ሪፖርት | የኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ አሸናፊነት በአርባምንጭ ተገትቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛው ሳምንት በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተላቀቀበትን ድል አስመዝግቧል።

ከጨዋታው አስቀድሞ እጅግ በርካታ ተመልካቾች ስታዲየሙን ሞልተው የታዩ ሲሆን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ውጤት ክለቡ በመራቁ ምክንያት ከክለቡ ርቀው የነበሩ የአርባምንጭ ደጋፊዎች ዳግም ወደ ሜዳ በመመለስ በስቴዲየሙ ደምቀው ታይተዋል።  ከአዲስ አበባ ረጅም ርቀትን ተጉዘው የመጡት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በክለባቸው ውጤት ማጣት ሳይበግራቸው በህብረ ዝማሬያቸው ሜዳውን አድምቀው የታዩበት ነበር። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ ፣ የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር እና የጋሞጎፋ ዞን አስተዳደር ለአርባምንጭ የገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል።

ባሜዳዎቹ አርባምንጮች በኤሌክትሪክ በተረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ መካከል በረከት አዲሱን በዘካሪያስ ፍቅሬ ምትክ ፣ ከቅጣት የተመለሰው በረከት ቦጋለን በአንድነት አዳነ ምትክ በማሰለፍ በ4 5 1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች መከላከያን ከረቱበት ጨዋታ ወንዲፍራው ጌታሁንን በኤፍሬም ወንድሰን፣ አስራት ቱንጆን በአቡበከር ነስሩ ተክተው በ4 3 2 1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው መሪነት ሰአቱን ጠብቆ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎችን ጥንቃቄ ላይ ትኩረት ያደረገ እንብስቃሴን ተመልከነናል። የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚን በመፍጠሩ ረገድ ደግሞ አዞዎቹ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን በ2ኛው ደቂቃ ላይ በረከት አዲሱ የሰጠውን ኳስ አጥቂው ብርሀኑ አዳሙ ሞክሮ ሀሪሰን ሄሱ አድኖበታል። ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ የታየው በ38ኛው ደቂቃ ላይ በረከት አዲሱ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታበታለች።
በእንግዳው ቡድን ኢትዮጵያ ቡና በኩል ሳኑሚ የግል ጥረቱ የአርባምንጭ የተከላካይ መስመርን ለመረበሽ ከሚያደርገው ጥረት ውጪ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ መፍጠር ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ስኬታማ የሆነበት ፤ ኢትዮጵያ ቡና ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ለመድረስ ያልተሳካ ጥረት ያደረጉበት ነበር። በ50ኛው ደቂቃ ላይ በእንዳለ ከበደ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት አማኑኤል ጎበና በአግባቡ ሲያሻግሯት ፀጋዬ አበራ ጋር ደርሳ የመስመር አጥቂው ከመረብ በማሳረፍ አርባምንጭን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ አዞዎቹ ይበልጥ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ መስዑድ መሀመድ እና ኤልያስ ማሞን ካስገቡ በኃላ ኳስን በመቆጣጠር የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በሚቆራረጡ ኳሶች ምክንያት ግን ወደ ግብ በአግባቡ መድረስ አልቻሉም። ይልቁንም ለአርባምንጮች የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲያጋልጣቸው ታይቷል።

በመጨረሻወቹ ሰላሳ ደቂቃዎች ግቧን አስጠብቆ ለመውጣት አርባምንጮች መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን በሚገኙ አጋጣሚዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በ76ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶ መሪነታቸውን ማስፋት ችለዋል። ጎሉም አምበሉ አማኑኤል ጎበና የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ወደ ሳጥን በመግባት ቶማስ ስምረቱን በማታለል ግሩም ግብ በማስቆጠር የተገኘ ነበር።

ከዚህ ጎል በኃላ  ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ግብ ከመድረስ ይልቅ የተስፋ መቁረጥ ምልክት ሲተታይባቸው ለማጥቃት ያደረጉት ፍላጎትም ወርዶ ታይቷል። በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በብስጭት ስሜት ሜዳውን ለቀው ሲወጡም ታዝበናል። አርባምንጮች ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ የተቀረውን ደቂቃ በመከላከል ላይ አመዝነው በመጫወት 2-0 አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

አስተያየቶች

አሰልጣኝ እዮብ ማለ – አርባምንጭ

እንደተመለከታቹት ክለቡ ቀስ በቀስ ወደ ሪትም እየገባ ነው ፤ ቅረፁን ለመያዝም እየሞከረ ነው፡፡ኢትዮጵያ ቡናዎች ትልቅ ቡድን እንደመሆናቸው ይህንን ጨዋታ ማሸነፋችን በራስ መተማመናችንን ያሳድግልናል፡፡ ኳስን ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል ፤ ውጤቱም ይገባናል።
ደጋፊዎች ልክ እንደዛሬው ሁሌም ከጎናችን እንዲሆኑ እንፈልጋለን። በውጤቱ እጅግ እጅግ ደስተኛ ነኝ። አርባምንጭ ይወርዳል ለሚሉትም መልስ ነው።

አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ

በጨዋታው ጥሩ ለመንቀሳቀስ ምክረናል። ተጋጣሚዎቻችን ኃይልና ጉልበት የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ሲያደረጉ ተመልክታችኋል፡፡ ይህ ደግሞ ለኛ ከብዶን ነበር። ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጠን የሚገቡ ዕድሎች ነበሩ ፡፡ ተከላካዮቼ በዛሬው ጨዋታ ስህተቶችን ሲሰሩ ነበር። ጎሎቹም በዚህ ምክንያት የመጡ ናቸው፡፡ አሁን የሊጉ ተፎካካሪ ሆነን ይህንን ውጤት ማምጣታችን አበሳጭቶኛል፡፡ ደጋፊውንም ይቅርታ እጠይቃለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *