ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ19ኛ ሳምንት የሚያዚያ 3 ጨዋታዎች – ክፍል 1

በ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መሀከል አዳማ እና ጅማ እንዲሁም አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚካሄዱትን ሁለት ጨዋታዎች ጨምረን በክፍል 1 ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

አዳማ ከተማ ከ መከላከያ

በወላይታ ድቻ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ምክንያት በ18ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች አራፊ የነበረው አዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና የ 2-0 ሽንፈት የደረሰበትን መከላከያን ያስተናግዳል። በሜዳው ጥሩ ሪከርድ ያለው አዳማ ለመጨረሻ ጊዜ ወልዲያን አስተናግዶ 3-1 ካሸነፈ በኃላ ሲሆን መከላከያ የሚያገኘው ጦሩ በሁለተኛው ዙር ወደ ሶዶ ተጉዞ አንድ ነጥብ ይዞ ከተመለሰ በኃላ ሁለተኛው የሜዳ ውጪ ጨዋታው ይሆናል። ከመሪዎቹ በመጠኑ ራቅ ያለው አዳማ ከተማ ልዩነቱን ለማጥበብ ፤ ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኘው መከላከያም ራሱን ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለማስጠጋት በአዳማ አበበ ቢቂላው ጨዋታ እንደሚፎካከሩ ይጠበቃል።

አዳማ ከተማ ኤፍሬም ዘካሪያስን እና ሰራፌል ዳኛቸውን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ ልምምድ የተመለሰው ሚካኤል ጆርጅም ለጨዋታው ብቁ ባለመሆኑ ምክንያት አሁንም አይሰለፍም፡፡ መከላካያ ደግሞ ሽመልስ ተገኝ እና ምንይሉ ወንድሙን በቅጣት ሲያጣ ቴዎድሮስ በቀለን በጉዳት አያሰልፍም። 

ከሁለቱም ቡድኖች ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት በሚጠበቅበት በዚህ ጨዋታ ከምንይሉ ቅጣት እና ከአዳማ የመሀል ክፍል ጥንካሬ አንፃር መከላከያ አምስት አማካዮችን እንደሚጠቀም ይጠበቃል። ሆኖም አዳማ ከተጋጣሚው ይልቅ ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ላይ ፈጣን ሆኖ የሚታይበት መከላከያ ደግሞ ይበልጥ ለኳስ ቁጥጥር ቦታ የሚሰጥበት ጨዋታ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። በዚህ ረገድ የመከላከያ የኃላ ክፍል ወደ መሀል ሜዳ ሲጠጋ ለወጣቶቹ የአዳማ አጥቂዎች ፍጥነት የተመቸ ክፍተትን ላለመስጠት መጠንቀቅ ሲኖርበት የሁለቱ የመስመር አማካዮች እና የከንዓን ቀጥተኛ እንቅስቃሴም ሌላው ጦሩ ሊፈተንበት የሚችልባቸው ነጥቦች ናቸው። በአዳማ በኩል በዳዊት እስጢፋኖስ ላይ የተመሰረተውን የተጋጣሚውን የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ በማቋረጥ በኩል የነኢስማኤል ሳንጋሪ ሀላፊነት እጅግ ወሳኝ ይሆናል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ከ23 ጨዋታዎች መከላከያ 7 ጊዜ አሸንፎ የበላይነቱን ሲወስድ አዳማ ደግሞ በ6 ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል። ግብ በማስቆጠርም ረገድ መከላከያ በ18 ግቦች ቀዳሚ ሲሆን አዳማ 16 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተል።

– ቡድኖቹ እስካሁን አቻ ከተለያዩባቸው 7 ጨዋታዎች አራቱ የተመዘገቡት በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ነው። ከነዚህ መሀል ሶስቱ 0-0 ተጠናቀዋል።

– አዳማ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው መከላከያን ያሸነፈው በ2004 የውድድር ዘመን ነበር።

– በሜዳው ሽንትፈ ሲገጥመው የማይታየው አዳማ ከተማ ዘንድሮ ካስተናገዳቸው 8 ቡድኖች አራቱን አሸንፏል።

– ዘንድሮ በአምስት አጋጣሚዎች ወደ ክልል የወጣው መከላከያ አንዴ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፎ ወደ አዲግራት ካቀናበት ጨዋታ ብቻ ሶስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል።

ዳኛ

ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ይህን ጨዋታ ለመምራት ታመርጧል። ይርጋለም የተቋረጠውን የወልዋሎ ዓ.ዩ እና መቐለ ከተማን ጨዋታ ሳይጨምር በ6 ጨዋታዎች 17 የቢጫ እና 1 የቀይ ካርዶችን አሳይቷል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ጅማ አባ ጅፋር ከ መቐለ ከተማ

3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የቀመጡት ሁለቱ ቡድኖች የሚገናኙበት ይህ ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግባቸው ከሚጠበቁ የሳምንቱ ጨዋታዎች ቀዳሚው ነው። ሁለተኛውን ዙር በሽንፈት የጀመረው አባ ጅፋር ከፋሲል እና ከድሬደዋ ጨዋታ አራት ነጥቦች ቢያሳካም በሶስቱ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ ደካማው ጎኑ ነው። በተቃራኒው በአራት ግቦች አርባምንጭን ለረታው መቐለ ከተማ ከወልዋሎ የነበረው ጨዋታ መቋረጡን እና ቅዱስ ጊዮርጊስም ጨዋታ መተላለፉን ተከትሎ ከውድድር አጋማሽ እረፍት በኃላ ሁለተኛው ጨዋታው ይሆናል። ቡድኖቹ ነጥባቸውን ከሰላሳ በላይ በማድረስ በመጀመሪያ አመት ተሳትፏቸው ፉክክሩ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ከፍ ለማድረግ እርስ በእርስ የሚገናኙበትን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ወሳኝ ይሆናል።

በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ከሆነው የጅማ አባጅፋር አጥቂ ተመስገን ገብረኪዳን አለመኖር ውጪ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሰማ ሌላ የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና ባይኖርም የመቐለው ወጣት አማካይ ሀብታሙ ተከስተ ከክለቡ ጋር ያልተስማማባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ወደ ጅማ እንዳልተጓዘ ተሰምቷል።

በኦኪኪ አፎላቢ እና ቢስማርክ ኦፖንግ የሚመራ ስል የአጥቂ ክፍል ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ኳስ ወደ ሁለቱ አጥቂዎች የሚደርሱባቸውን መንገዶች በአግባቡ መቆጣጠር ይጠበቅባቸዋል። በጅማም ሆነ በመቐለ በኩል ያሉ የመስመር አማካዮች የመጨረሻ ዕድሎችን በመፍጠር ስኬታማ መሆናቸው ከጅማ አባ ጅፋሩ የአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው እንዲሁም የመቐለ ከተማው የሚካኤል ደስታ እና የዐመለ ሚልኪያስ ጥምረት በሜዳው ስፋት ለተከላካይ መስመራቸው ትልቅ ሽፋን የመስጠት ሀላፊነታቸው ከፍተኛ ነው። ከዚህ ባለፈ የመስመር ተከላላዮችም የመከላከል ሀላፊነት ሊነሳ የሚገባው ሲሆን የማጥቃት ባህሪ ያለው የጅማው የቀኝ መስመር ተከላካይ ኄኖክ አዱኛ እና የመቐለው ወሳኝ የግራ መስመር አማካይ አማኑኤል ገብረሚካኤል የሚገናኙበት የሜዳ ክፍል ትኩረትን የሚስብ ይሆናል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የመጀመሪያው ዙር የመቐለው ጨዋታ የባለሜዳው 1-0 አሽናፊነት ተመዝግቦበታል።

– እስካሁን በሜዳው አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠመው አባ ጅፋር በ9 አጋጣሚዎች ካስተናገዳቸው ቡድኖች ስድስቱን ድል አድርጓል።

– ከሜዳው ውጪ አንድ ሽንፈት ብቻ የቀመሰው መቐለ በአራት አጋጣሚዎች 1 እንዲሁም ሶስት ጊዜ ደግሞ 3 ነጥቦችን ይዞ ተመልሷል።

ዳኛ

ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው የሁለተኛ ዙር የዳኝነት ምደባውን በዚህ ጨዋታ ይጀምራል። ተፈሪ በመጀመሪያው ዙር በዳኛቸው 4 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ የቀይ ካርድ ያሳየ ሲሆን 19 የቢጫ ካርዶችንም መዟል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ደደቢት ከ ድሬዳዋ ከተማ

የአዲስ አበባ ስታድየሙ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እና ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን ቢያገናኝም ደደቢት ከሽንፈት ድሬደዋ ከተማ ደግሞ ከድል በኃላ የሚገናኙበትም ጭምር ነው። ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎቹ በሶስቱ ሽንፈት የቀመሰው እና በአዳማ ጨዋታ ላይ ከተገኘችው የኤፍሬም አሻሞ ግብ ውጪ ሌላ ማስቆጠር ያልቻለው ደደቢት በሊጉ አናት ተቀምጦ መቆየቱ ዕድለኛ ያደርገዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን ይህን ጨዋታም ተሸንፎም ቦታውን ላይለቅ ቢችልም በተለይ ተስተካካይ ጨዋታ ላላቸው ተከታዮቹ ተጨማሪ ዕድል መስጠቱ ግን አይቀሬ ነው። ዘንድሮ በሊጉ ሁለተኛውን ድል ለማግኘት 12 ጨዋታዎችን የጠበቀው ድሬደዋ ከተማ ሶስተኛውን አሸናፊነቱን ከሶስት ጨዋታዎች በኃላ ተጎናፅፏል። ደደቢትን መርታት ከቻለ ደግሞ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ ሲችል በሊጉ የመቆየት ህልሙን ማለምለምም ይታደላል።

በሀዋሳው ጨዋታ ላይ በ18ኛው ደቂቃ ጉዳት የገጠመው የደደቢቱ አጥቂ አቤል ያለው ከዚህኛውም ጨዋታ ወጪ ሆኗል። በድሬደዋ በኩል ደግሞ አትራም ኩዋሜ ፣ ጀማል ጣሰው እና ዘነበ ከበደ ጉዳት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።

ደደቢት ሰሞኑን እንደሚያደርገው ሁሉ ከፊት ሁለት አጥቂዎችን እንዳሚጠቀም ይገመታል። በመሆኑም በጨዋታው ተመሳሳይ ቅርፅ ይኖረዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ድሬደዋ ከተማ ጋር በቁጥር የተስተካከለ የአማካይ ክፍል ፍልሚያን እንድንጠብቅ ያደርገናል። በህዚህም መሰረት ኢማኑኤል ላርያን በተከላካይ አማካይነት ቦታ በማሰለፍ ለቀሪዎቹ ሶስት ኣማካዮች በተለይ ለዮሴፍ ዳሙዬ እና ዘላለም ኢሳያስ የተሻለ ነፃነት እንደሚሰጥ የሚታሰበው የድሬደዋ የመሀል ክፍል ከአስራት መገርሳ እና የአብስራ ተስፋዬ የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች ወሳኝ ይሆናሉ። በደደቢት በኩል ደግሞ ከዚህ በተለየ መልኩ በኢማኑኤል ላርያ ግራ እና ቀኝ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የመስመር አማካዮቹ ሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ ዋነኛ የማጥቃት አማራጮች ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– እስካሁን በሊጉ 11 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ 2 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ደደቢት 7ቴ ድሬደዋ ደግሞ 2ቴ አሸንፈዋል። ከተቆጠሩት 23 ግቦችም ደደቢት የ16ቱ ድሬደዋ ደግሞ የ7ቱ ባለቤቶች ናቸው።

– ቡድኖቹ አዲስ አበባ ላይ አምስቴ በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች በሙሉ ደደቢት አሸናፊ ነበር።

– ደደቢት 7 ጊዜ የክልል ቡድኖችን አስተናግዶ 4 ጊዜ አሸንፎ አንዴ ተሸንፏል።

– ሶስቴ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ድሬደዋ ከተማ ማሳካት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ነበር።

ዳኛ

ይህ ጨዋታ ድንቅ ዓመት እያሳለፈ ለሚገኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በሊጉ አምስተኛ ጨዋታው ይሆናል። በአምላክ እስካሁን 9 የቢጫ ካርዶችን ያሳየ ሲሆን በቀይ ካርድ ከሜዳ ያሰናበተው ተጨዋች ግን የለም።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

አምና ዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆነው እጅግ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ በሁለተኛው ዙር ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ በደረጃቸው 5ኛ እና 10ኛ ላይ ይገኛሉ። ከስድስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኃላ ፋሲል ከተማን ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ካራ ብራዛቪልን ከረታ በኃላ ወደዚህ ጨዋታ መምጣቱ ጥሩ የዐዕምሮ ደረጃ ላይ እንዲገኝ እንደሚያግዘው ይታሰባል። ሲዳማ ቡናም ወልዋሎን የረታበት የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ ከአምስት ጨዋታዎች በኃላ የተገኘ እና በሁለተኛው ዙር ለመጀመሪያ ጊዜ ጎሎች ያስቆጠረበትም ነበር። ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ4ኛ እና 5ኛው ሳምንታት በኃላ ተከታታይ ድል ለማግኘት ሲዳማ ቡና ደግሞ ከሜዳው ውጪ የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ለማሳከት የሚፋለሙበት ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሳላዲን ሰይድ በተጨማሪ የታደለ መንገሻን እና የአስቻለው ተመነን አገልግሎት እንደማያገኝ ተሰምቷል። በሲዳማ ቡና በኩል ግን የጉዳት ዜና ባይኖርም ከክለቡ ከተሰናበተ በኃላ ዳግም የተመለሰው ዮሴፍ ዮሀንስ በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የማይሰለፍ ብቸኛው ተጨዋች ይሆናል ፡፡

በዋነኛነት ከመስመር አጥቂዎቻቸው በሚነሳ ጥቃት ያሚታወቁት ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ከአማካይ ክፍል ፍልሚያው ይልቅ ከሜዳው የግራ እና ቀኝ ክፍሎች የሚነሱ ኳሶች ቀልብ ይስባሉ። መስመራቸውን ይዘው ሲያጠቁ የሚታዩት የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎች ወደ መሀል ያሚያሻግሯቸው ኳሶች የፈረሰኞቹ ዋነኛ የግብ ምንጭ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ሂደትም ውስጥ የዚሁ ስፍራ ተሰላፊዎች የሚኖራቸው ድርሻ ለሲዳማ የኃላ ክፍል ትልቅ ፈተና ነው። በተመሳሳይ ቦታ ላይ ከእንግዶቹ በኩል የሚነሱት አዲስ ግደይ እና አብዱለጢፍ መሀመድ ከአማካይ ክፍላቸው ከሚደርሳቸው ኳሶች በፍጥነት ወደ ውስጥ ለመግባት ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ የፈረሰኞቹን የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ የማፈን ሀላፊነት ይኖራቸዋል። በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ግን ዋነኛው የቡድኖቹ ትኩረት በማጥቃት ሽግግሮች ወቅት ለመስመር አጥቂዎች በሚላኩ ኳሶች ላይ እንደሆነ ይታሰባል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ የበላይ በሆነበት የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት በ17 ጨዋታዎች 26 ግቦች አስቆጥሮ 12ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎችም በአቻ ውጤት የተጣናቀቁ ነበሩ።

– ቅዱስ ጊዮርጊስን አንዴም አሸንፎ የማያውቀው ሲዳማ ቡና በ17ቱ ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው 5 ግቦች 4ቱን ያገኘው አዲስ አበባ ስታድያም ላይ ነው። በመጨረሻዎቹ 4 ጨዋታዎችም ግን ግብ ማስቆጠር አልቻለም።

– ዘንድሮ ሶስት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ሲዳማ ሁለት ጊዜ አንድ ነጥብ አሳክቷል።

– በስድስት አጋጣሚዎች የክልል ቡድኖችን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንዴም ሽንፈት ያልገጠመው ሲሆን ሶስት ጊዜ አሸንፏል።

ዳኛ

በ16ኛው ሳምንት በፋሲል ከተማ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ መሀከል ከተደረገው ጨዋታ በኃላ 8ኛ ጨዋታውን የሚዳኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይህን ጨዋታ የመራዋል። ብሩክ እስካሁን 28 የቢጫ ካርዶች እና 1 የቀይ ካርድ አሳይቷል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *