ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ19ኛ ሳምንት የሚያዚያ 3 ጨዋታዎች – ክፍል 2

በአርባምንጭ ፣ ወልዲያ እና ዓዲግራት ከተማዎች የሚደረጉት ሶስት የ19ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ሁለተኛ ክፍል ትኩረቶች ሆነዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በሜዳው በተከታታይ ነጥቦችን እየሰበሰበ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ በዋቅታዊ አቋሙ በሊጉ ቀዳሚው የሆነው ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስታናግድበት ጨዋታ በላይኛው እና በታችኛው የሰነጠረዡ ክፍል ላይ ለውጦች የማምጣት ሀይል ይኖረዋል። ሲዳማን አሸንፎ ከመጨረሻ ደረጃ ፈቀቅ ብሎ የነበረው አርባምንጭ በኢትዮ ኤሌክትሪክ የደረሰበት ሽንፈት ዳግም ወደ ግርጌው እንዲመለስ አድርጎታል። ድሬደዋም ወልዲያ ላይ ያስመዘገበው ድል አርባምንጭ ከቡና ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ግዴታ ውስጥ የሚከተው ሌላኛው ነጥብ ነው። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ በድል ከተመለሰ ወደ ደደቢት ለመጠጋት ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ ከሚጫወቱት አባ ጅፋር እና መቐለም ለመራቅ ትልቅ አጋጣሚ ይፈጥርለታል።

በአርባምንጭ ከተማ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በረከት ቦጋለ ከ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት በኃላ ይመለሳል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወደ አርባምንጭ ያልተጓዙት ጉዳት ላይ የሚገኙት አስቻለው ግርማ እና አለማየሁ ሙለታ ሲሆኑ ወንድይፍራው ጌታሁን በ5 ቢጫ እንዲሁም አስናቀ ሞገስ በቀይ ካርድ ቅጣት ላይ ይገኛሉ።

በአርባምንጭ ከተማ የአጥቂ አማካይነት ሚና የተሰጠው እንዳለ ከበደ የቡድኑ ዋነኛ የእንቅስቃሴ ማዕከል ነው። ተጨዋቹ ፍጥነት በታከለበት የማጥቃት ሽግግር ከአማኑኤል ጎበና እና ሌሎች ከጀርባው ካሉ ተጨዋቾች ጋር የሚያደርጋቸው ቅብብሎች ወደ መስመር አጥቂዎቹ ፀጋዬ አበራ እና ዘካርያስ ፍቅሬ ሲደርሱ አርባምንጭ የተሻለ ክፍተትን ሲያገኝ ይስተዋላል። በዚህ በኩል ቡድኑ በዘካርያስ አማካይነት አስናቀ ሞገስ ባለመኖሩ ሊሳሳ ወደሚችለው የኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር የመከላከል ክፍል አድልቶ እንደሚያጠቃ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ መከላከያን ያሸነፈበትን መንገድ አርባምንጭ ላይም እንዳሚተገብር ይጠበቃል። ድንቅ ብቃት ላይ በሚገኘው አማኑኤል ዮሀንስ መሪነት የተጋጣሚውን የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ በመስበር እና የሚገኙ ኳሶችን በቶሎ ለሳሙኤል ሳኑሚ በማድረስ ዕድሎችን የመፍጠር እቅድ እንደሚኖረው ይታሰባል። ቡድኑ ግብ ካስቆጠረ በኃላም በጥልቀት ባይሆንም የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም በሚያስችል አኳኃን መከላከልን እንደሚመርጥ ይታሰባል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– 13 ጊዜ እርስ በእርስ የተገናኙት ቡድኖቹ 4 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 15 ግቦችን ያስቆጠረው ኢትዮጵያ ቡና 5 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 4 ጊዜ ድል የቀናው አርባምንጭ 12 ግቦችን አስቆጥሯል።

– ኢትዮጵያ ቡና ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፎ መመለስ አልቻለም።

– ኢትዮጵያ ቡና ወደ ክልል ከወጣባቸው ስድስት ጨዋታዎች በመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ከተሸነፈ በኃላ አንዴ አቻ ወጥቶ ቀሪዎቹን ሁለቱን አሸንፏል።

– አርባምንጭ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ 1-0 ውጤት አሸንፏል።

ዳኛ

ጨዋታው ዘንድሮ በሊጉ 7 ጨዋታዎችን በዳኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው የመራል። በነዚህ ጨዋታዎች ዳዊት 4 የቀይ ካርዶችን ሲያሳይ በ29 አጋጣሚዎች ደግሞ የቢጫ ካርዶችን መዟል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ወልዲያ ከ ፋሲል ከተማ

በመጀመሪያው ዙር ማብቂያ ላይ ከተስተካካይ ጨዋታዎች የሰበሰባቸው ነጥቦች መነቃቃት ፈጥሮለት የነበረው ወልዲያ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሶስቱን በሽንፈት ደምድሟል። ክለቡ እስካሁን ያገኛቸውን ድሎች በሙሉ ሜዳው ላይ ከማሳካቱ አንፃር ከሀዋሳው የአቻ ውጤት በኃላ ወደ ሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲን ስቴዲየም መመለሱ ጥሩ ዕድል ይሰጠዋል። በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስር የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ፋሲል ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ ሁለት ድሎችን በተከታታይ ካሳካ በኃላ በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ ከዋንጫ ፉክክሩ ከወዲሁ እንዳይርቅ ስጋት የጣለበት ይመስላል። በመሆኑም ከጨዋታው የሚገኘው ነጥብ ወልዲያን ከወራጅ ቀጠናው የማራቁን ያህል ፋሲልንም ወደ መሪዎቹ ዳግም የሚያስጠጋው በመሆኑ የጨዋታውን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል።

ወልዲያ እጅግ በሳሳው የተጨዋች ስብስቡ ምክንያት እንዲሁም ፋሲል ከተማ በአዲስ አሰልጣኝ ስር ከመሆኑ አንፃር የዚህን ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መገመት ከባድ ይሆናል። ሆኖም ወልዲያ በማጥቃቱ ከነብሩክ ቃልቦሬ እና ሀብታሙ ሸዋለም በረጅሙ በቀጥታ ለአንጋፋው አጥቂ አንዷለም ንጉሴ በሚላኩ ኳሶች ላይ እንደሚመረኮዝ ይታሰባል። የፋሲል ከተማው የሰንደይ ሙቱኩ እና ከድር ኸይረዲን ጥምረትም እነዚህን ኳሶች ከግብ ክልሉ የማራቅ ሃላፊነት ይጣልበታል። በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ፋሲሎችም የመስመር አጥቂዎቻቸውን ጉዳት ተከትሎ እንደሁለተኛ ዕቅድ የሚጠቀሙበትን የአምስት አማካዮች አሰላለፍ ጥቅም ላይ በማዋል በተጋጣሚያቸው ላይ የመሀል ሜዳ የበላይነት ለመውሰድ እንደሚሞክሩ ይገመታል። ከሁሉም በላይ ግን የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥት በቡድኖች ላይ የሚፈጥረው ተነሳሽነት ፋሲል ይታወቅበት በነበረው እና እየተቀዛቀዘ በመጣው ድንገተኛ እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ መሻሻሎችን ሊያመጣለት እንደሚችል ይታሰባል።

ወልዲያ ምንያህል ተሾመን በቅጣት ሲያጣ ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ ከነበሩ ተጨዋቾች ላይ አማረ በቀለ እና ተስፋዬ አለባቸው ተጨምረዋል። አይናለም ኃይለ ፣ አብዱራህማን ሙባረክ እና ያሬድ ባዬ በጉዳት ራምኬል ሎክ በቅጣት ወደ ወልዲያ ያልተጓዙ ሲሆን የመሀመድ ናስርም የመሰለፍ ጉዳይ እርግጥ አይደለም።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምና ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያውን ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ሲለያዩ በሁለተኛው ዙር አአ ላይ በተደረገ ጨዋታ ፋሲል ከተማ 1-0 አሸንፏል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ጎንደር ላይ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

– ዘንድሮ ሜዳው ላይ ባደረጋቸው 8 ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ወልዲያ በግማሹ አሸንፏል።

– ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ ያደረጋቸውን የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሽንፈት ደምድሟል።

ዳኛ

ዘንድሮ በርካታ ጨዋታዎችን ከዳኙ አልቢትሮች መሀከል አንዱ ለሆነው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ የወልዲያው ጨዋታ 9ኛው ይሆናል። በእስካሁኑ ሪከርዱ ግን 33 የቢጫ እና 2 የቀይ ካርዶችን መዟል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ወልዋሎ ዓ.ዩ.ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነው ዓዲግራት ላይ የሚገናኙት ክለቦች ራሳቸውን በሊጉ ለማቆየት በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ከሆኑ ጨዋታዎች መሀከል አንዱን ያደርጋሉ። በመሀላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ መኖሩም በዚህ ወቅት እርስ በእርሳቸው የመገናኘታቸውን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል። ተከታታይ ሶስት ሽንፈቶች የገጠሙት ወልዋሎ ሊጉን ከመምራት የተነሳው መንሸራተቱ ቀጥሎ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቃምጧል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም በካሉሻ አልሀሰን የግል ብቃት አርባምንጭ ከተማን ማሸነፉ እስትንፋስ ቢሰጠውም አሁንም ከለመደው የወራጅ ቀጠና ጨርሶ ለመውጣት ተመሳሳይ መልክ ያለውን ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይለዋል።

ብርሀኑ አሻሞ በቅጣት እንዲሁም በረከት ተሰማ በጉዳት ከጨዋታ ውጪ የሆኑ የወልዋሎ ተጨዋቾች ሲሆኑ የኤሌክትሪኮቹ ጥላሁን ወልዴ ፣ ሄኖክ ካሳሁንና እና ምንያህል ይመርም ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

የነጥብ መጠጋጋቱ ከሚፈጥረው ውጥረት አንፃር ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥር ቡድን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጥንቃቄን መርጦ ውጤቱን ለማስጠበቅ እንደሚጫወት ቢታሰብም የኢትዮ ኤሌክትሪክ አቀራረብ ከጅምሩም ተመሳሳይ የጥንቃቄ መልክ እንደሚኖረው መናገር ይቻላል። በሶስትዮሽ የአማካይ ክፍሉ በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ የሚያጠቃው ወልዋሎ ዓ.ዩ ዛሬም በተመሳሳይ ዕቅድ በዋነኝነት ከድር ሳሊህ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆን የጥቃቱ መነሻ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ወደ ራሱ ጎል በጥልቀት የሚሳበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካይ መስመር የሁለቱን የመስመር አጥቂዎች ወደ መሀል እየጠበበ የሚመጣ ጥቃት የመመከት ፈተና ይኖርበታል። ለኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በመሰል ጨዋታዎች ወደ ተከላካይ አማካዩ ቀርቦ እንዲጫወት የሚገደደው ካሉሻ አልሀሰን በግሉ ተጨዋቾችን በማለፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ለታፈሰ ተስፋዬ እንዲሁም ዲዲዬ ለብሪ የሚያደርሳቸው ኳሶች ከጀርባው ሰፊ ክፍተት የሚተወው የወልዋሎ የተከላካይ መስመር ዋናኛ ትኩረቶች ይሆናሉ።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ በሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋናኙበት የአዲስ አበባው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በወልዋሎ ዓ.ዩ የ 3-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

– ከሜዳው ውጪ የተሻለ ሪከርድ ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ክልል ከወጣባቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሶስቱ የአቻ ውጤትን አሳክቷል።

– ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ4ኛው ሳምንት በኃላ ካገኛቸው 10 ነጥቦች 9ኙን የሰበሰበው ዓዲግራት ላይ ነው።

ዳኛ

የሁለተኛውን ዙር መክፈቻ ሁለት ጨዋታዎች ዳኝቶ በ18ኛው ሳምንት አራፊ የነበረው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ለዚህ ጨዋታ ተመርጧል። ቴዎድሮስ 4 የቀይ እና 37 የቢጫ ካርዶችን በ8 ጨዋታዎች ላይ አሳይቷል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *