አርባምንጭ ከሰንጠረዡ ግርጌ ሲላቀቅ ወልዲያ ከሀዋሳ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ዛሬ አምስት ጨዋታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተካሂደዋል። አርባምንጭ ወደ ድል ሲመለስ ሀዋሳ ከተማ እና ወልዲያ ነጥብ ተጋርተዋል።

አርባምንጭ ከተማ 1-0 ሲዳማ ቡና

በ16ኛው ሳምንት ከባድ ሽንፈት አስተናግዶ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ በመቀመጥ ጨዋታውን ያደረገው አርባምንጭ ከተማ በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ሽንፈት የደረሰበት ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ላይ ነፍስ ዘርቷል።

እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች በ6ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በሳጥን ውስጥ ተገፍቶ በመውደቁ ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል በማለት በእለቱ ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ ላይ ተቃውሞን አሰምተዋል። ብዙም ሳይቆይ በ14ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ብርሀኑ አዳሙ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት እንዳለ ከበደ ወደ ግብነት ለውጦ አዞዎቹን አሸናፊ አድርጓል።
እዮብ ማለ – አርባምንጭ ከተማ
” ደጋፊያችን እየራቀን የመጣው ውጤት ስላጣን ነው። በውጤታችን ተከፍቷል። ዛሬም ተጋድሎ አድርገን አሸንፈን ወጥተናል። ስለዚህ ህዝቡ መታገስ አለበት። በሙሉ ልብ መጫወት መቻላችን ለድል አብቅቶናል፡፡ ”
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
“ካለፉት በተሻለ በሜዳ ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለናል። ማሸነፍም ይገባን ነበር። የዳኝነቱ ችግር ዋጋ አስከፍሎናል። እንዲህ ነው ብዬ መናገር ባልፈልግም ተበድለናል። በቀጣይ ከዚህ ሁሉ ወጥተን ተሽለን እንቀርባለን ፤ ወደ አሸናፊነትም እንመለሳለን፡፡ ”
ወልዲያ 1-1 ሀዋሳ ከተማ

ሁለት ተከታታይ ጨዋታ በማሸነፍ በጥሩ አቋም ላይ ሆኖ ወደ ወልዲያ የተጓዘው ሀዋሳ ከተማ በውድድር አመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ለማሸነፍ ቢቃረብም በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ጎል ነጥብ ተጋርቷል።

ሀዋሳ ከተማዎች በ52ኛ ደቂቃ ላይ ወጣቱ አጥቂ እስራኤል እሸቱ ባስቆጠራት ጎል ቀዳሚ በመሆን እስከ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ድረስም መሪ መሆን ቢችሉም በጭማሪ ደቂቃ ላይ ምንያህል ተሾመ ያስቆጠራት ጎል ወልዲያ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጋለች።

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ወልዲያ

” ጨዋታው ውጥረት የበዛበት ነበር። ሀዋሳ ኳስን ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። እኛም ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ብንገባም በሜዳ ላይ ያሰብነውን ማድረግ አልቻለንም። ለዚህ በቡድኔ ውስጥ ያለው የተጫዋቾች እጥረት በየጫወታው ለውጤታችን መጥፋት ትልቁን ሚና ይወስዳል። ማሸነፍ እየቻልን በሰራነው ስህተት እንደእቅዳችን መሆን ከብዶናል። ”

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
” በጨዋታው እኛ ከተጋጣሚያችን የተሻልን ነበርን። ነገር ግን ተጫዋቾቼ እየተደበደቡ ዳኛው በዝምታ ማለፋቸው እና በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ቢጫ መስጠታቸው የሚያበሳጭ ነው። ጨዋታው ላይ የነበረው ሁኔታ ሁሉ አሳዛኝ ድርጊቶች ናቸው። በአንቅስቃሴያችን ደስተኛ ነኝ፤ ማሸነፍም ይገባን ነበር። እግር ኳስ እንዲህ ከሆነ ያሳዝናል። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *