የኢትዮጵያ ክለቦች በኮንፌድሬሽን ዋንጫው እነማንን ሊያገኙ ይችላሉ?

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ከሚያዘጋጃቸው የክለብ ውድድሮች መካከል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ አንዱ ነው፡፡ በፈረንሳዩ ግዙፍ ድርጅት ቶታል ስፖንሰር የሚደረገው እና በአህጉሪቱ ሁለተኛው የክለቦች ውድድር የሆነው ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ሲደረግ ይህ ለ15ኛ ግዜ ነው፡፡ በ1992 የካፍ ዋንጫ በሚል ስያሜ የተጀመረው ውድድር በ2004 የአፍሪካ አሸናፊዎች ዋንቻ (አፍሪካን ካፕ ዊነርስ ካፕ) ጋር በመደባለቅ ነበር ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በሚል ስያሜ የተጀመረው፡፡

በዘንድሮው የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምድብ ለመግባት ሁለቱ የኢትዮጵያ ክለቦች ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ምሽት ካይሮ በሚገኘው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በሚወጣው ድልድል ተጋጣሚዎቻቸውን ያውቃሉ፡፡ በትላንትናው እለትም ካፍ የቋት ድልድሉን ይፋ ያደረገ ሲሆን ፈረሰኞቹ በቋት 1 እንዲሁም የጦና ንቦቹ ቋት 4 ላይ መገኘታቸው እርስበእርስ የመጫወት እድልም እንዲፈጥርላቸው ሆኗል፡፡ ሁለቱም ክለቦች እርስበእርስ የሚገናኙ ከሆነ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር የኢትዮጵያ ክለቦች ሲገናኙ የመጀመሪያ ግዜ ይሆናል፡፡ እኛም ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያገኟቸው ከሚችሏቸው ክለቦች መካከል ጠንካራ የሚባሉት አቅርበናል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ሊሆኑ የሚችሉ ክለቦች

ወላይታ ድቻ (ኢትዮጵያ)፣ ራጃ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ)፣ ፎሳ ጁኒየር (ማዳጋስካር)፣ ዲፖርቲቮ ኒፋንግ (ኤኳቶሪያል ጊኒ)፣ አል መስሪ (ግብፅ)፣ ጆሊባ ኤሲ (ማሊ)፣ ሬኔሳንስ በርካን (ሞሮኮ)፣ ኮስታ ዶ ሶል (ሞዛምቢክ)፣ አክዋ ዩናይትድ (ናይጄሪያ)፣ ካራ ብራዛቪል (ኮንጎ ሪፐብሊክ)፣ ላ ማንቻ (ኮንጎ ሪፐብሊክ)፣ ሲአር ቤሎዝዳድ (አልጄሪያ)

ፈረሰኞቹ ከቻምፒየንስ ሊጉ በኬሲሲኤ ተሸንፈው ከወረዱ በኃላ ወደ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምድብ መግባት የሚችሉ ከሆነ ደካማ የውድድር ዘመናቸውን የማስተካከል እድል እንደሚያገኙ ይታመናል፡፡ ሆኖም ወደ ምድብ ለመግባት ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ክለቦች መካከልም ጠንካራ የምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ ክለቦች መገኘታቸው ጉዞው ቀላል እንደማይሆን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ራጃ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)

በሞሮኮ እግርኳስ የክለቦች ውድድር ስመ ገናና የሆነው ራጃ ካዛብላንካ የከተማ ተቀናቃኙ እና የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ዋይዳድ መዳከምን ተክተሎ በሊጉ ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር ከኢትሃድ ታንገ እና ሁስ አጋድር ጋር ለቦቶላ ሊግ ቻምፒዮንነት እየተፎካከረ ይገኛል፡፡ ሞሮኳዊው አጥቂ ሙሴን ላሆርም በጥሩ ብቃት ላይ እያደረገ ሲሆን በ14 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡ ራጃ ከአመታት በኃላ ወደ አህጉሪቱ የክለቦች ውድድር የተመለሰ ሲሆን በውድድሩም ላይ ወደ ምድብ የማምራት አቅም እንዳላቸው ከሚታመኑ ክለቦች መካከል ነው፡፡

ሬኔሳንስ በርካን (ሞሮኮ)

በቦቶላ ሊግ 8ተኛ ደረጃን ይዞ ቢገኝም በሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ፋውዚ ሌካ የሚመራው የበርካን ክለብ በኮንፌድሬሽን ዋንጫው የቱኒዚያውን ሃያል ክለብ ክለብ አፍሪካን በአጠቃላይ ውጤት 4-1 በማሸነፍ ወደ መጨረሻው ዙር ማለፉ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የበርካን ጥንካሬ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ናቸው፡፡ በሞሮኮ ተዘጋጅቶ በነበረው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው አዩብ ኤል ካቢ እና ቶጎዋዊ ኢንተርናሽናል ፎዶ ላባ ለቡድኑ ግብ አምራች ናቸው፡፡ ወደ ዓለም ዋንጫ የመጓዝ እድሉ የሰፋ የሚመስለው ኤል ካቢ በግቦቹ በርካንን ለመጨረሻ ግብ አብቅቷል፡፡

ካራ ብራዛቪል (ኮንጎ ሪፐብሊክ)

በኮንጎ ብራዛቪል የክለቦች ውድድር ጠንካራ ፉክክር የሚያሳየው እና ለአፍሪካ የክለቦች ውድድር አዲስ ያለሆነው ክለብ ካራ ነው፡፡ ካራ ብራዛቪል በ1997 ቅዱስ ጊዮርጊስን በቻምፒየንስ ሊጉ የመግጠም እድል አግኝቶ 2-1 በአጠቃላይ ውጤት ማሸነፍ መቻሉ ይታወቃል፡፡ ካራ የመጨረሻ ማጣሪያ ላይ ለመድረስ የቱኒዚያውን ቤንጎርዳን እና የጋናው አሻንቲ ኮቶኮን አሸንፏል፡፡ በሜዳው ባደረጋቸው የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎችም እስካሁን አልተሸነፈም ሆኖም ከሜዳው ውጪ ሽንፈቶችን ቀምሷል፡፡

አል መስሪ (ግብፅ)

የፖር ሳዒድ ክለብ የሆነው አል መስሪ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች እያሉት 4ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በቀድሞ የፈርኦኖቹ ኮከብ ሆሳም ሀሰን የሚሰለጥነው መስሪ በሜዳው ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡ በቅርብ አመታትም መስሪ ከሊጉ ሃያሎች ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ባይችል እንኳን እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በማድረግ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው ክለቡ ከቀናት በፊት ለአሰልጣኝ ሀሰን እና መንታ ወንድሙ ኢብራሂም ሀሰን የውል ማራዘሚያ የፈፀመው፡፡
የአልጄሪያ ዋንጫ አሸናፊው ቤሎዝዳድ በሊግ 1 ደካማ ጉዞ እያደረገ ይገኛል ሆኖም ጠንካራ ተጋጣሚ ነው፡፡ የሞዛምቢኩ ኮስታ ዶ ሶል ኬፕ ታውን ሲቲን ከሜዳው ውጪ አሸንፎ ነው የመጣው፡፡

የወላይታ ድቻ ተጋጣሚ ሊሆኑ የሚችሉ ክለቦች 

ቅዱስ ጊዮርጊስ (ኢትዮጵያ)፣ አል ሂላል (ሱዳን)፣ ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ዛናኮ (ዛምቢያ)፣ አሴክ ሚሞሳ (ኮትዲቯር)፣ ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ)፣ ጎር ማሂያ (ኬንያ)፣ ዊልያምስቪል (ኮትዲቯር)፣ ዩዲ ሶንጎ (ሞዛምቢክ)፣ ማውንቴን ኦፍ ፋየር ሚኒስትሪ (ናይጄሪያ)፣ አዱና ስታርስ (ጋና)፣ ቤድቬስት ዊትስ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን)፣ ጄኔሬሽን ፉት (ሴኔጋል)፣ ፕሌቶ ዩናይትድ (ናይጄሪያ)፣ ራዮን ስፖርት (ሩዋንዳ)

የጦና ንቦቹ የሳምንቱ መነጋገሪያ የሆነ ድል የአምስት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ዛማሌክ ላይ ካስመዘገቡ በኃላ ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ትኩረትን ስበዋል፡፡ ወላይታ ድቻ ዚማሞቶን ሀዋሳ ላይ ያሸነፈበት መንገድ አሳማኝ ባይሆንም ዛማሌክን በመለያ ምት በማሸነፍ ከውድድር ያስወጣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክለብ ሆኗል፡፡ ክለቡ ከቀናት በፊት ያሳካውን ድል ለማስቀጠል እና ወደ ምድብ ለማምራት ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ ለድቻ ትልቁ ዜና የሚሆነው ደግሞ በዚህ ዙር የሚገኙ አምስት የሰሜን አፍሪካ ክለቦችን በድልድሉ አለማግኘቱ ነው፡፡

አል ሂላል (ሱዳን)

የኦምዱሩማኑ ክለብ ከቻምፒየንስ ሊግ በቶጎው ፖርት ቶጎ መሰናበቱ ለደጋፊዎቹ የሚዋጥ አልሆነም፡፡ ሂላል ለሴካፋ ዞን ክለቦች ምሳሌ በሚሆን መልኩ የእራሱ ስታዲየም፣ ሆቴል፣ ራዲዮ እና ቴሌቭዢን ጣቢያ ያለው ክለብ ነው፡፡ ሂላል በተደጋጋሚ በቻምፒየንስ ሊጉም ሆነ ኮንፌድሬሽን ዋንጫው ምድብ መጓዙ ከፍተኛ ልምድ እንዲያካብት አስችሎታል፡፡

ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)

የኪንሻሳው ክለብ በፋይናንስ አቅሙ ከፈረጠመው ቲፒ ማዜምቤ ጋር የሚገዳደር ቡድን እየሰራ ለዓመታት የኮንጎ የክለቦች ውድድር ላይ መንገስ ችሏል፡፡ ቪታ እንደሂላል ሁሉ ወደ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ማምራት ሳይችል ቀርቷል፡፡ በፎሎሮ ኢቤንጌ የሚሰለጥነው ቪታ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለመርታት አስቸጋሪ ነው፡፡

ጄኔሬሽን ፉት (ሴኔጋል)

የሴኔጋሉ የእግርኳስ አካዳሚ ክለብ ጄኔሬሽን ፉት የሰኔጋልን ሊግ እየመራ ይገኛል፡፡ ክለቡ በቻምፒየንስ ሊጉ ልምድ ባይኖረውም የግብፁን ምስር ኤል ማቃሳን ከውድድር አስወጥቷል፡፡ በወጣቶች የተገነባ ቡድን ያለው ክለቡ ከቻምፒየንስ ሊጉ በሆሮያ ተሸንፎ ነበር ከውድድር ውጪ የሆነው፡፡

በቻምፒየንስ ሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳናቸው እንደዛናኮ፣ አሴክ ሚሞሳ እና ቤድቬስት ዊትስ የድቻ ተጋጣሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ከምስራቅ አፍሪካ እንደጎር ማሂያ፣ ያንግ አፍሪካንስ እና ራዮን ስፖርትም ያለት ክለቦችም በእጣ ድልድሉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የቻምፒየንስ ሊጉ የምድብ ድልድል እና የኮንፌድሬሽን ዋንጫው የመጨረሻ ማጣሪያ ዙር ድልድል ምሽት 12፡00 ሲካሄድ በቤን ስፖርትስ የዜና ጣቢያ እና ሱፐርስፖርት 4 ላይ ቀጥታ የቴሌቭዢን ስርጭት ያገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *