ሪፖርት | መቐለ ከተማ በኦፖንግ ሐት-ትሪክ ታግዞ ከመሪው ያለውን ልዩነት አጥብቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታ በሜዳው ትግራይ ስታድየም አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው መቐለ ከተማ በጋናውያን ተጨዋቾቹ ግቦች ታግዞ 4-0 ማሸነፍ ችሏል:: የባለሜዳዎቹ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እና የእንግዶቹ የመከላከል ድክመት በጉልህ የታየበት ጨዋታ ሆኖም አልፏል፡፡

የጨዋታው የመጀመሪያ ፊሽካ ከተበሰረበት ደቂቃ አንስቶ በፈጣን እንቅስቃሴ የአርባምንጭ ተከላካይ መስመር መፈተሽ የጀመሩት መቐለ ከተማዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የፈጠሩት ጫና ሰምሮላቸው በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ጋናዊው አጥቂ ቢስማርክ ኦፖንግ በአደጋ ክልሉ ውስጥ መቶ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡ አማኑኤል ገብረሚካኤል በአዞዎቹ የተከላካይ ክፍል መሃል አሾልኮ የላከለትን ኳስ አፖንግ በአግባቡ ተጠቅሞ ነበር መቐለዎች መሪ መሆን የቻሉት፡፡ መቐለ ከተማ በሁለቱ የመስመር አጥቂዋች አማኑኤል እና ቢስማርክ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሜዳው ስፋት ለመጠቀም ሲሞክር በአንፃሩ አርባምንጮች ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ረጃጅም  ኳሶች የመቀለን ተከላካይ መስመር ሲፈትኑ ተስተውልዋል::

አርባምንጭ ከተማ በመሃል ሜዳው የጠበበ እና ከጎኑ ሰፊ ክፍተት የሚተው አጨዋወት ይዘው በመግባታቸው መቐለ በሁለቱም የመስመር አጥቂዎች አማካኝነት ብዙ የግብ እድል እንዲፈጥር አስችሎታል፡፡ በተለይም በ11ኛው ደቂቃ ላይ ሁለቱ ጋናውያን ናሁ ፉሳይኒ እና ቢስማርክ አንድ ሁለት ተቀባብለው ቢስማርክ ነፃ ለነበረው አማኑኤል አቀብሎት የአጥቂ አማካዩ ሞክሮ ጃክሰን ፊጣ በቀላሉ የያዘበት የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ በሚታዩ እንቅስቃሴዎች እና በዋነኝነት የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም የጎል እድሎች ሲፈጥሩ በነበሩት አርባምንጮች በኩል በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከተካልኝ ደጀኔ የተሸማውን የማዕዘን ምት አለልኝ ኣዘነ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነበር፡፡

በ20ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ ሚካኤል ደስታ በ2 ተጫዋቾች መሃል ያሾለከውን ኳስ አማኑኤል ተተቅሞ ቢሞክርም በአዞዎቹ ተከላካዮች ተመልሳለች፡፡ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ እና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ የቻሉት መቐለ ከተማዎች በ23ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የዝውውር መስኮት የሊባኖሱን ክለብ ሸባብ ኣል ሳህል ለቆ መቐለ ከተማን የተቀላቀለው አጥቂው ፉሴይኒ ኣክርሮ የመታውን ኳስ ጃክሰን ሲተፋው ከግቡ አቅራብያ የነበረው ቢስማርክ ኣግኝቶ ባስቆጠረው ግብ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል፡፡

 

ከግቡ መቆጠር በኃላ አርባምንጮች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ቢሆንም ወደ ግብነት ለመለወጥ ግን ተቸግረው ተስተውሏል፡፡ በመጀመርያው ኣጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ተጭነው የተጫወቱት አርባምንጮች በ41ኛው ደቂቃ ተካልኝ ያሻገረውን ኳስ ዘካርያስ ፍቅሬ በግንባሩ ገጭቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ የወጣባት እንዲሁም በ44ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት አለልኝ መትቶ ለጥቂት በግቢ ኣግዳሚ ጎን የወጣበት ኳስ ልዩነቱን ሊያጠቡባቸው የሚችሏቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ በጥቂት የግብ ሙከራዎች እና በዘገምተኛ የጨዋታ ፍጥነት ምክንያት እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሳቢ ኣልነበረም:: እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት መቐለ ከተማዎች በዚህ ክፍለ ጊዜም ጎሎች ለማስቆጠር አልተቸገሩም፡፡ በመልሶ ማጥቃት የተገኝው ኳስ አማኑኤል አመቻችቶ ያቀበለውን በእለቱ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቢስማርክ የአርባምንጭ ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተጠቅሞ ወደ ግብነት በመቀየር ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡ ጋናዊው አጥቂ በውድድር ዘመኑ ሐት-ትሪክ የሰራ 4ኛው ተጫዋች ለመሆም በቅቷል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ መቐለ ከተማዎች ወደ መከላከሉ ሲያመዝኑ አርባምንጮች በበኩላቸው የጨዋታ የበላይነት ወስደዋል፡፡ ሆኖም ባለሜዳዎቹን በግብ ፌሽታ ያሰከረች አራተኛ ግብ በጨዋታው ለጎሎች መቆጠር ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የዋለው አማኑኤል ለአዲሱ ፈራሚ ፉሴይኒ ለማቀበል ሲሞክር ከግብ ክልሉ ወጥቶ ኳስን ለማቀረቅ ያልተሳካ ጥረት ያደረገውን የአርባምንጩ የግብ ዘብ ጃክሰንን አልፋ ጋናዊው አጥቂ በመጀመሪያው ጨዋታ ኳስ እና መረብ እንዲገናኝ አስችሏል፡፡

በረከት አዲሱ ተቀይሮ ከገባበት ደቂቃ አንስቶ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያሳዩት አርባምንጮች ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡ በ81ኛው ደቂቃ በረከት ከረጅም ርቀት ሞክሮ ኳስ በግቡ አናት ለጥቂት የወጣችበት እንዲሁም አማካዩ አማኑኤል ጎበና ሳጥን ውስጥ ያገኝዉን እድል የመቐለ ተከላካዮች ጨርፈው አውጥተውበታል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ የተገኝው የመልሶ ማጥቃት ኣጋጣሚን ተጠቅሞ አዲሱ ፈራሚ እያሱ በቀለ ይዞ በመግባት ለያሬድ ከበደ ሰጥቶት ያሬድ በማስቆጠር ደስታቸውን ከገለፁ በኋላ የእለቱ ዳኛ ዳዊት አሳምነው እያሱ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በማለት ሳያፀድቁ ቀርተዋል፡፡

ጨዋታው በመቐለ ከተማ 4-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በያዝነው የውድድር ዓመት ወደ ሊጉ ያደገውና ጥቂት ግቦች አስተናግዶ በዛው መጠን ግብ ለማስቆጠር የሚቸገረው መቐለ ከተማ ከሁለት ጎል በላይ በሆነ ውጤት ለመጀመርያ ጊዜ በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 28 ከፍ አድርጓል፡፡ ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው ደደቢትም በአንድ ነጥብ አንሰው ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡

አስተያየቶች

የመቐለ የግብ ጠባቂ ኣሰልጣኝ ሚካኤል ሲሳይ

ጨዋታው ለኛ ጥሩ ነበር፡፡ ከጨዋታው በፊት እንዳደረግነው ዝግጅት ውጤቱ ይገባናል፡፡ ህ ውጤት ለቀጣይ ጨዋታዎች የሞራል ስንቅ ይሆነናል፡፡ ዘንድሮ የቡድናችን አላማ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ነው፡፡

አርባምንጭ ከተማ ምክትል አሰልጣኝ ማትዮስ ለማ

በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ሁለቱ ጎሎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች መቆጠራቸው ነገሮችን ከባድ አድርገውብናል፡፡ በተረፈ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፡፡ መቐለ ያገኛቸውን የመልሶ ማጥቃት እድሎች ተጠቅሞ አሸንፎን ወጥቷል፡፡ በቀጣይ በሜዳችን ከሲዳማ ቡና ጋር ላለብን ጨዋታ በሚገባ እንዘጋጃለን፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *