ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች – ክፍል 1

ነገ መጋቢት 26 የሊጉ 18ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች እንዲካሄዱ ታስቦ የነበረ ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻን የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ተከትሎ የጨዋታዎቹ ቁጥር ወደ ስድስት ዝቅ ብሏል። በክፍል አንድ ዳሰሳችንም ሀዋሳ፣ ጎንደር እና አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉትን ሶስት ጨዋታዎች ተመልክተናቸዋል።


ሀዋሳ ከተማ ከደደቢት

ምንም እንኳን አሁን ላይ በመሀከላቸው የ10 ነጥብ ልዩነት ቢኖርም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሳምንቱ ተጠባቂ ከሆኑ ጨዋታዎች መሀከል አንዱ ነው። ሀዋሳ ከተማ ለ2 ወራት ከሽንፈት መራቅ ቢችልም ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ዘልቆ ለመግባት የተቸገረ ይመስላል። ሳምንት ወልዲያ ላይ ሶስት ነጥብ ለማሳካት ተቃርቦ በመጨረሻ ሰዓት ነጥብ ለመጣል መገደዱም ከነገ ተጋጣሚው ጋር ይበልጥ አራርቆታል። ክለቡ በዚህ ጨዋታ ላይ በደል ድርሶብኛል በማለት ለፌዴሬሽኑ ማመልከቱም የሚታወስ ነው። ከሶስት ጨዋታዎች በኃላ በተገኘችው የኤፍሬም አሻሞ ብቸኛ ጎል አዳማን በማሸነፍ ከሁለቱ ሽንፈቶች ያገገመው ደደቢት አሁንም ቢሆን ከተከታዮቹ በሚገባ አልራቀም። መሪነቱን ለማረጋጋት ደግሞ በሜዳው አይቀመሴ የሆነውን ሀዋሳ አሸንፎ የመመለስ ግዴታ ይኖርበታል።

በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ምንም የተለየ ጉዳት የሌለ ሲሆን በወልዲያ ጨዋታ ጉዳት ገጥሟቸው የነበሩት እስራኤል እሸቱ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ታፈሰ ሰለሞን ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ሲገለፅ መሀመድ ሲላ ከ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት በኃላ ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡ በተቃራኒው ደደቢት የቀኝ መስመር ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬን በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት የማይጠቀም ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቤል እንዳለ ከደደቢት መሳይ ፓውሎስ፣ ዮሀንስ ሴጌቦ እና ፀጋአብ ዮሴፍ ከሀዋሳ ከተማ ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመመረጣቸው ይህ ጨዋታ ያልፋቸዋል፡፡

በጨዋታው ደደቢት ሰሞኑን እየተከተለው ካለው አጨዋወት አንፃር የሀዋሳ ከተማ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ነፃነት የሚያገኝ ይመስላል። ደደቢት ወደ 4-4-2 መምጣቱን ተከትሎ የአስራት መገርሳ እና ያብስራ ተስፋዬ የመሀል አማካይ ጥምረት ከመስመር አጥቂዎቹ የቅርብ ርቀት እገዛ ከሚያገኘው የታፈሰ ሰለሞን እና ሙሉአለም ረጋሳ የማጥቃት ሃይል ጋር ይጋፈጣል። የፍሬው ሰለሞን እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ወደ አማካይ ክፍሉ መቅረብም ለመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ በር የሚከፍት ይሆናል። ሆኖም ደደቢት የሜዳውን ስፋት እንዲጠቀም ሀላፊነት የሚሰጣቸው ሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ የተጋጣሚያቸውን አማካዮች ከመቆጣጠር ባለፈ ከሀዋሳ መስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያም የሚጠበቅ ነው።

የሀዋሳው ጋብርኤል አህመድ ብቸኛ የተከላካይ አማካይ በመሆኑ የሜዳውን የጎን ስፋት በቦታው ከመከላከሉ ባለፈ ከጀርባው ለሚኖሩት ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው የሚላኩ ኳሶችን የማቋረጥ ሀላፊነቱ ከፍ ያለ ነው። ተጨዋቹ በሜዳው ቁመት ከተካላካይ መስመሩ ጋር የሚኖረውን ክፍተት ማመጣጠን እና ሁለቱ አጥቂዎች ያለ ኳስ ብዙ ነፃነት እንዳይኖራቸው ማድረግ የሚችል ከሆነም ሀዋሳ በድንገተኛ ኳሶች ጥቃት እንዳይሰነዘርበት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። በተቃራኒው ደግሞ የሀዋሳው የመሀል አጥቂ እስራኤል እሸቱ ከቡድኑ አጨዋወት አንፃር ከአማካይ ክፍሉ የኳስ ፍሰት ጋር ወደ ኋላ ተጠግቶ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር የሚከውነው ቅብብል በደደቢት የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መሀል ክፍተትን ሊያስገኝ ስለሚችል የአስራት መገርሳን የቅርብ ክትትል የሚፈልግ ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው 17 አጋጣሚዎች ደደቢት 11 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 36 ግቦችን አስቆጥሯል። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 17 ጊዜ ግብ ሲቀናው 2 ጊዜ አሸንፏል።

– ሀዋሳ ላይ በተደረጉ 8 ጨዋታዎችም ደደቢት 4 ጊዜ አሸንፎ 13 ግቦችን አስቆጥሯል። አንዴ ድል የቀናው ሀዋሳም 7 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

– ክለቦቹ በታሪካቸው ሶስት ጊዜ አቻ የተለዩባቸው ጨዋታዎች በሙሉ ሀዋሳ ላይ ተደረጉ ነበሩ፡፡

– ሀዋሳ በሜዳው ከደደቢት ጋር ያለው ሪከርድ ደካማ ነው። በ2006 የውድድር አመት 2-1 ከማሸነፉ ውጪም ድል አስመዝግቦ አያውቅም።

– ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች 5ቱን አሸንፎ 3ቱን አቻ ወጥቷል።

– ደደቢት ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ከወጣባቸው 6 አጋጣሚዎች ሶስቱንም ውጤቶች ሁለት ሁለት ጊዜ ሲያስመዘግብ ሽንፈቶቹ ግን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የመጡ ነበሩ።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ዛንቢያ የሚሄድ መሆኑን ተከትሎ የዚህ ጨዋታ የመሀል ዳኝነት ለፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘው ተሰጥቷል። ቢኒያም በሊጉ አራተኛ ጨዋታውን የሚዳኝ ሲሆን እስካሁን 11 የቢጫ እና 1 የቀይ ካርዶችን መዟል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ፋሲል ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ይህ ጨዋታ በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ልዩነቶችን የመፍጠር አቅም አለው። ፋሲል ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ መሸነፉ ከመሪው ጋር እንዲራራቅ ቢያስገድደውም በ4 ደረጃዎች ከሚበልጠው አባ ጅፋር ያለው ርቀት የሶስት ነጥብ ብቻ ነው። በኦኪኪ አፎላቢ ጎል ድሬደዋን የረታው ጅማ አባጅፋር በበኩሉ ደደቢትን በቅርብ ርቀት እየተከተለው ይገኛል። ቡድኑ የነገውን ፈተና ማለፍ ከቻለ ደግሞ መሪውን ይበልጥ በመቅረብ በቀጣይ በሜዳው ለሚያስተናግደው ጨዋታ ዝግጁ መሆን ይችላል። ሆኖም ፋሲል ከተማ በሜዳው የሚጫወት በመሆኑ እና መሸነፍ ከፉክክሩ በእጅጉ ስለሚያርቀው ጨዋታውን የማሸነፍ ግዴታ አለበት።

አሁንም ረዘም ያለ ጉዳት ላይ የሚገኘው የፋሲሉ አይናለም ኃይለ ወደ ሜዳ የማይመለስ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ ጉዳት ከገጠማቸው አጥቂዎች መሀመድ ናስር እና አብዱራህማን ሙባረክ መሀከል አብዱራህማን ለጅማው ጨዋታ እንደማይደርስ ተሰምቷል፡፡ በጅማ አባ ጅፋር በኩል እንዳለ ደባልቄ ከጉዳት ሲመለስ ተመስገን ገብረኪዳን ደግሞ በምትኩ ከጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡

ፋሲል ከተማ በማጥቃት ሂደቱ ውስጥ ዋና መሳሪያዎቹ የሆኑት ከአማካይ ክፍል ወደ መስመሮች የሚላኩ ኳሶች የጥራት ደረጃ በዚህ ጨዋታ ላይ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል። በቀላሉ ክፍተት የማይሰጠው የአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻውን ጥምረት አልፈው ወደነ ራምኬል ሎክ የሚሻገሩ ለመልሶ ማጥቃት የተመቹ ኳሶችን ማግኘት ካልተቻለም በጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ እንደተመለከትነው የመሀል ክፍል ተሰላፊዎቹን ቁጥር ሊጨምር የሚችልበት ዕድል አለ። በዚህም መሰረት ቡድኑ ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ ከመጣ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫን በመውሰድ ብቸኛ የፊት አጥቂውን እንቅስቃሴ ያማከለ የማጥቃት አቀራረብ ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል።

ጀማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን የመስመር አማካዮቹ ኄኖክ ኢሳያስ እና ዮናስ ገረመው ቀዳሚ ሀላፊነት ከአሚኑ እና ይሁን ግራ እና ቀጥ ያሉ ቦታዎች ለፋሲል የመስመር አጥቂዎች ነፃ እንዳይሆኑ በማድረግ ላይ የሚያተኩር ይመስላል። ሆኖም በማጥቃት ሽግግር ወቅት ከሁለቱ የመስመር ተሰላፊዎቹም ሆነ ከመሀል አማካዮቹ የሚነሱ ኳሶች ላይ ኦኪኪ እና ሳምሶን የሚደርሱባቸው ፍጥነት ለጅማ እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ሁለቱ አጥቂዎች ወደ መስመር እየወጡ ኳስ የሚቀበሉበት ሁኔታም ይህን ሂደት የሚያቀላጥፍ ሲሆን በዛው መጠን ከፋሲል የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉትን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ ለመጀመርያ ጊዜ በተገናኙበት የዘንድሮው ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ ፍሊፕ ዳውዝ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ፋሲል ከተማ አሸናፊ ሆኗል፡፡

– ፋሲል ከተማ ጎንደር ላይ ካስተናገዳቸው 6 ጨዋታዎች ውስጥ 3ቱን ሲያሸንፍ ሁለቱ ድሎች በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የተገኙ ናቸው።

– ከሜዳው ውጪ 8 ጨዋታዎችን አድርጎ በግማሹ የተሸነፈው አባ ጅፋር በሁለት አጋጣሚዎች ድል ቀንቶት ተመልሷል።

ዳኛ

– ዘንድሮ በሊጉ ከተደረጉ ጨዋታዎች መሀከል ስድስቱን በመዳኘት 19 የማስጠንቀቂያ እና 1 የቀይ ካርድ የመዘዘው ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አሊጋዝ ይህንን ጨዋታ ይመራዋል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልገጠማቸው እና ጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙትን ክለቦች ያፋልማል። መከላከያ አሁንም ከስጋት ውጪ ለመሆን ብዙ ቢቀረውም ኢትዮ ኤሌክትሪክን ማሸነፉ እና ከሶዶ አንድ ነጥብ ይዞ መመለሱ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ እንዲጠጋ አግዞታል። ከሁሉም የሊጉ ክለቦች አንፃር መልካም አቋም ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ያለሽንፈት ሁለት ወራትን ያሳለፈ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት በስድስት ጨዋታዎች 12 ነጥቦችን መሰብሰብ ሲችል ጎል ያላስቆጠረው መቐለ ላይ በተደረገው ጨዋታ ብቻ ነበር። ቡድኑ በሂደት ራሱን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ማምጣት የቻለ ሲሆን በሌሎቹ ውጤት ላይ ቢመሰረትም ካሸነፈ እስከ 2ኛነት ከፍ ሊል መቻሉ የጨዋታውን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል።

መከላከያ አሁንም የትከሻ ህመም ገጥሞት እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ክለቡን የማያገለግለው ቴዎድሮስ በቀለን እና ወደ ልምምድ ቢመለስም ለጨዋታ ብቁ ያልሆነው አዲሱ ተስፋዬን የማያሰልፍ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወደ ልምምድ የተመለሰው አክሊሉ አየነው ለጨዋታው ብቁ ካለመሆኑ በቀር የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም አቡበከር ነስሩ እና ሚኪያስ መኮንን በ20 አመት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው የማይኖሩ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው መዋቅር አንፃር ጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ የተጨዋቾች መደራረብ እንዳይኖረው ያሰጋል። መከላከያ የመስመር ተከላካዮቹን ተሳታፊ እያደረገ በማይገኘው የ4-4-2 ዳይመንድ አጠቃቀሙ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናም የመስመር አጥቂዎቹን ጨምሮ ወደ ኋላ በጥልቀት የሚመለሱት የአጥቂ አማካዮቹ መሀል ሜዳው ላይ በአንድነት የሚገናኙባቸው ጊዜያት ለሁለቱም ቡድኖች የቅብብል ስኬት አሉታዊ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል። በመሆኑም መከላከያም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል።

በመከላከያ በኩል ይህን ለማሳካት የመስመር ተከላካዮቹ ሽመልስ ተገኝ እና ታፈሰ ሰረካን ወደ ፊት በሚደረግ እንቅስቃሴ መጠቀም አንዱ አማራጩ ይሆናል። ሁለቱ ተጨዋቾች ይህን ለማድረግ የኢትዮጵያ ቡናን የመስመር አጥቂዎች ጫና ባገናዘበ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አስራት ቱንጆ እና እያሱ ታምሩ ወደ ኤልያስ ማሞ እና ሳምሶን ጥላሁን ያለቅጥ ከመቅረብ ይልቅ መስመራቸውን ጠብቀው በማጥቃት ለሳሙኤል ሳኑሚ ክፍተትን ቢፈጥሩ የተሻለ ይሆናል። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ቡና ከመስመር ተከላካዮቹ ሲያገኝ የማይታየውን ጥቅም ማካካስ ይችላል። መሀል ሜዳ ላይ በሚኖረው ፍልሚያም ዳዊት እስጢፋኖስ እና ኤልያስ ማሞ ኳስ በሚይዙባቸው አጋጣሚዎች የቡድን ጓደኞቻቸው በተመጠነ እና የተጋጣሚ ተከላካይ መስመር ቅርፅን በሚረብሽ እንዲሁም የማጥቃትን ፍጥነትን ለመጨመር በሚያስችል ርቀት ላይ መገኘት ይጠበቅባቸል፡፡

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– በሊጉ 25 ጊዜ የመገናኘት አጋጣሚ የነበራቸው ሁለቱ ክለቦች ለ8 ጊዜያት አቻ ሲለያዩ በ4ቱ መከላከያ በቀሪዎቹ 8 ጨዋታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና አሸናፊ ሆነዋል። በ25ቱ ጨዋታዎች ከተቆጠሩ 50 ግቦች ውስጥም መከላከያ የ20፣ ኢትዮጵያ ቡና የ30ው ባለቤቶች ናቸው።

– ባለፉት 10 የእርስ በእርስ ግንኙነቶች አንድ ጊዜ ብቻ አቻ ከመለያየታቸው በቀር በሌሎቹ ተሸናንፈዋል።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው የአመቱን ስድስተኛ ጨዋታውን እንደሚመራ ይጠበቃል። አርቢትሩ ከዚህ ጨዋታ በፊት 2 የቀይ እና 24 የቢጫ ካርዶችን አስመልክቷል።


የክፍል ሁለትን ሊንኩን በመጫን ያንብቡ | LINK

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *