የፋሲል ከተማ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ሊያገኙ ነው

ፋሲል ከተማ በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲያገኙ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ውል መፈፀሙን ታውቋል፡፡

የቴሌዚዥን ስርጭት መብቱ የተፈፀመው በሶስት አካላት ሲሆን የፕሮዳክሽን ስራዎችን የሚሰራው ኤቢ ኤቭንት ኦርጋናዚንግ ፣ ፋሲል ከተማ እና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በገንዘብ ክፍፍሉ እና ህጋዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት በመድረሳቸው ፋሰል ከተማ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ከተጋጣሚ ክለቦች ጋር በስምምነት የማስተላለፍ ውል ተፈራርመዋል፡፡

የኤቢ ኤቭንት ኦርጋናይዚንግ ስራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት በስምምነቱ መሰረት ከትርፉ ላይ ፋሲል ከተማ ግማሽ ሲያገኝ  ኤቢ ኤቭንት ኦርጋናዚንግ 25 በመቶውን የሚወስድ ይሆናል፡፡ ተጋጣሚው ክለብ ደግሞ ቀሪውን 25 በመቶ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የሚኖረውን ሁኔታም በባለሜዳዎቹ ክለቦች ፈቃደንነት እና ስምምነት እንደሚከናወን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

ፋሲል ከተማ የሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽን ከወልዋሎ ጋር አዲስ አበባ ስታድየም በሚያርገው ጨዋታ የሚጀምር ሲሆን ስምምነቱ በታቀደው መሰረት ከተጓዘ በዋልታ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የሚያገኝ ይሆናል፡፡

ወጥ የሆነ የጨዋታ ብሮድካስቲንግ አሰራር እና ጉዳዩን በበላይነት የሚቆጣጠር አካል የሌለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዘንድሮው አመት በርከት ያሉ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ቀጥታ ስርጭት ሽፋኖች እየተሰጠው ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *