ሪፖርት | ደደቢት ወደ አሸናፊነቱ ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር ሊጉን በ29 ነጥብ እየመራ የሚገኘውን ደደቢትን በ26 ነጥብ 5ኛ ላይ ከተቀመጠው አዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በኤፍሬም አሻሞ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ደደቢት አሸንፎ መሪነቱን አስቀጥሏል፡፡

ባለሜዳዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ሶዶ ላይ በወላይታ ድቻ 1ለ0 ከተረታው ቡድን ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ላይ ክዌኬ አንዶህን በስዩም ተስፋዬ እንዲሁም አማካዩ ፋሲካ አስፋውን በአጥቂው አቤል ያለው ተክተው በ4-4-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ በአንጻሩ አዳማ ከተማዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ በሜዳቸው ወልዲያ ከተማን 3ለ1 ከረታው ቡድን ውስጥ በግብጠባቂ ስፍራ ላይ ጃኮ ፔንዜ ዳግም ወደ ቡድኑ ሲመለስ በተጨማሪም ሙጂብ ቃሲም ፣ አፍሬም ዘካሪያስና ደሳለኝ ደባሽ በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊነትን እድል አግኝተው በተመሳሳይ የ4-3-3 አደራደር ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች በተለይ ደደቢቶች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ በተደጋጋሚ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል፡፡ በነዚህ ደደቢቶች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢይዙም ወደ ግብ በመድረስ የመጀመሪያውን አስደንጋጭ ሙከራ ያደረጉት ግን አዳማ ከተማዎች ነበሩ። በ12ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ ሱሌይማን ሰሚድ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ዳዋ ሆቴሳ ከጠበበ አንግል ወደ ግብ የላካትን ኳስ ክሌመንት አድኖበታል፡፡

ከሰሞኑ ድንቅ እንቅስቃሴን እያደረገኘ የሚገኘው የአዳማ ከተማው አማካይ ከነዓን ማርክነህ በዛሬው ጨዋታ አለመኖሩን ተከትሎ የአዳማ ከተማ በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል የነበረው የፈጠራ አቅም በእጅጉ ተዳክሞ ተስተውሏል ፤ ነገርግን ከዳዋ ሙከራ በኃሏ በነበሩት በመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች በጨዋታው የበላይነት በወስደው በተደጋጋሚ የደደቢትን የግብ ክልል መፈተሽ ችለዋል፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴ በተለይ የመስመር አጥቂው በረከት ደስታ ሚና እጅግ የጎላ ነበር፡፡

ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ25ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በረከት ደስታ ያሳለፈለትን ኳስ የደደቢቱ የመሀል ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ቡልቻ ሹራ አፈትልኮ አሞልጦ ከደደቢቱ ግብጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ ጋር 1ለ1 ቢገናኝም ቡልቻ ኳሷን በግብጠባቂው አናት ላይ አሳልፋለው ብሎ በቀላሉ ያሳቀፈው ኳስ በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ደደቢቶች የቅርጽ ለውጥ በማድረግ በመጀመሪያ አጋማሽ በመስመር አማካይነት ሲጫወት የነበረው ኤፍሬም አሻሞን ከአቤል ያለውና ጌታነህ ከበደ ጋር በሶስትዮሽ የአጥቂ መስመሩን እንዲመሩ በማድረግ ሌላኛውን በመጀመሪያው አጋማሽ የመስመር አማካይ የነበረው ሽመክት ጉግሳን ከያብስራ ተስፋዬና አስራት መገርሳ ጋር የመሀል ክፍሉን እንዲመሩ በማድረግ በ4-3-3 አሰላለፍ ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ ይህም ቅያሬ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታውን ሚዛን ወደ ደደቢት የቀየረ ነበር ብሎ ለመናገር ያስደፍራል። በአዳማ ከተማ በኩል ከአራቱ ተከላካዮቹ ፊት የተሰለፈው ኢስማኤል ሳንጋሪ ከሁለቱ የመሀል አማካዮች በመከላከል ወቅት በቂ ድጋፍ ባለማግኘቱ የተነሳ በግራ በቀኙ የነበሩትን ሰፋፊ ክፍተቶች ሽመክትና ያብስራ በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

በ57ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ ቦጋለ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አቤል ያለው በግል ጥረቱ ሶስት የአዳማ ተጫዋቾችን በማለፍ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ ደገፍ በማድረግ ቡድን መሪ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል ፤ ይህችም ግብ ደደቢቶች ከሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ያስቆጠሯት የመጀመሪያ ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡ ከግቧ መቆጠር በደቂቃዎች ልዩነት በተመሳሳይ አቤል ከመስመር ተጫዋቾችን ቀንሶ ወደ ውስጥ በመግባት ወደ ጎል የላካትን ኳስ ጃኮ ፔንዜ ሲያድንበት ከቆይታ በኋላ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው አቤል ጉዳት አጋጥሞት ወጥቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የነበሩት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ እጅጉን ተዳክመው ተስተውለዋል፤ በዚህም የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ግብ ለመድረስ ያደርጉት የነበረው ጥረት በደደቢት ተከላካዮች በቀላሉ ሲከሽፍ ተስተውሏል፡፡

በ82ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስአበባ ስታዲየም ፓውዛ ሙሉ ለሙሉ በመጥፋቱ ጨዋታው የተቋረጠ ሲሆን ከ27 ደቂቃዎች በኋላ ቀጥሎ በቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተለይም ደደቢት በሽመክት ጉግሳና በበረከት ደስታ እጅግ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን አምክነዋል፡፡
ጨዋታው በደደቢት የ1ለ0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢቶች ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኃላ ዳግም ወደ ድል በመመለስ ነጥባቸውን ወደ 32 በማሳደግ በመሪነታቸው ቀጥለዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

” ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኃላ የተገኘ ድል ስለሆነ በጣሙን ተደስቻለሁ፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ካለመረጋጋት የመነጨ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶብን ነበር። ነገርግን በሒደት ክፍተቶቻችን በማረም ልናሸንፍ ችለናል፡፡”

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

“በጨዋታው አቅደን የመጣነውን ነገር ማሳካት አልቻልንም። በአጠቃላይ የጨዋታው ውጤት ለኛ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ የተጫዋቾች ጉዳትና በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን እድሎች አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡”

Leave a Reply