ወላይታ ድቻ በአዲስ አበባ አቀባበል ተደርጎለታል

የግብፁን ሃያል ክለብ በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ከውድድሩ ውጪ ያደረገ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ክለብ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ አድናቆት እየተቸረው የሚገኘው ወላይታ ድቻ ቡድን አባላት ዛሬ ንጋት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ አለማቀፍ ኤርፖርት በተለያዩ የክብር እንግዶች በተገኙበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ሆቴል እስኪደርሱ ድረስ በየመንገዱ ከህዝቡ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

03:45 ላይ ኢትዮጵያ ሆቴል የደረሱት ወላይታ ድቻዎች በዕለቱ የክብር እንግዶች አማካኝነት የአበባ ጉንጉን የተበረከተላቸው ሲሆን የዕለቱ የክብር እንግዶች እና የተለያዩ ተቋማት ሀላፊዎች በየተራ ንግግር አድርገዋል። ባስተላለፉት መልዕክትም ወላይታ ድቻ የግብፁ ዛማሌክን ከውድድር በማስወጣት የመጀመርያ ሆኖ ታሪክ መስራቱ ድሉን ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀው በቀጣይ ከክለቡ ጋር ያላቸውን አብሮነት ከማበረታቻ ጋር ገልፀዋል። በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ አርማ ያለበት ትጥቅ እና የ150,000 ሺህ ብር ቼክ እንዲሁም የወላይታ ሶዶ ተወላጆች የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደግሞ 350,000 ሺህ ብር ስጦታ አበርክተዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ሙስጠፋ የተባሉ ግለሰብም እንዲሁ 150,000 ብር ሰጥተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ባደረገው ንግግር ለአቀባበሉ እና ሽልማቱ ምስጋናውን አቅርቦ “ይህ ውጤት የልፋታችን ውጤት ነው። ሆኖም ጀመርን እንጂ አልጨረስንም። በዚሁ ውጤት የምንዘናጋም አይሆንም። ብዙ መንገድ ይቀረናል። ከአሁን ጀምሮ ብዙ ስራ ስለሚጠብቀን ከጎናችን መሆናችሁን ስለገለፃችሁልን እናመሰግናለን። ግብፅ ላይ ተጨዋቾቼ ብዙ ተጋድሎ አድርገዋል። የወላይታ እና የኢትዮጵያን ስምም አስጠርተዋል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ተስፋ እንዳለው ያመለከተ እና ሌሎች ክለቦች እኛ የደረስንበት እንዲሁም ከእኛም በላይ መሄድ እንደሚችሉ ያሳየንበት ውጤት ነው። አሁንም ጠንክረን ከዚህ በላይ ውጤት ለማምጣት እንሰራለን።” ብሏል።

በቀጣይ ክለቡ ረፋድ ላይ በቀጥታ ወደ ሀዋሳ ከተማ የሚያቀና ሲሆን እዛ በተዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካፍሎ ነገ ወደ ወላይታ ሶዶ እንደሚያመራ ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *