግርኳስ የፕሮፌሽናል ቡድኖችን እንቅስቃሴያዊ መዋቅሮች በንዑሳን የቁጥር አደራደሮች በበቂ ሁኔታ መግለጽ ይቻላል?” በማለት ፎርሜሽኖች ሙሉ የቡድን ቅርጽን በአግባቡ ስለመግለፃቸው ጥያቄ ያነሳል፡፡

የ<Zonal Marking> ታክቲካዊ ድህረ-ገጽ መስራችና አዘጋጁ ማይክል ኮክስ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የሚሰጠው ምላሽ አለው፡፡ “ከጨዋታ ኡደት (Cyclical Process) ምዕራፎች አንዱና ዋነኛ በሆነው የመከላከል ስርዓትና በአጠቃላይ አንድ ቡድን ከኳስ ቁጥጥር ውጪ ሲሆን ጠንካራ የተጫዋቾች የመስመር አደራደርንና ጥብቅ የቦታ አያያዝን (Structural Positioning) በበርካታ ቡድኖች እንመለከታለን፡፡” በማለት ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ሀሳቡን በስፋት ሲያብራራም ” በዚህ ዘመን የእግርኳስ እድገት ደረጃ የቡድኖች አጠቃላይ የማጥቃት እንቅስቃሴዘ አላማ (Attacking Aim) ጠንካራ የመከላከል አደጃጀቶችን የመበታተን፣በተጋጣሚ የተከላካይ እና አማካይ መስመሮች መካከል(Between The Lines) ክፍተትን በመፈለግ በላይኛው የሜዳ ክፍል የሚገኙ የማጥቃት ተጫዋቾች በቦታው እንዲገኙ ማድረግ እና የመጫወቻ ቦታዎችን በመለዋወጥ (Changing Positions) ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህም ምክንያት በማጥቃት ሒደት የቡድኖችን ቅርጽ በፎርሜሽኖች ደረጃ ለማስቀመጥ ያስቸግራል። እንደ ጓርዲዮላ ባሉ አሰልጣኞች የሚሰለጥኑና በሚመርጡት አጨዋወት የመዋለልና በፍጥነት የቅይይር ባህሪን የተላበሱ (Fluidity Character) ቡድኖች ላይ የሚታዩት ፎርሜሽኖች በቀላሉ የማይታይ የትርጉም ልዩነት (nuances) እንዳላቸው ቢታወቅም በመሰረታዊነት በሶስት ወይም በአራት ተከላካዮች መጫወት የቅርጽ መለያየትን መፍጠሩ እርግጥ ነው፡፡” ይላል፡፡ “ፎርሜሽኖች የቡድኖችን የመከላከል አደረጃጀትና በሜዳ ላይ የሚገኙ የመጫወቻ ቦታዎችን ለመግለጽ ቢያስችሉም ዋናው ጉዳይ ግን በኳስ ቁጥጥር የበላይነት የምትቆይበት ጊዜና ቅብብሎች የሚኖራቸው እንቅስቃሴና ጥራት ነው፡፡” በማለት በዘመናዊ እግርኳስ በመከላከል አጨዋወት ጥብቅ ትስስር ያለው ቦታ አያያዝ እና በማጥቃት ሒደት ደግሞ የተጫዋቾች የሚዋልል እንቅስቃሴ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ይገልጻል፡፡ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕም የኮክስን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ የ<Sky Sports> አዘጋጆች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽም በመከላከል ሒደት ቡድናቸው እንደሁኔታው (አንድ የተከላካይ አማካይ ሲጠቀም) በ4-4-2 ሲከላከል በኳስ ቁጥጥር የበላይነትና የማጥቃት ሒደቶች ግን ውስን የቡድን ቅርጽ(ፎርሜሽን) እንደማያሳይ ይናገራሉ፡፡ ወደ ሰባት የሚጠጉ ተጫዋቾች በማጥቃት ወረዳው የመገኘትና በተለያዩ ቦታዎች የመጫወት ነፃነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ስለዚህም በማጥቃት ሒደት ይህን መሰል እንቅስቃሴና ቦታ አያያዝ በፎርሜሽኖች ሊገለጽ አለመቻሉን እንረዳለን፡፡

11) የቋሚ ተሰላፊዎች ዝርዝር መነሻ ፎርሜሽኖችን እንድንለይ ይረዳል?

በቅድመ ጨዋታ የቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾች ስም ዝርዝርን የሚያሳዩ መረጃዎች አሰልጣኞች ከተጫዋቾቻቸው ምርጡን ግልጋሎት ሊያገኙ የሚችሉበትን የሜዳ ላይ አደራደር ሙሉ በሙሉ ባያመላክቱንም የተወሰነ ፍንጭ የምናገኝባቸውን መንገዶች ግን ሊመሩን ይችላሉ፡፡ በተጫዋቾች ወቅታዊ ብቃትና የአጨዋወት ባህሪ፣ በአሰልጣኞች ታክቲካዊ እቅድ፣በተጋጣሚ ቡድን አቀራረብ እና በጨዋታው ዋጋ (የአስፈላጊነት መጠን) መሰረት የጨዋታው እንቅስቃሴ ስለሚወሰን በሚታወቀው መደበኛ የተሰላፊዎቹ ቦታ ላይ ተንተርሶ የፎርሜሽኖችን ቅድመ-ይዘት መወሰን አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ተንታኞች አስቀድመው በሜዳው የተለያዩ ክፍሎች ሊሰለፉ የሚችሉና አንድ-ለ-አንድ የሚገናኙ ተጫዋቾችን አንጻራዊ ብቃትና ጥንካሬ እንዲሁም ደካማ ጎኖች ግምታዊ ቅድመ-ግምገማ እንደሚሰሩባቸው ሚሃይል ቭላዲሚሮቭ ይናገራል፡፡

12)ፎርሜሽኖች ከስመው ቀሪ ናቸውን?

ፎርሜሽኖች በዘለቄታዊነት ጥቅም ላይ የመዋል ባህሪያትን አልተላበሱም፡፡በተለያዩ የአጨዋወት ስልቶች ውስጥም እንደ አስፈላጊነታቸው ይገባሉ፤ይወጣሉ፡፡ ደብዝዘውና ከስመው ቢሰወሩም እንኳ በታክቲካዊ መሻሻሎች ምክንያት ከዘመናት በኋላ ተመልሰው ሌላ የዝርያ ቅርጽ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ዝርጉና የሜዳውን ስፋት መስመሮች ታከው በሚጫወቱት የመስመር አማካዮች የሚጠቀመው 4-4-2 እንኳ በጠባቡ 4-4-2፣በዳይመንድ 4-4-2(4-1-2-1-2)፣ በ4-1-3-2፣በ4-3-1-2፣በ4-4-1-1 እና ሌሎችም) ጥቅም ላይ ውሎ ተመልክተናል፡፡ 3-5-2ም ቢሆን 3-1-4-2፣ 3-4-1-2፣ 3-4-2-1፣ 3-5-1-1፣ 5-3-2 እንዲሁም ዋናውን ዝርግ 3-4-3 እየሆነ ዳግም ጥቅም ላይ መዋሉን ልብ ይሏል፡፡ ከ80 አመታት በፊት ያገለገለው 2-3-5ም በዚህኛው ዘመን እግርኳስ እንደ መነሻ ሆኖ ባናየውም እንቅስቃሴያዊ በሆነ የጨዋታ ሒደት (Phases) በተለይም የማጥቃት ሒደት ላይ እጅጉን በታክቲክ ዝግመታዊ እድገት ከፍተኛ እምነት ባላቸው እንደ ጓርዲዮላ አይነት አሰልጣኞች ቡድኖች ውስጥ 2-3-2-3 ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *