ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | 17ኛ ሳምንት የመጋቢት 21 ጨዋታዎች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ትናንት ከተደረጉት አምስት ጨዋታዎች በተጨማሪ ዛሬ ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ያስተናግዳል። ሶዶ እና አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉትን እነዚህን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

ወላይታ ድቻ ከ መከላከያ

ዛሬ በ9 ሰዓት ሶዶ ስታድየም ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አሸናፊ የነበሩትን ሁለት ክለቦች ያገናኛል። ወላይታ ድቻ 14ኛው ሳምንት ላይ ከደረሰበት የጅማ አባ ጅፋር ሽንፈት ውጪ በአፍሪካ መድረክም ሆነ በሊጉ በድል እየተንበሸበሸ ይገኛል። በመጀመሪያው ዙር አዲስ አበባ ላይ 1-0 በረታው መከላከያ ላይ ዳግም ውጤት ከቀናውም ወደ 6ኛ ደረጃ የማደግ ዕድል ይኖረዋል። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ ለተቀመጠው መከላከያም ይህ ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው። ቡድኑ ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ማሸነፍ መቻሉ እየተሻሻለ መምጣቱን ቢያሳይም በዛሬው ጨዋታ ከሜዳው ውጪ በተመሳሳይ ብቃት ሶስት ነጥቦችን ይዞ በመመለስ ራሱን ከስጋት ማዳን ይጠበቅበታል።

ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት የድቻዎቹ ፀጋዬ ብርሀኑ እና እርቅይሁን ተስፋዬ ወደ ሜዳ የማይመለሱ ሲሆን ለ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከተመረጠው እዮብ አለማየሁ በተጨማሪ ከሲዳማ ቡና ተዘዋውሮ በደደቢቱ ጨዋታ ድንቅ የነበረው ፀጋዬ ባልቻ በልምምድ ወቅት በገጠመው ጉዳት የማይሰለፍ ይሆናል። በመከላከያ በኩል አሁንም አዲሱ ተስፋዬ ከጉዳቱ ያልተመለሰ ሲሆን ሲሆን በቅርቡ ቀዶ ጥገና እንደሚደረግለት የተነገረው ቴዎድሮስ በቀለም ከጨዋታው ውጪ ነው።

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ስር አንድ ጨዋታ ያደረገው መከላከያ የተጨዋቾች እና የአሰላለፍ ለውጥ አድርጓል። በ4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ በኃይሉ ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰን ተጠባባቂ አድርጎ የኢትዮ ኤሌክትሪኩን ጨዋታ የጀመረው የጦሩ ቡድን ዳዊት እስጢፋኖስን ማዕከል ያደረገ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ዋነኛ የጨዋታ ምርጫው ያደረገ ይመስላል። የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም የመስመር ተከላካዮቹን እገዛ እምብዛም ባያገኝም የቡድኑ የአማካይ ክፍል በዛ ጨዋታ የከፋ ብልጫ አልተወሰደበትም። ሆኖም የዛሬው ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ መከላከያ በዳይመንዱ ግራ እና ቀኝ የሚሰለፉት ሁለቱ ሳሙኤሎች ከኳስ ጋር ወደ መሀል ሲሳቡ በግራ እና ቀኝ የሚተውቱን ቦታ በመስመር ተከላካዮቹ ካልተሸፈነ በአመረላ ደልታታ እና ዘላለም እያሱ አማካይነት ሊጠቀምበት መቻሉ ግልፅ ነው። በመሆኑም ቦታውን የጨዋታው ዋነኛ የፍልሚያ ቀጠና ያደርገዋል። 

አማካይ ክፍል ላይ የሚጠበቀው ሌላኛው ፍልሚያ ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ የመጫወት ኃላፊነት የሚጣልበት ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሌሎቹ የጦሩ አማካዮች ከአብዱልሰመድ አሊ እና በዛብህ መለዮ ቀጥሎም ከኃይማኖት ወርቁ ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። እንደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጀርባው ብዙ ክፍተት የማይሰጠው የድቻ የተከላካይ ክፍል ከተጠቀሱት አማካዮቹ ጥሩ ሽፋን እንደሚያገኝም ይጠበቃል። መከላከያ ከምንይሉ ወንድሙ ሌላ በነ ማራኪ ወርቁ ግቦችን ማግኘቱ ወላይታ ድቻም ከጃክም አራፋት ውጪ እንደ አመረላ ደልታታ ባሉ ተጨዋቾች ግብ ማስቆጠር መጀመሩ ጨዋታው በግብ ፊት ጥሩ ውሳኔ የሚያሳልፉ ተጨዋቾችን እንደመያዙ በርካታ ሙከራዎችን ሊያስተናግድ የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– እርስ በእርስ በተገናኙባቸው 9 የሊግ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 11 ግቦችን አስቆጥሮ 5 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ከ3 አቻ ውጤቶች መመዝገብ ውጪ መከላከያ አንዴ ብቻ ድል ሲቀናው 6 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

– በወላይታ ድቻ ሜዳ በተደረጉት 4 ደግሞ ጨዋታዎች መከላከያ እስካሁን አንድ ጊዜ አቻ ሲለይይ ድቻ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ቀሪዎቹን 3 ጨዋታዎች ድል አድርጓል።

– መከላከያ በ2008 ቦዲቲ ላይ 1-1 ከተለያበት ውጤት በቀር በሌሎች ጨዋታዎች በድቻ ሜዳ ጎል አላስቆጠረም።

– ወላይታ ድቻ ለመጨረሻ ጊዜ ሶዶ ላይ ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ሲያሸንፍ 8 ግቦችን አስቆጥሮ 1 ጊዜ ብቻ ግብ አስተናግዷል።

– ዘንድሮ በአራት አጋጣምዎች ከአዲስ አበባ የወጣው መከላከያ ዓዲግራት ላይ ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ከጅማ አንድ ነጥብ ይዞ ሲመለስ አርባምንጭ እና ወልዲያ ላይ ሽንፈት ገጥሞታል።

ዳኛ

– የዛሬውን የሶዶ ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ የሚመራው ይሆናል። ተካልኝ ዘንድሮ በዳኛቸው 5 ጨዋታዎች 16 የማስጠንቀቂያ እና 2 የቀይ ካርዶችን መዟል።

Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ከስምንተኛው ሳምንት በኃላ እንዳደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያ ቡና ከድል እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሽንፈት መልስ ነው ዛሬ የሚገናኙት። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዛ ጨዋታ ላይ ካገኘው ድል በቀር የአቋም መዋዠቁ አሁንም ቀጥሏል። ከሜዳ ውጪ ያሳካቸው ሁለት የአቻ ውጤቶች እና ድሬዳዋ ከተማ ላይ በአዲስ አበባ ያሳካው ድል ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር በተስፋ እንዲጨርስ ቢያደረውም በአመቱ ለአራተኛ ጊዜ ሶስት ግቦችን አስተናግዶ በመከላከያ የቀመሰው የ3-1 ሽንፈት ነገሮችን ወደ ቦታቸው እንዳይመለስ ያሰጋል። ከዚህ ፍፁም የተለየ ጊዜ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በየሳምንቱ ራሱን ወደ ሊጉ መሪዎች ማስጠጋቱን ተያይዞታል። ዛሬ ደደቢት እና አዳማ እርስ በእርስ እንደመገናኘታቸው ከአርባ ቀናት በኃላ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የሚመለሱት ቡናማዎቹ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ሊጉን የሚመራውን ክለብ በጥቂት ነጥቦች ርቀት መከተል ይችላሉ። 

ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ጉዳት ላይ ከነበሩ ተጨዋቾች መሀከል አክሊሉ አያነው ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን አለማየሁ ሙለታም ቀለል ያሉ ልምምዶችን ጀምሯል። በቡድኑ ውስጥ አዲስ የተሰማ የጉዳት ዜና ግን የለም። በተመሳሳይ አልሀሰን ካሉሻ የሚመለስለት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስብስብም ጉዳት አላስተናገደም። ሆኖም የመከል ተከላካዩ ግርማ በቀለ በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት ይህ ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። 

እንደ ክለቡ ውጤት ሁሉ መሻሻል አሳይቶ የነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመከላከል አደረጃጀት መሀል ሜዳ ላይ ጥሩ የኳስ ፍሰትን የሚያሳካ ቡድን ከገጠመው ስህተቶችን ሊሰራ እንደሚችል የመከላከያው ጨዋታ አሳይቶናል። በዚህ ረገድ ከመከላከያም የተሻለ ጥንካሬ ያለው የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ክፍል ተመሳሳይ ብልጫን ከወሰደ የግብ ዕድሎችን ማግኘቱ አይቀርም። ሆኖም እንደመከላከያው ጨዋታ ከተከላካዮች ጀርባ ሰፊ ክፍተት ላይተው ከሚችለው የቀዮቹ ተጨዋቾች አማካይ ቦታ አያያዝ አንፃር የቡና የመስመር አጥቂዎች እና ሳሙኤል ሳኑሚ በጠበበ ክፍተት ውስጥ የመንቀሳቀስ ግዴታ ሊኖርባቸው ይችላል። ተፈላጊውን ነፃነት እንዲያገኙም በተጨዋቾች ብዛት እንደሚጨናነቅ ከሚጠበቀው የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ይልቅ ኢትዮጵያ ቡናዎች የመስመር ተከላካዮች እገዛ ሊያገኙ በሚገባቸው  የግራ እና ቀኝ አቅጣጫዎች ጥቃቶችን ቢፈፅሙ  የተሻለ እንደሚሆን ይታሰባል።

አልሀሰን ካሉሻን ካልያዘ ሙሉ ለሙሉ ከቅርፁ የሚወጣው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የአማካይ ክፍል ተጨዋቹ እንደተባለው ከጉዳት ከተመለሰለት እንደሚሻሻል ይጠበቃል። ፊት ላይ የሚኖረው የዲዲዬ ለብሪ እና ታፈሰ ተስፋዬ ጥምረት ንፁህ የግብ ዕድሎችን እንዲያገኝ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሊወሰድበት የሚችለው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ወደ ማጥቃት በሚያርገው ሽግግር ላይ ፈጣን መሆን እና ያልተዛነፉ ኳሶችን ለአጥቂዎቹ ማድረስ ይጠበቅበታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ተክሉ ታፈሰ እና በሀይሉ ተሻገርን የመሰሉ የቡድኑ አማካዮች ካሉሻ አልሀሰን ከአጥቂዎች ጀርባ ነፃ ሆኖ ኳስ መቀበል የሚችልባቸውን አማራጮች ለመፍጠር በመከላከል ላይ ከሚኖራቸው ተሳትፎ ባለፈ ከሀሪሰን ፊት ሊኖር የሚችለውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ነፃ  በሆኑ መስመሮች የቡድኑን ጥቃት የማስጀመር ሀላፊነት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። 

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በሁሉም ዓመታት ተሳታፊ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች 39 ጊዜ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና 20 እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ 10 ጊዜ አሸናፊ ሆነዋል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በ39ኙ ጨዋታዎች ቡናዎች 65 እንዲሁም ኤሌክትሪኮች 43 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– ከዚህ ቀደም በአዝናኝነቱ የሚጠቀሰው ይህ ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪክ ከፍተኛ ጎል ያስተናገደ ግንኙነት ነው። (108)

– በኢትዮጵያ ቡና በኩል በትልቅነቱ የሚጠቀሰው ድል በ2002 6-2 ያሸነፈበት ጨዋታ ሲሆን በወቅቱ የአሁኑ የኤሌክትሪክ አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ለብቻው አራት ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወሳል። በኤሌክትሪክ በኩል የሚጠቀሰው ደግሞ በ1995 የውድድር ዘመን 4-2 ያሸነፈበት ነው።

– ኢትዮጵያ ቡና ከጥር አጋማሽ በኃላ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ሲሆን ከአምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ባለድል ሆኗል።

– ኢትዮ ኤሌክትሪክ የዛሬ ተጋጣሚውን ከረታበት የታህሳስ 19ኙ ጨዋታ በኃላ 9 የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው በአምስቱ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በ16ኛው ሳምንት ድሬደዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጉት ጨዋታ መልስ በዚህ ጨዋታ ላይ ተመድቧል። ዘንድሮ 9ኛ ጨዋታውን የሚመራው በላይ አንድ ጊዜ ቀይ ካርድ ሲመዝ በ31 አጋጣሚዎች ደግሞ ቢጫ ካርዶችን አሳይቷል።

Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ደደቢት ከ አዳማ ከተማ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች ሁሉ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ይህ ጨዋታ 11፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል። በአመዛኙ ለወጣት ተጨዋቾች ዕድል በመስጠት የመጀመሪያውን ዙር በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሆነው የጨረሱት ሁለቱ ክለቦች በቅርብ ሳምንታት እያሳዩ ያሉት አቋም ግን የተለያየ ሆኗል። የሊጉ መሪ ደደቢት 6 ጨዋታዎችን ከማሸነፍ ጉዞው በኃላ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስቴ ለመሸነፍ ተገዷል። ከነዚህ ሽንፈቶች ሁለቱ ደግሞ የተመዘገቡት በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቹ ነበር። በአንፃሩ በነዚህ ጊዜያት አርባምንጭ ላይ ብቻ ሽንፈት የገጠመው አዳማ ከተማ ሶስት ጊዜ አሸናፊ መሆን ችሏል። ቡድኑ ዛሬም ውጤት ከቀናው ከተጋጣሚው ጋር በነጥብ እኩል በመሆን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ይችላል።

ደደቢት ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ካስመረጠው አቤል እንዳለ በስተቀር ሙሉ ስብስቡን ለዚህ ጨዋታ እንደሚጠቀም ይጠበቃል። አዳማ ከተማ ግን በወልዲያው ጨዋታ ተመልሶ በ9ኝ ደቂቃዎች ውስጥ ሌላ ጉዳት የገጠመው ወሳኙን አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሚካኤል ጆርጅን ሲያጣ ተስፋዬ በቀለ እና ሙጂብ ቃሲም ከጉዳት ይመለሱለታል። በተጨማሪ አዲስ ፈራምው ፍርድአወቅ ሲስይን አሁንም በአዲሱ ክለቡ አሰላለፍ ውስጥ እንደማንመለከተው ሰምተናል።

ጌታነህ ከበደን በአንዱ ዳዋ ሆቴሳን ደግሞ በሌላው ጫፍ የሚያገናኘው ጨዋታ የሁለቱንም ቡድን ተከላካዮች ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። ጌታነህ ካለው ልምድ አኳያ የትኛውንም ጨዋታ ውጤት በግል ብቃቱ የመቀየር ብቃት አለው። ዳዋ ደግሞ በቅርብ ጨዋታዎች ከጀርባው ካሉት ተጨዋቾች እና ከሌላው አጥቂ ቡልቻ ሹራ ጋር እያሳየ ያለው መናበብ ቡድኑ ለሚሰንዝራቸው ጥቃቶች ዋነኛ መቋጫ ያደርገዋል። በዚህም መሰረት የደስታ ደሙ እና የከድር ኩሊባሊ የመሀል ተከላካይ ጥምረት በእንቅስቃሴ በተሞላው የሁለቱ የአዳማ ከተማ አጥቂዎች አጨዋወት ውስጥ የመከላከል ቅርፁን እንዳይለቅ መጠንቀቅ ይኖርበታል። ወሳኝ ተጨዋቾቹን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው የአዳማ የኃላ መስመር ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከኳስ ጋር በሚገናኝባቸው ቅፅበቶች ኳሶችን ከማስጣል ባለፈ በመስመር አጥቂዎቹ እንቅስቃሴ ምክንያት በአራቱ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ መሀል የሚኖረውን ክፍተት አስፍቶ ለተጨዋቹ ግልፅ የሙከራ ዕድል ላለመስጠት መጠንቀቅ ይገባዋል።

አማካይ ክፍል ላይ የሚጠበቀውን ፍልሚያ ስንመለከት ደግሞ ደደቢት ከአስራት መገርሳ በቀጥታ ከሚጣሉ ኳሶች ባለፈ በፋሲካ አስፋው እና የአብስራ ተስፋዬ ቅብብሎች መነሻነት በተለይም የማጥቃት ተሳትፎ በሚያደርገው የአዳማው የግራ መስመር ተከላካይ ሱሌይማን መሀመድ በኩል በማድላት ጥቃቶችን እንደሚፈፅም ይጠበቃል። ከአዳማ የአማካይ ክፍል ጥንካሬ አንፃርም ደደቢቶች የመስመር አጥቂዎቻቸውን ለአማካይ ክፍላቸው በማቅረብ በኢስማኤል ሳንጋሪ እና በመሀል ተከላካዮቹ መሀል ለሚንቀሳቀሰው ጌታነህ ከበደ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይታሰባል። የአዳማ ከተማ የማጥቃት ሂደት ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ከንዓን ማርክነህ ከጎኑ ከሚሰለፈው ኢስማኤል ሳንጋሪ እስከ ሁለቱ የፊት አጥቂዎች ድረስ ባለው ቦታ ላይ መሀል ለመሀል የሚያደርጋቸው ቅብብሎች እና ዘግይቶ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ መግብያ ላይ ሲደርስ የሚሞክራቸው ኳሶች ለቡድኑ ትልቅ ዋጋ ይኖራቸዋል። በዚህ ሂደርም ተጨዋቹ ከአስራት መገርሳ ጋር አንድ ለአንድ የሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ወሳኝ ይሆናሉ። አዳማ ከተማ በመስመር አማካይነት እንደሚጠቀምባቸው የሚጠበቁት ሱለይማን ሰሚድ እና በረከት ደስታ ቀርበው ኳስ ከሚቀበሏቸው አጥቂዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው ቅንጅትም የደደቢት የመስመር ተከላካዮችን የመፈተን አቅሙ የጎላ ነው።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ደደቢት እና አዳማ ከተማ በሊጉ ከተገናኙባቸው 15 ጨዋታዎች ውስጥ 29 ግቦች ያስቆጠረው ደደቢት 7 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 9 ጊዜ አሸንፎ 16 ግቦችን አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። 

– ከነዚህ መሀል አዲስ አበባ በተገናኙባቸው 7 ጨዋታዎች አንዴ ብቻ አቻ ሲለያዩ  ደደቢት 4 ጊዜ እንዲሁም አዳማ 2 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ደደቢት አዳማ ካስቆጠራቸው 6 ግቦች ሶስት እጥፍ የሚሆን ያህል ጊዜ የተጋጣሚውን መረብ ከኳስ ጋር አገናኝቷል። 

– የእርስ በእርስ ግንኙነቱ በርካታ ጎሎች (45) የተቆጠሩበት ሲሆን ደደቢት በሁለት አጋጣሚዎች (6-1 እና 7-1) ያሸነፈባቸው ውጤቶች ለጎሎቹ መጠን መጨመር እንደምክንያት የሚጠቀስ ነው።

– ደደቢት ዘንድሮ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች በአምስቱ ድል የቀናው ሲሆን ከሜዳቸው በወጡባቸው 8 አጋጣሚዎች በአራቱ አቻ የተለያዩት አዳማዎች ሁለት ጊዜ 3 ነጥቦችን ይዘው ተመልሰዋል። 

– ከሜዳው ውጪ ጥሩ ሪከርድ ያለው አዳማ ዘንድሮ አዲስ አበባን በጎበኘባቸው ሶስት ጨዋታዎች ከመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ሲጋራ ኢትዮኤሌክትሪክን ማሸነፍ ችሏል።

ዳኛ

– የመጨረሻውን የሳምንቱ የሊግ ጨዋታበመሀል ዳኝነት የሚመራው እስካሁን በአምስት ጨዋታዎች ሰባት የቢጫ እና ሁለት የቀይ ካርዶችን የመዘዘው ፌደራል ዳኛ ማኑኤ ወልደፃዲቅ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *