ሪፖርት | ፋሲል ከተማ ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምሯል

8 ሰዐት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በተጀመረው የሊጉ ሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ወልዋሎ ዓ.ዩን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ሁለቱም ቡድኖች በ15ኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች በርከት ያሉ ለውጦችን አድርገዋል። ፋሲል  አርባምንጭን ከረታበት ጨዋታ ከረጅም ጊዜ በኃላ ከጉዳት የተመለሰው ያሬድ ባየህን መሀል ተከላካይ ቦታ ላይ በማስገባት ሰይድ ሁሴንን በፍፁም ከበደ ተይዞ ወደ ነበረው የግራ መስመር ተከላካይ ቦታው ወስዶታል። አማካይ መስመር ላይ ሔኖክ ገምቴሳ በኤፍሬም አለሙ ከፊት ደግሞ ናትናኤል ጋንቹላ በአብዱርሀማን ሙባረክ ሌሎች ቡድኑ ያደረጋቸው ቅያሪዎች ነበሩ። ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በተጠራው በረከት አማረ ምትክ ዘውዱ መስፍንን በግብ ጠባቂነት ያስገቡት ወልዋሎዎች ፊት መስመራቸው ላይ በቢንያም አየለ እና ሳምሶን ተካ ቦታ ከጉዳት የተመለሱትን ሙሉአለም ጥላሁን እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆን ተጠቅመዋል። በድሬደዋው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው ብርሀኑ አሻሞ ምትክ ደግሞ አሳሪ አልማሃዲ በተከላካይ አማካይነት ሲሰለፍ አዲሱ ፈራሚ አለምነህ ግርማን የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ተጫውቷል።

ጨዋታው ግብ ያስተናገደው በተጀመረ ገና በሁለተኛው ደቂቃ ነበር። በፈጣን ማጥቃት ጨዋታውን የጀመሩት ፋሲሎች በመሀመድ ናስር አማካይነት ከሳጥን ውስጥ ያደረጉትን ሙከራ የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን ካዳነ በኃላ በመወርወር ጨዋታ ለማስጀመር ሲሞክር ኳሷን ወደ ራሱ መረብ ልኳት ለፋሲል ከተማ እንድትቆጠር ሆኗል። በዚህ መልኩ መሪ የሆኑት አፄዎቹ በጀመሩበት ፍጥነት ጨዋታውን ቀጥለው ወልዋሎዎች ለመቀባበል የሚሞክሯቸውን ኳሶች ከራሳቸው ሜዳ ጀምሮ ለማስጣል በመሞከር በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመጠጋት ሙከራ ሲያደርጉ ይታዩ ነበር። ሆኖም ከአስረኛው ደቂቃ በኃላ ነገሮች እንዳጀማመራቸው አልቀጠሉም። በሂደት ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ወልዋሎዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ኳስ በሚይዙበት የሜዳ ክፍል ላይ ተጠጋግቶ በሚጫወተው የአማካይ ክፍላቸው ጫና መፍጠር ጀመሩ።

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በተሰለፈበት የግራ መስመር ያደላው ማጥቃታቸውም ቀስ በቀስ ወደ ሙከራዎች መለወጥ ጀምሯል። ከዚህም መካከል 16ኛው ደቂቃ ላይ ወደኃላ እያጠበበ ለአማካይ መስመሩ የቁጥር ብልጫን ሲፈጥር የነበረው ፕሪንስ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የሰነጠቃት እና ከድር ሳሊህ ከቅርብ ርቀት የሳታት ኳስ ተጠቃሽ ናት። 26ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አለምነህ ግርማ መሬት ለመሬት ከርቀት የመታትን የቅጣት ምት አሳሪ አልመሃዲ ሳይደርስባት ቀርቷል። 28ኛው እና 30ኛው ደቂቃ ላይም የቡድኑን ማጥቃት በዋና ተዋናይነት ይመራ የነበረው ፕሪንስ ያደረጋቸው ሙከራዎችም ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ ተጨዋቹ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ የሞከራት ኳስ በሳሜኬ ጥረት ጎል ከመሆን የዳነች ነበረች። ጫና በተፈጠረባቸው በነዚህ ደቂቃዎች በአመዛኙ በራሳቸው አጋማሽ ላይ ለመቅረት ተገደው የነበሩት ፋሲሎች ኳስ በሚቀሙባቸው አጋጣሚዎች ለወትሮው የሚታወቁበትን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለማድረግ በሚሞክሩባቸው ሰዐታት ይሰሩ የነበረው ይቅብብል ስህተት ከመጀመሪያው ደቂቃ የመሀመድ ናስር ሙከራ በኃላ የጠራ የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። የወልዋሎዎችም ብልጫ ቢሆን በመጨረሻዎቹ አስር የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች እየተቀዛቀዘ ሄዶ ቡድኖቹ በአፄዎቹ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያው ከተጠናቀቀበት ብዙም ባልተለየ መልኩ የተጀመረ ነበር። ወልዋሎዎች አሁንም ብዙ የኳስ ንክኪ በማድረግ እና ተጠጋግተው በመጫወት ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ሁለቱን መስመሮቻቸውን ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በረጅሙ የመታትን ቅጣት ምት ሳማኬ ለመያዝ ሲሞክር አንሸራቶት ኳስ ሊያመልጠው ቢቃረብም እንደምንም ያዳነበት አጋጣሚም ለቡድኑ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ወልዋሎዎች ከስምንት ደቂቃ በኃላም ክፍት ሆኖ ባገኙት የፋሲል ሳጥን ውስጥ በሙሉአለም ጥላሁን እና ከድር ስሳሊህ ጥሩ ቅብብል ለፕሪንስ አጋጣሚ ቢፈጥሩም ፕሪንስ ኳሷ ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተረጋግተው በራሳቸው ሜዳ ኳስን በመያዝ የጨዋታውን ፍጥነት ማቀዝቀዝ የቻሉት ፋሲሎች በመልሶ ማጥቃት በሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ቢታዩም ሙከራዎችን ማድረጋቸው ግን አልቀረም። 62ኛው ደቂቃ ላይ ከአምሳልሉ ጥላሁን ቅጣት ምት ያሬድ ባየህ በግንባሩ የሞከረው እና ኢላማውን ያልጠበቀው ኳስ እንዲሁም የዘውዱን መውጣት ተመልክቶ መሀመድ ናስር ወደ ግብ ሞክሮት ወደ ላይ የተነሳው ኳስ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበሩ።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍጥነታቸው የቀነሰው ወልዋሎዎች የጨዋታው መገባደጃ እስኪደርስ ድረስ ባሉት ደቂቃዎች ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ዋነኛ የማጥቃት አማራጫቸው የነበረው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በፋሲሎች በቅርብ ርቀት ክትትል ውስጥ መግባቱ እና በሌላኛው መስመር ከእንየው ካሳሁን ይጀምር የነበረው ጥቃታቸው ደሞ የፋሲል ከተማው ሀሚዝ ኪዛ ከገባ በኃላ በነበረው ጥንካሬ አለመቀጠሉ ለዚህ ምክንያት ነበር። ፋሲሎች ከኤርሚያስ ኃይሉ አጥተውት የነበረውን የሜዳውን ስፋት የመጠቀም እና የተጋጣሚን የመስመር ተከላካይ የማፈን ሚና ከሀሚዝ ካገኙ በኃላ ጨዋታው እምብዛም አልከበዳቸውም ነበር። አልፎ አልፎ በረጅሙ በሚጣሉ  ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ መሞከራቸውም አልቀረም። ሆኖም ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ መሀመድ ናስርን አስወጥተው ሰንደይ ሙቱኩን በማስገባት የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ማብዛታቸው ፊት ላይ ይፈጥሩት የነበረውን ጫና ስለቀነሰው በጥልቀት ወደ ግባቸው ለማፈግፈግ ተገደው ነበር። ያም ቢሆን የተሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች ተቋቁመው ጨዋታውን ፈፅመዋል። ፋሲሎች ያሳኩት ሶስት ነጥብ ነጥባቸውን 25 አድርሶት ወደ አምስተኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ወልዋሎ ዓ.ዩ ወደ 13ኝነት ዝቅ ብሏል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

ባሰብነው እና በፈለግነው መንገድ አልተጫወትንም። ሆኖም ዋናውን ነገር አሳክተናል። አሸንፈን ሶስት ነጥብ ይዘናል። ነገር ግን ቡድኑ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እንደሚሻሻል አስባለው። የመጀመሪያው ዙር ላይ በወልዋሎው ጨዋታ በጣም ተበልጠን ነበር። ከዛ ትምህርት ወስደን ጠንካራ ቡድን ይዘን በመግባት የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረናል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ጨዋታ ላይ ቡድናችን ከዚህ በላይ ይሻሻላል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወልዋሎ ዓ.ዩ

የሁለተኛውን ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ነው የተሸነፍነው። ከሽንፈታችን ተምረን ለቀጣይ ጨዋታዎች መማር እና በእያንዳንዱ ጨዋታ ነጥብ መሰብሰብ ይኖርብናል። የገባብን ጎልም በተጋጣሚያችን ጥንካሬ ሳይሆን በግል ስህተት የተቆጠረ ነው። ወደ ጨዋታው መንፈስ ከመግባታችን በፊት መቆጠሩ አስቸጋሪ አድርጎብን ነበር።  ሆኖም ከዛ በኃላ አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል። ያው እንግዲህ አልተሳካልንም ውጤቱንም በፀጋ ተቀብለናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *