የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሸኛኘት ተደረገለት

በቡሩንዲ አሰተናጋጅነት በሚካሄደው ከ17 አመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ ረፋድ ወደ ቡሩንዲ ከማቅናቱ በፊት ዛሬ አመሻሽ ላይ ባረፈበት ብሉ ሳካይ ሆቴል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ፣ የስራ አስፈፃሚ አባል ኢንጂነር ቾል ቤል እና የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ በተገኙበት አሸኛኘት ተደርጎለታል።

በሽኝት መርሀግብሩ ላይ ንግግር ያደረገው የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በውድድሩ ታሪክ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግሯል። ” ከልጅነታችን የሀገርን አርማ መልበስ ህልማችን ነበር። ይህ ተሳክቶልናል ፣ ይህ ብቻውን ግብ አይደለም። ታሪክ መስራት አለብን ። ይህን ለማድረግ በቂ ዝግጅት ፣ ፍላጎት ፣ አቅም አለን። ታሪክ ለመስራት ተዘጋጅተናል።” ብሏል።

የቡድኑ አምበል እና አጥቂው አደም አባስ በበኩሉ ይህን እድል ስላገኙ ደስተኞች መሆናቸውን ገልጾ ከቡሩንዲ በጥሩ ውጤት እንደሚመለሱ ተናግሯል።

በመቀጠል የባንዲራ እርክክብ የተደረገ ሲሆን በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ቡድኑ ውጤት ይዞ እንዲመለስ የአደራ እና የመልካም እድል ምኞት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።


የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን 27 የሉዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ነገ ረፋድ 05:00 ላይ ወደ ቡሩንዲ የሚያቀና ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታውንም ከሱማሊያ ጋር ሚያዝያ 6 ቀን 08:00 ላይ የሚያደርግ ይሆናል ።

የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ 1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ባደረገለት በዚህ የሴካፋ ውድድር ላይ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የሚያስመዘግበው መልካም ውጤት ታንዛኒያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ አላፊ እንደሚያደርገው ተገልጿል ።

Leave a Reply