ሁለት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ለሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ተመርጠዋል

አማኑኤል ኃይለስላሴ እና በላቸው ይታየው በቡሩንዲ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ከሚዳኙ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡

ሴካፋ ለውድድሩ 7 ዋና እና 6 ረዳት ዳኞችን ከአባል ሀገራቱ የመረጠ ሲሆን በመሃል ዳኝነት አማኑኤል ኃይለስላሴ ፣ በረዳት ዳኝነት ደግሞ በላቸው ይታየውን አካቷል፡፡ የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዓመቱ ምስጉን ዳኛ ሆኖ የተመረጠው አማኑኤል ዘንድሮ በሊጉ 6 ጨዋታዎችን ዳኝቶ 22 ቢጫ ካርዶች እና 1 የቀይ ካርድ መዟል፡፡ ረዳት ዳኛው በላቸውም በተመሳሳይ 6 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፏል፡፡

ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ የምትካፈል ሲሆን በውድድሩ ላይ በሚመዘገብ ውጤት መሰረት ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፈው ቡድን ይለያል፡፡

ከወራት በፊት በተደረገው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ላይ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ከኢትዮጵያ በብቸኝነት የተወከለ ዳኛ እንደነበር የሚታወስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *