45 ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ቤሊንጋ ኤኖህ . . .

ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ አራት ዓመታት አልፈውታል፡፡ ለአዲስ አበባ ውሃ ሥራዎችና ለመቐለ ከተማ ተጫውቶ አሁን ደግሞ የወልዲያን ግብ በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ወልዲያን ከተቀላቀለ ወዲህ ለ78 ተከታታይ ጨዋታዎች መሰለፍ የቻለ ሲሆን ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ እና በሊጉም እንዲደላደል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።


ኤይሜ ማዳንዳ ቤሊንጋ 
ኤኖህ ለክለቡ 45 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በተከታታይ ካደረገ በኋላ በዚህ ሳምንት ወልዲያ ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ በተቀያሪ ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡ ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ስለወልዲያ ቆይታው፣ ያለረፍት ስለተጫወታቸው ጨዋታዎች፣ ስለወጥ አቋሙ እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጣቸውን መልሶች እነሆ።

45 ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ስለመጫወቱ

በርግጥ ከባድ ነው፤ ነገር ግን ይቻላል፡፡ እግር ኳስ ተጫዋች ስትሆን የሚጠበቁብህን ነገሮች ማድረግ ከቻልክ ይቻላል፡፡ እኔ ልምምዶቼን በአግባቡ እሠራለሁ፤ በሚገባ ዕረፍት አደርጋለው፡፡ ባለቤቴ ሊያ ተሾመ በሥራዬ ሁሉ ታግዘኛለች፤ ቤቴ ሰላም ነው፡፡ ሥራዬን በሚገባ ስለማውቅ የማስጠንቀቂያ ካርድም አልነበረብኝም፡፡ በጸሎት አምናለው፡፡ ሁልጊዜ እጸልያለው፤ አምላኬ ነው ከጉዳት የሚጠብቀኝ፡፡ በኔም ብርታት ብቻ ሳይሆን በአምላኬም ጥበቃ ነው ይህንን ማድረግ የቻልኩት፡፡

ከረጅም ጊዘ በኋላ ተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ

በአጠቃላይ ከወልዲያ ጋር ያለ እረፍት 78 ጨዋታ ነው ያረግኩት፤ ከከፍተኛ ሊግ ወደፕሪምየር ባደግንበት ዓመት ሙሉ በሙሉ የወልዲያን ግብ የጠበቁት እኔ ነኝ፤ በተጨማሪ አምና የጥሎ ማለፉን ሶስት ጨዋታዎችም እኔ ነኝ ተጫወትኩት እነዚህ ሁሉ ከተቆጠሩ ጨዋታዎቹ ወደ 78 ያድጋሉ፤ በዚህ ሳምንት ላልከኝ ደግሞ እኔ ጉዳት አልነበረብኝም የአሰልጣኝ ውሳኔ ነው፡፡

ስለ ዘንድሮው የወልዲያ የተከላካይ መስመር መዳከም

እውነት ነው ዓምና ጥሩ የመከላከል አቅም ነበረን፤ ከኔ ፊት ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ነበሩ፤ በጣም እንግባባ ነበር፡፡ እኔ ሳጠፋ ያርሙኛል፤ እነሱ ሲያጠፉ እኔ የነሱን ስህተት አርማለው። በጣም እንግባባ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን አዲስ ቡድን ነው ብዙ አዳዲስ ተጫዋቾች መጥተዋል ፤ለመግባባት ጊዜ ያስፈልገን ነበር። አሁን ግን እየተዋወቅን ነው ፤ በቅርብ የሚቀረፍ ችግር ነው፡፡

ስለ ሀገራችን ግብ ጠባቂዎች

በጣም ብቃት ያላቸው የሃገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች አሉ፤ ችግሩ በራስ መተማመን ይመስለኛል፡፡ የውጭ ግብ ጠባቂዎችን የሚያስንቅ አቅም ያላቸው አሉ። ራሳቸውን በትልቅ ተጫዋች ደረጃ የማየት፣ በራስ የመተማመን እና የትኩረት ችግር ካልሆነ በቀር፡፡


የግብ ጠባቂ ሥልጠና

እዚህ በጣም ጥሩ ስልጠና ነው ያለው። እኔ እዚ ከመጣው አራት አመታት አልፎኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች፣ በመቐለ ከተማ እና በወልዲያ የገጠሙኝ ሁሉ ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ወልዲያ ውስጥ ጥሩ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ነው ያለኝ፤ የሚለኝን ሁሉ በሚገባ እፈጽማለው። በደንብ እንግባባለን፤ በአሰልጣኑም በስልጠናውም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ስለእቅዶቹ

ብዙ ያልተጫወትናቸው ጨዋታዎች ነበሩን፤ አርፍደን ነው የተጫወትናቸው። አሸንፈን ወደሰንጠረዡ አማካይ መጥተናል። አሁንም ብዙ ነጥብ መሰብሰብ ያስፈልገናል። ብዙ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልገን ለቡድን አጋሮቼ መግለፅ እፈልጋለው። ለወልዲያ ደጋፊዎችም አሁንም ደግፉን ማለት እፈልጋለው፡፡ የበለጠ ተፎካካሪ መሆን ይጠበቅብናል፤ በሰኝጠረዡ የተሻለ ደረጃ እንደሚኖረን እምነቴ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *