ቻምፒየንስ ሊግ | የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኬሲሲኤ አሰልጣኞች ከጨዋታው በፊት የሰጡት አስተያየት

የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ካርሎስ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ እና የካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦውቶሪቲ (ኬሲሲኤ) አሰልጣኝ ማይክ ሙቴይቢ ስለወሳኙ የሁለቱ ክለቦች የቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ለዩጋንዳ ሚዲያዎች አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡

“እኔ እንደማስበው ለሁለታችንም ከባድ ጨዋታ ነው የሚሆነው” ካርሎስ ማኑኤል ቫዝ ፒንቴ

“እኔ እንደማስበው ለሁለታችንም ከባድ ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ በነበረው ጨዋታ ተጫዋቾቼን የነገርኳቸው ማሸነፍ እንዳለብን እና ግብ ማስተናገድ እንደሌለብን ነበር፡፡ ሁሌም ወደ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ለተጫዋቾች፣ ለአሰልጣኞች፣ ለክለቡም ሆነ ለሃገሪቱ ወሳኝ ነው፡፡ ዓምና በቀድሞ ክለቤ ወደ ምድብ ማለፍ ችለን ነበር (ኮንፌድሬሸን ዋንጫ)፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስም ይህኑን ለመድገም ነው ፍላጎቴ፡፡”

“የተለየ ጨዋታ እና ታሪክ ነው ሜዳ ላይ የሚኖረው፡፡ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከቀናት በፊት የተደረጉ ጨዋታዎችን ከተመለከትን ያለፈ ጨዋታ እምብዛም ትርጉም አይኖረውም፡፡ ሲቪያ በቻምፒየንስ ሊጉ ታሪክ የለውም፤ ግን ማንቸስተር ዩናይትድን ከውድድር አሰናብቷል፡፡”

“በሜዳችን ወይም ከሜዳችን ውጪ ስንጫወት ተጫዋቾቻችን ስለጨዋታዎች በሚገባ ይረዳሉ፡፡ ካምፓላ ላይ የሚደግፉን ደጋፊዎች ይኖራሉ፤ ወሳኙ ነገር ግን ትኩረት ማድረጋችን ላይ ነው፡፡”

“የመጫወቻ ሜዳው የተለየ ነው፤ ሰው ሰራሽ ሳር ነው፡፡ ቢሆንም ተጫዋቾቼ ሜዳውን በሚገባ ያውቁታል፡፡”

“መጠንቀቅ እና እድሎችን ስናገኝ መጨረስ ይገባናል” ማይክ ሙቴይቢ

“እውነት ለመናገር ተጫዋቾቻችን ለጨዋታው ያላቸው መነሳሳት እና ዝግጁነት መልካም ነው፡፡ ይህ የነሱ ግዜ እንደሆነ እና የሚፈለገውን ውጤት ማሳካት እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ከዚህ በፊት በጉዳት ከጨዋታ ውጪ ከሆኑት በተጨማሪ ሌላ የጉዳት ዜና የለንም፡፡ ሳዳም ጁማ ለሁለት ወር ከሜዳ ይርቃል፡፡ ከዚህ ውጪ ሙሉ ቡድኑ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል፡፡”

“የምንጫወተው ኳስን በጥሩ መልኩ ከሚጫወት ቡድን ጋር ነው፡፡ እነሱ የተሻለ አድቫንቴጅ እንዳለቸው ሊያስቡ ይችላሉ፤ ምክንያቱም የመጀመሪያው ጨዋታ ያለግብ አቻ ነው ጨዋታው የተፈፀመው፡፡ እዚህ ሲመጡ ግብ ማስቆጠር በፍጥነት እንዳለባቸው አምነው ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ በዚህ መልኩ ለማጥቃት እንደሚመጡ፡፡ እኛም እናጠቃለን እነሱም ያጠቃሉ፤ ስለዚህ ክፍት ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ መጠንቀቅ እና እድሎችን ስናገኝ መጨረስ ይገባናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *