” የምንከላከል ከሆነ ስህተት መስራታችን አይቀርም ” በዛብህ መለዮ

በአፍሪካ የክለቦች መድረክ ኢትዮጵያ ወክሎ በመሳተፍ ላይ ያለው ወላይታ ድቻ ዛማሌክን በሜዳው 2 – 1 በማሸነፍ ለመልሱ ጨዋታ ከትላንት በስቲያ ምሸት ወደ ግብፅ አምርቷል። በመጀመርያው ጨዋታ ለወላይታ ድቻ ማሸነፍ ትልቁን ሚና የተጫወተው በዛብህ መለዮ ለጨዋታው ስላደረጉት ዝግጅት ፣ ስለ የእስካሁኑ ቆይታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዛሬ ከስፍራው ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ መልኩ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

” ግብፅን እንደጠበቅናት አላገኘናትም። ከኛ ጋር የሚመሳሰል በጣም ተመሳሳይ የሆነ የአየር ፀባይ አላት። ወደዚህም በሰላም እና ደስ በሚል መልኩ መጥተናል። አሁን ላይ የቡድናችን መንፈስ ደስ የሚል ድባብ አለው። ትላንት የመጀመሪያ ልምምዳችንን ስንሰራም ደስ የሚል ነገር በቡድኑ ውስጥ በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ። ይህም ለኛ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተለየ እና በተመቸ ሜዳ ላይ ትላንት ልምምዳችንን የሰራን ሲሆን በካይሮ ስታዲየም ሁለተኛ የመለማመጃ ሜዳ ላይ ነው ልምምዱን ያደረግነው።”

” አሁንም የኛ እቅድ ወደ ሜዳ ስንገባ አሸንፎ ለመውጣት ነው። ውጤቱ በእጃችን ነው ብለን ለመከላከል አንገባም። ባለን የማሸነፍ መንፈስ ተጠቅመን አሁንም ወደ ቀጣይ ዙር ምናልፈው እኛ ነን። ገና 90 ደቂቃ ይቀረናል። እንከላከላለን ውጤትም አስጠብቀን እንወጣለን የሚባል ነገር በኛ ውስጥ የለም። የምንከላከል ከሆነ ስህተት መስራታችን አይቀርም። ትላንት ልምምድ ስናደርግ በነበረው መሠረት አጥቅተን ለማሸነፍ እንገባለን፤ እኛ አሁንም አሸንፈን በማለፍ የኢትዮጵያን ህዝብ በድጋሚ እናስደስታለን። ”

ወላይታ ድቻ ማረፊያውን በግብፅ አየር መንገድ አቅራቢያ በሚገኘው ኖቫ ሆቴል ያደረገ ሲሆን ከትናንቱ ልምምድ በኃላ ዛሬ ምሽት 1 ሰአት ላይ ጨዋታውን በሚያደርግበት ካይሮ ከተማ 30 ሺህ ተመልካች በሚይዘው አልሰላም ሜዳ ላይ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *