ሪፖርት | የአልሀሰን ካሉሻ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ኤሌክትሪክን ከግርጌው አላቋል

በ18ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወራጅ ቀጠናው የሚገኑ ሁለት ክለቦች ሲያገናኝ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ኢትዮ-ኤክትሪክ አርባምንጭ ከተማን 1-0 አሸንፏል፡፡ ኤሌክትሪክ ከተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት በኃላ ሙሉ ሶስት ነጥብ መጨበጥ ችሏል፡፡ ጋናዊው አማካይ ካሉሻ አል-ሃሰን ከረጅም ሳምንታት በኃላ ግብ ማስቆጠር የቻለበት ጨዋታም ሆኖ አልፏል፡፡

ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈበት ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርግ ተጋጣሚው አርባምንጭ በበኩሉ ሲዳማ ቡናን በሜዳው ከረታበት ቡድኑ ውስጥ 3 ተጫዋቾችን ለውጧል፡፡ ኤሌክትሪክ ጫላ ድሪባን በግርማ በቀለ በመለወጥ የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ አምበል የቀኝ ተካላካይ ቦታን ሲይዝ በአርባምንጭ በኩል ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ፅዮን መርድ፣ ተከላካዩ ወርቅይታደል አበበ እና አጥቂው ዛካሪያስ ፍቅሬ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ተመልሰዋል፡፡ የዘካሪያስ በፊት አጥቂነት መሰለፉን ተክተሎ ተመስገን ካስትሮ ወደ ተከላካይነት ተሸጋግሯል፡፡

በመጀመሪያው 45 ሁለቱም ቡድኖች የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡ ሆኖም አርባምንጮች ከኤሌክትሪክ በተሻለ የግብ እድሎችን በአጋማሹ ፈጥረዋል፡፡ አዞዎቹ በ2ተኛው ደቂቃ ተመስገን ካስትሮ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት አምበሉ አማኑኤል ጎበና ከርቀት የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ በግቡ አና ወጥቷል፡፡ ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ታፈሰ ተስፋዬ የመታውን ኳስ ታካልኝ ደጀኔ ተደርቦ ሲያወጣ ፀጋዬ አበራ አርባምንጭን መሪ ማድረግ የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ የአጋማሹ ምርጥ የማግባት እድል የነበረው እንዳለ ከበደ ቢሆንም በሳጥኑ ውስጥ ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በማጥቃቱ ወረዳ በዝተው አለመገኘታቸው፣ የካሉሻ አል-ሃሰን ግራ አጋቢ ሚና እና ጨዋታን ያለመቆጣጠር ችግር ከአርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ አጋማሽ ብልጫ ጋር ተዳምሮ በኮትዲቯራዊው ዲዲዬ ለብሪ አማካኝነት ከፈጠሩት እድል ውጪ ይህ ነው የሚባል የማግባት ሙከራ አላደረጉም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች አንፃራዊ ብልጫ ሲወስዱ አዞዎቹ በእንቅስቃሴ ወርደዋል፡፡ በሰዓቱ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጥል በነበረው ዝናብ ታጅበው ኤሌክትሪኮች መሪ ለመሆን ያደረጓቸው ሙከራዎች ጥቂት ቢሆኑም የጠሩ የግብ እድሎች ግን ነበሩ፡፡ በ57ኛው ደቂቃ ለብሪ ለካሉሻ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ ጋናዊውን ግብ ጠባቂው ፅዮን ጋር ቢያገናኝ አጥቂው ሳይጠምባት ኳስ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ ጨዋታው ለበርካታ ደቂቃዎች ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳይደረግበት ቆይቶ በ78ኛው ደቂቃ ለብሪ ያገኘውን ቀላል እድል ሲያመክን የጨዋታው መገባደጃ ላይ ካሉሻ በሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ በመምታት ባስቆጠረውን ድንቅ ግብ ኤሌክትሪክ መሪ መሆን ችሏል፡፡ አርባምንጮች ከደቂቃ በኃላ አፀፋውን የመመለስ እድል ቢያገኙም የኤክትሪኩ ግብ ጠባቂ አቡ ሱሌማና ኳስ ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡

አሰልጣኝ አሸናፊ ወደ ቡድኑ ከመጡ በኃላ በተከታታይ ጨዋታዎች ኤሌክትሪክ ደካማ ጉዞ አድርጓል፡፡ ድሉን ተከትሎ ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጣውን መውጣት ባይችልም በ17 ነጥብ 14ኛ ነው፡፡ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው አርባምንጭ ከተማ በ16 ነጥብ ወደ ሊጉ ግርጌ ተመልሷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *