ከፍተኛ ሊግ | አዲስ አበባ ደረጃውን ሲያሻሽል ፌደራል እና ደሴም አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ14ኛው ሳምንት እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታዋች ተደርገው አዲስ አበባ ከተማ ወደ ሁለተኛነት ከፍ ያለበትን ድል ሲያስመዘግብ ፌደራል ፖሊስ እና ደሴ ከተማም ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያግዝ ነጥቦችን አሳክተዋል።


ደሴ ከተማ 1 0 አክሱም ከተማ

(በዮናታን ሙሉጌታ)

የደሴ ከተማ እና አክሱም ከተማ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም ሰሞኑን ሲካሄድ በነበረው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የመዝጊያ ፕሮግራም ምክንያት ከ40 ደቂቃ መዘግየት በኃላ የተጀመረ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ መነቃቃት ያሳዩት ደሴዎች የግብ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ። በዚህም 3ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር አማካዩ ክብሮም አፅብሀ በቀኝ በኩል ከርቀት የመታው ኳስ ለጥቂት በአክሱሞች ግብ ጎን ወጥቶበታል። ኳስ ይዘው በመጫወት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደሩጉት ጥረት እየተሳካላቸው የመጡት አክሱሞች በበኩላቸው 8ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ክፍሎም ሐጎስ መቶ ኳስ ግብ ጠባቂውን ብታልፍም የደሴው ግራ መስመር ተከላካይ አሰፋ ይመር ከመስመር ላይ አውጥቷታል። 13ኛው ደቂቃ ላይ መዋዕል ቀፀላ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው እና ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም አጥቂው ቢንያም ደበሣይ ከመስመር አሻግሮት ሀፍቶም ገብረ እግዚአብሔር በግንባሩ ሳይጠቀም የቀረው ኳስ የአኩሱሞችን የበላይነት ያሳዩ ሙከራዎች ነበሩ። ደሴዎች የመጀመሪያውን ያህል ባይሆንም አልፎ አልፎ ወደ ግብ ሲሄዱ ቆይተው 31ኛው ደቂቃ ላይ ግዙፉ የፊት አጥቂ ቢኒያም ጌታቸው ከተስፋዬ ወሰን ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ ባደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ከተጋጣሚያቸውን የተሻለ የሚባል ንፁህ እድል የፈጠሩ ቢሆንም ቀዝቃዛ የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ያለግብ መጠናቀቁ ግን የግድ ነበር።

ከእረፍት መልስም በተሻለ ወደ ግብ መድረሳቸውን የቀጠሉት አክሱሞች 48ኛው ደቂቃ ላይ ቴውድሮስ መብራቱ የቅጣት ምት እና 54ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉጌታ ወርሃነ ከርቀት ባደረገው ሙከራ ሁለት ጊዜ ኢላማቸውን ቢጠብቁም የሰለሞን አረጋውን መረብ መድፈር ግን አልተቻላቸውም። ደሴዎች እየተወሰደባቸው የነበረው ብልጫ ጫና ውስጥ እየከተታቸው ሲሄድ ቢታይም አንጋፋውን አማካይ ዳንኤል አያሌውን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ግን ጥሩ የሚባሉ የማጥቃት ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በተለይ 70ኛው ደቂቃ ላይ ተስፉ ወሰን ከዳንኤል ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። ቡድኑ ጥረቱን ቀጥሎም 77ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረን ኳስ በመጠቀም ቢኒያም ጌታቸው በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታውን አሸንፎ መውጣት ችሏል። ደሴዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሙሉ ለሙሉ አፈግፍገው ለመጫወት አለማሰባቸው የአክሱሞችን ጫና እንዲቆጣጠሩ ረድቷቸዋም ታይቷል። ሆኖም አክሱሞች በጭማሪ ደቂቃ የደሴው የመሀል ተከላካይ ዓለማየው ግርማ በእጁ በነካው ኳስ ምክንያት የፍፁም ቅጣት ምት ዕድል ሊያገኙ ቢችሉም የክፍሎም ሀጎስ ምት በግቡ ቋሚ ተመልሶበት አቻ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።


ፌደራል ፖሊስ 1-0 ለገጣፎ

(በዳንኤል መስፍን)

በኦሜድላ ሜዳ በተደረገው ይህ ጨዋታ ለገጣፎዎች ኳሱን በሚገባ አደራጅተው በሁሉም የሜዳ ክፍል ወደ ጎል በመሄድ የተሻሉ በመሆናቸው የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው የነበረ ቢሆንም ያገኙትን አጋጣሚዎች አለመጠቀማቸው ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ለገጣፎዎች በራሳቸው በሚፈጥሩት ስህተት የሚያገኙትን ነፃ የሜዳ ክፍል በመጠቀም ረገድ ደግሞ ፌደራል ፖሊሶች ቀላል የማይባሉ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቆ ከእረፍት መልስ በጣለው ከበድ ያለ ዝናብ ሜዳው በመጨቀይቱ ምክንያት የለገጣፎዎችን ኳስ ተቆጣጥሮ የመጫወት የጨዋታ እቅድ ያበላሸባቸው ሲሆን ፌደራሎች የተሻለ ጉልበት ያላቸው በመሆኑ በዚህ ተጠቅሚ መሆን ችለው ነበር ። ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቀቀ ተብሎ የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ቢራ ከግራ መስመር ወደ ቀኝ ሰብሮ ሰው ቀንሶ ወደ ሳጥን በመግባት ባስቆጠረው ግሩም ጎል ፌደራል ፓሊስ አሸንፎ ወጥቷል።


ተስተካካይ ጨዋታ

ሱሉሉታ ከተማ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት አዳማ ላይ ባደረገው ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ የ3-0 ሽንፈት ደርሶበታል። ቡድኖቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በ35ኛው እና 41ኛው ደቂቃ ፍቃዱ አለሙ እና ዳዊት ማሞ ባስቆጠሯቸው ግቦች ወደ እረፍት ሲያመሩ በሁለተኛው አጋማሽ ፍቃዱ አለሙ ለራሱ ሁለተኛ እና ለቡድኑ ሶስተኛ የሆነች ግብ አስቆጥሮ የመዲናዋን ቡድን አሸናፊነት አረጋግጧል። ውጤቱ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን ወደ 26 ከፍ አድርጎ ወደ ሁለተኛነት እንዲመለስ አግዞታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *