ሪፖርት| ቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሃግብር የመጀመሪያ ቀን የመጨረሻ ጨዋታ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሜ መሀመድ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በመታገዝ ከመሪው ደደቢት ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሶስት ነጥብ አጥብቦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ቅዳሜ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ የቡድን ተሰላፊ ተጫዋቾች ውስጥ ግብ ጠባቂውን ሮበርት ኦዶንካራን አሳርፈው ለአለም ብርሃኑን ከተኩበት ቅያሬ በስተቀር ተመሳሳይ ተጫዋቾችን ተጠቅመዋል፡፡ በአንጻሩ ሲዳማ ቡናዎች በ18ኛው ሳምንት መርሃግብር ወልዋሎን ከረታው የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ውስጥ በ5 ቢጫ ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ቡድኑን ማገልገል ያልቻለውን ዮሴፍ ዮሀንስን በወንድሜነህ አይናለም ብቻ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡
ከጨዋታው መጀመር በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በቅርቡ በኩላሊት ህመም እየተሰቃየ የሚገኘውን ታዳጊውን ክለቡ ደጋፊ ዘካሪያስ ተፈሪን በማሰብ የልጁ ስምና ፎቶ የታተመበትን ነጭ ቲሸርት በመልበስ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የቅዱስ ጊዮርጊሰ የሰፓርት ማህበር ለታዳጊው ዘካሪያስ ህክምና ይረዳ ዘንድ የ100ሺህ ብር ድጋፍ ሲያደርግ በተመሳሳይ የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀል በግላቸው የ200ሺህ ብር ድጋፍ እና ለህክምና ወደሚያቀናበት ሀገር የሚሆን የደርሶ መለስ የአውሮፕላን ትኬት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንቅስቃሴ በአመዛኙ ወደ ሲዳማ ቡና የሜዳ ክፍል አጋድሎ የተካሄደ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊሶች የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ ግብ እድሎች መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች አልፎ አልፎ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ ከሚላኩ እና ኢላማቸውን ካልጠበቁ ኳሶች በስተቀር ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በሲዳማ ቡናዎች በኩል ፊት ላይ በመጨረሻ አጥቂነት ከተሰለፈው ባዬ ገዛኸኝ በስተቀር የቀሩት የቡድኑ ተጨዋቾች በጥሩ ሁለት የመከላከል መስመሮች ሲከላከሉ ተስተውሏል። ኳሶችን በሚያገኙበት ወቅት ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎቻቸውን ማለትም አዲስ ግደይን እና መሀመድ አብዱለቲፍን በመጠቀም አልፎ አልፎ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል፡፡

ጨዋታው የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማስተናገድ 36 ያክል ደቂቃዎችን አስጠብቋል። በዚሁ ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የግራ መስመር ተከላካይ መሃሪ መና ከግራ መስመር ሰብሮ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ከደረሰ በኃላ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ፍቅሩ ወዴሳ በሚገርም ሁኔታ አድኖበታል። በዚህች ሙከራ ከተገኘችው የማእዘን ምት በሀይሉ አሰፋ ያሻማውን ኳስ ከሰሞኑ ጥሩ እንቅስቃሴ እያረገ የሚገኘው አሜ መሀመድ በሲዳማ ቡና ተጫዋቾች መዘናጋት ታግዞ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ ያረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ የጨዋታ መንፈስ ላይ መነቃቃት ተስተውሏል ፤ በተለይ ሲዳማ ቡናዎች በ38ኛው እንዲሁም በተጨማሪ ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብጠባቂ ለአለም ብርሃኑ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከናቸው ሁለት ወርቃማ አጋጣሚዎች በአጠቃላይ የጨዋታውን መንፈስ መቀየር የሚችሉ ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ እየተመሩ ወደ መልበሻ ቤት አቅንተው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለቀቀ ብለው መቅረብ ችለዋል፡፡ ይህም ለቅዱስ ጊዮርጊሶች የተመቸ ይመስላል። በዚሁ አጋማሽ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው በተሻለ በቀጥተኛ አጨዋወት በተደጋጋሚ የሲዳማን የመከላከል አደረጃጀት መፈተን ችለዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ በነበሩበት የሁለተኛው አጋማሽ በተለይ በ58ኛው እንዲሁም በ61ኛው ደቂቃ ላይ በጋዲሳ መብራቴ እና አሜ መሀመድ ጥሩ የሆኑ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በሲዳማ ቡናዎች በኩል በ72ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻማውን የቅጣት ምት የመሀል ተከላካያቸው አበበ ጥላሁን በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡
ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊሶች 1ለ0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን ወደ 30 ከፍ በማሳደግ መሪዎቹ ላይ ጫና ማሳደሩን ቀጥሏል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት
ቫዝ ፒንቶ- ቅዱስ ጊዮርጊስ

ይህንን ድል መታሰቢያነቱን ለታዳጊው ደጋፊያችን ዘካሪያስ ተፈሪ ይሁንልኝ፡፡ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር፤ ተጋጣሚያችን ሲዳማ ቡና ጥሩ መጫወት ችለዋል፡፡ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች መሀል ሜዳ ላይ የኛ ተጫዋቾችን ጫና ውስጥ በመክተት እንደፈለግነው እንዳንጫወት አድርገውናል፡፡ ቢሆንም ግን ዋነኛ አላማችንን ማሳከት በመቻላችን በጣም ተደስተናል፡፡

 

ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

በሁለቱም አጋማሾች የተሻልን የነበርን ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከኛ በተሻለ ያገኙትን አንድ አጋጣሚ በመጠቀማቸው ሊያሸንፉ ችለዋል፤ ከእነሱ በተሻለ ወደ ጎል መድረስ ብንችልም ያገኘናቸውን እድሎች መጠቀም ባለመቻላችን ተሸንፈናል፡፡ ሽንፈቱ ግን በጭራሽ አይገባንም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *