ከፍተኛ ሊግ | ደቡብ ፖሊስ ወደ መሪነቱ ተመልሷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ደቡብ ፖሊስ በዲላ ከተማ ለአንድ ሳምንት የተነጠቀውን መሪነት ሲያስመልስ ሀላባ ከተማ እና ሀምበሪቾም ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል አስመዝግበዋል። የከፍተኛ ሊጉ ችግር የሆነው ጉዳይ በዚህ ሳምንትም ተከስቶ አልፏል። 

ወደ ድሬዳዋ የተጓዘው ደቡብ ፖሊስ ድሬዳዋ ፖሊስን ገጥሞ 1-0 በማሸነፍ ካለፈው ሳምንት ሽንፈቱ አገግሟል። ከሜዳው ውጪ ሶስጥ ነጥብ ይዞ መመለስ የሚቸገረው ደቡብ ፖሊስን አሸናፊ ያደረገች ወሳኝ ጎል ያስቆጠረው ብርሀኑ በቀለ ነው። የደቡበ ፖሊስን ማሸነፍ እና የዲላን ነጥብ መጣል ተከትሎም የሀዋሳው ክለብ ምድቡን በ25 ነጥቦች እንዲመራ አስችሎታል።

ለረጅም ጊዜ የመራውን ሰንጠረዥ ለደቡብ ፖሊስ አስረክቦ ምድቡ መሪ የነበረውና ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ለደቡብ ፖሊስ አስረክቦ የነበረው ዲላ ከተማ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ መሪ መሆን ቢችልም ከሜዳው ውጪ ግርጌ ላይ በሚገኘው ነገሌ ቦረና ነጥብ በመጣሉ ሳይሳካ ቀርቷል። ጨዋታው የተጠናቀቀው ያለ ግብ ነበር።

ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀላባ ከተማ ወደ አናት የተጠጋበትን ድል በወልቂጤ ከተማ ላይ አስመዝግቧል። በሀላባ 2-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ በ39ኛው ደቂቃ ኄኖክ ተረፈ ፣ በ76ኛው ደቂቃ ደግሞ ናትናኤል ጌታሁን ጎሎችን አስቆጥረዋል። በተከታታይ ሳምንታት ጨዋታዎችን ማደረረግ ያልቻለው ወልቂጤ ከፊቱ 5 ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል።

ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾ ከተማ መቂ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል። ለረጅም ደቂቃዎች ካለ ግብ በዘለቀው ጨዋታ ፍፁም ደስይበለው በ86ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ሀምበሪቾን ሶስት ነጥቦች አስጨብጣለች።

ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከ ሻሸመኔ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሻሸመኔ ከተማዎች በ22ኛው ደቂቃ ይድነቃቸው ብርሀኑ እና በ65ኛው ደቂቃ በውብሸት ወንድማገኝ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሁለት ጊዜ መምራት ቢችሉም ወራቤ በ37ኛ ደቂቃ እና 76ኛ ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች አቻ ተለያይተዋል።

በእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሴሜንት ቤንች ማጂ ቡናን በመሐመድ አብደላ (44′) እና ዳዊት ተሾመ (88′) 2-0 አሸንፏል።

በትላንትናው እለት መካሄድ ከነበረባቸው ጨዋታዎች መካከል የካፋ ቡና እና ቡታጅራ ከተማ ጨዋታ ወደ ሰኞ ሲሸጋገር የጅማ አባ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ሀዲያዎች ተጫዋቾቼ ታመውብኛል በሚል ጨዋታው እንዲራዘም ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል። በከፍተኛ ሊጉ “ተጫዋቾች ታመዋል” በሚል ምከንያት በርካታ ጨዋታዎች ሳይደረጉ ወደ ሌላ ጊዜ ሲተላለፉ መመልከት የተለመደ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *