ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ

ትናንት ሰባት ጨዋታዎች የተደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ሶዶ ላይ አንድ ጨዋታ ይስተናገድበታል። የዛሬው ዳሰሳችን ትኩረትም የሄው ብቸኛ ጨዋታ ይሆናል።

ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ የሚገኙበት የ8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ከትናንቱ ጨዋታዎች በኃላም አልተቀየረም። ከሜዳው ወጥቶ ጨዋታ ካደረገ 45 ቀናት ያስቆጠረው ወላይታ ድቻ ሳምንት አዳማ ላይ ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ መተላለፉ የሚታወስ ነው። ከዚያ አስቀድሞ ግን በሜዳው ከመከላከያ ነጥብ ከመጋራቱ ውጪ ወልዲያን እና ደደቢትን መርታት ችሏል። በሁለተኛው ዙር በሶስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ያሳካው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ አሁንም ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ ቢቸገርም ከሰንጠረዡ አጋማሽ ግን አልወረደም። ከ14ኛው ሳምንት በኃላ ምንም ሽንፈት ያልገጠማቸው ሁለቱ ቡድኖች ከመሀል ሰፋሪነት ተላቀው ወደ ዋንጫ ተፎካካሪዎቹ በጥቂቱም ቢሆን ለመጠጋት እንደዛሬው እርስ በእርስ የሚገናኙባቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ የግድ ይላቸዋል። ይህ በመሆኑም ጨዋታው ለማሸናነፍ የሚደረግ ጥሩ ፉክክርን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻ ጉዳት ላይ የሚገኙትን እርቂሁን ተስፋዬ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ዳግም ቀለምን አገልግሎት አሁንም የማያገኝ ሲሆን ጅብሪል አህመድ በህመም ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ በቤተሰብ ችግር እንዲሁም ያቡን ዊሊያም በጉዳት ከጨዋታው ውጪ የሆኑ የሀዋሳ ከተማ ተጨዋቾች ናቸው።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ከሀዋሳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ውጤታማነቱ መቀነሱ የሜዳዎች ጥራት መጓደል ቡድኑ ከሚከተለው አጨዋወት ጋር አብሮ ባለመሄዱ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ዛሬ ተመሳሳይ ፈተና ከፊቱ ተጋርጧል። ለአጫጭር ቅብብሎች ምቹ ያልሆነው የሶዶ ስታድያም የመጫወቻ ሜዳ ለሀዋሳ ከተማ አማካዮች ከነአብዱልሰመድ ዓሊ እና ሀይማኖት ወርቁ የድቻ የመሀል ክፍል ጥምረት ተጨማሪ ችግር ይሆንበታል። ከሁኔታው አንፃርም ለሀዋሳ መሀከለኛ ርዝመት ያላቸው እና ለፊት አጥቂው እስራኤል እሸቱ የሚደርሱ ኳሶች አማራጭ የጥቃት ምንጭ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ወላይታ ድቻዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በቀላሉ ማግኘት ባይችሉም ጥሩ የማጥቃት ተሳትፎ ካላቸው የሀዋሳ የመስመር ተከላካዮች ጋር በሚገናኙት የመስመር አማካዮቻቸው እንቅስቃሴ መነሻነት የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አማራጭ ይኖራቸዋል። ይህ እንዲሆን ግን በመከላከል ወቅት የሚነጥቋቸውን ኳሶች በተሻለ ፍጥነት ከወገብ በላይ ላሉ ተሳላፊዎቻቸው ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2006 ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች 9 ጊዜ ተገናኝተው ድቻ 5 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሀዋሳ ከተማ 1 አሸንፏል። በ3 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 10 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 5 አስቆጥሯል።

– በዘንድሮው የውድድር አመት የመጀመርያ ዙር ሀዋሳ ከተማ በያቡን ዊልያም ጎል ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው ድሉ ነው።

– በድቻ ሜዳ ላይ እስካሁን ባደረጓቸው 4 ጨዋታዎች ሶስቱን ድቻ ሲያሸንፍ አንዱን አቻ ተለያይተዋል።

– ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች 4 የአቻ ነጥቦችን ሲያሳካ 5 ጊዜ ተሸንፏል።

– ወላይታ ድቻ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው የመጨረሻ 6 ጨዋታዎች 5ቱን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ግብ ካስተናገደውም በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው።

ዳኛ

በመጀመሪያው ዙር ሁለት ጨዋታዎችን ዳኝቶ 8 የቢጫ ካርዶችን የመዘዘው ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንዲመራ ተመድቧል።