ጥቂት ነጥቦች በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ድልድል ዙርያ

የካፍ ኮንፌዴሬሽንስ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ድልድል ከደቂቃዎች በፊት በግብጽ መዲና ካይሮ ተካሂዶ ሁለቱ የኢትዮጵያ ክለቦች ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኮንጎ ሪፐብሊኩ ካራ ብራዛቪል ጋር ሲደለደል ወላይታ ድቻ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡ ጥቂት ነጥቦችም በሁለቱ ክለቦች ድልድል እና ተጋጣሚዎች ዙርያ እንመለከታለን፡፡

ያንጋ… 

ያንጋ በ1998 (እኤአ) ኢትዮጵያ ቡና የግብጹ አል አህሊን ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ጎል ልዩነት ከውድድር በማስወጣት እስካሁንም የሚታወስ ታሪክ ሰርቷል፡፡ ቀጥሎ የሆነው ግን ቡናማዎቹ ሁሌም ሊረሱት የሚመኙት ታሪክ ነው፡፡ በሁለተኛው ዙር ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር ሲደለደል አስቀድሞ ከጣለው የአፍሪካ ታላቅ ክለብ አንጻር እዚህ ግባ የማይባለው ያንጋን አሸንፎ ወደ ምድብ ድልድል እንደሚገባ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም በሜዳው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቶ ከሜዳው ውጪ 6-1 ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ 

በ2011 በሌላኛው የኢትዮጵያ ክለብ ደደቢት ተሸንፎ ከውድድር የወጣ ሲሆን አሁን ደግሞ በሌላኛው ኢትዮጵያዊ ክለብ በር ላይ ቆሟል፡፡ የአፍሪካ ሁለተኛው ታላቅ ክለብ የሆነው ዛማሌክን ከውድድር አስወጥቶ ሁለተኛው ዙር ላይ የተገኘው ወላይታ ድቻ ወደ ምድብ ለመግባት ያንጋን ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ወላይታ ድቻ የዛሬ 20 ዓመት የተከሰተውን የሚሽር ውጤት ያስመዘግባል? ወይስ ታሪክ ራሱን ይደግማል? በሀዋሳ እና ዳሬ ሰላም የሚደረጉ ጨዋታዎች መልስ ይሰጡናል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በድጋሚ ወደ ኮንጎ 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መካከለኛዋ አፍሪካ ሀገር ለተከታታይ አመት የሚጓዝ ይሆናል፡፡ አምና በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከሌላው የኮንጎ ክለብ ኤሲ ሊዮፓርድስ ጋር በመጀመርያው ዙር ተገናኝቶ ዶሊሴ ላይ በምንተስኖት አዳነ ጎል 1-0 ሲያሸንፍ አዲስ አበባ ላይ በሳላዲን ሰዒድ ጎሎች 2-0 በመርታት በድምር የ3-0 ውጤት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የምድብ ድልድሉን ተቀላቅሏል፡፡ አሁንም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት ሌላው የኮብጎ ሪፐብሊክ ክለብ ካራ ብራዛቪልን ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡

ፈረሰኞቹ ከ11 ዓመት በፊት (2007 እኤአ) ከሌላው የኮንጎ ክለብ ኤቷል ዱ ኮንጎ ጋር በቻምፒየስ ሊግ የመጀመርያ ዙር ተገናኝተው በድምር ውጤት 2-1 በመሸነፍ ከውድድር ውጪ ሆነው ነበር፡፡ በመጀመርያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ በናይጄርያዊው አጥቂ ኡቼ ቹኩ ጎል 1-0 አሸንፈው ወደ ብራዛቪል ቢያመሩም 2-0 ተሸንፈው ከውድድር ወጥተዋል፡፡ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮንጎ መጉላላት ደርሶበት እንደነበር መግለጹ ይታወሳል፡፡

ሁለት የኢትዮጵያ ክለቦች በሁለተኛው ዙር

የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ታሪክ በሁለተኛው ዙር ሁለት የኢትዮጵያ ክለቦች ሲገኙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ወደ ምድብ ድልድሉ ከተጓዙም ሌላ አዲስ ታሪክ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡ በ2013 (እኤአ) ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚሁ ዙር የግብፁ ኤንፒን በመርታት ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ምድብ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡  

ጉዞ ወደ ምድብ

ፈረሰኞቹ እና የጦና ንቦች ተጋጣሚዎቻቸውን መርታት ከቻሉ ወደ ምድብ ከመግባታቸው ባሻገር የኢትዮጵያ ክለቦች በካፍ ያላቸውን ነጥብ የሚያሳድግ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ክለቦች ባለፉት 5 አመታት በሰበሰቡት ነጥብ ከአፍሪካ 18ኛ ደረጃ በመገኘት አንድ ተጨማሪ ክለብ ከሚያሳትፈው ደረጃ በ11 ነጥብ የራቁ ሲሆን የሁለቱ ወደ ምድብ መግባት ደረጃዋን የሚያሻሽል እና አንድ ተጨማሪ ክለብ የማሳተፍ እድልን ለማግኘት ተስፋዋን የሚያለመልምላት ይሆናል፡፡ በ2004 በተደረገው ማሻሻያ ኢትዮጵያ የተወካዮቿ ብዛት ከሶስት ወደ ሁለት ዝቅ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *