ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | ካራ ብራዛቪል በሜዳው…

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እየተካፈለ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን አዲስ አበባ ላይ ከኮንጎ ብራዛቪሉ ክለብ ካራ ብራዛቪል ጋር ተጫውቶ አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ካሸነፈ በኋላ የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ዛሬ ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡

የብራዛቪሉ ክለብ ካራ ከጊዮርጊስ ጋር ላለው ሁለተኛ ዙር ያለፈው ባለፈው የካቲት ወር የጋና ኩማሲውን ክለብ አሳንቴ ኮቶኮን በደርሶ መልስ አቻ ውጤት ከዛም በመለያ ፍጹም ቅጣት ምቶች አሸንፎ ሲሆን በተለይ በብራዛቪል የተካሄደው የመልስ ጨዋታ እጅግ ብዙ ወከባና ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ድርጊቶች እንደነበሩበት ብዙ የጋና ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ እኛም ቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ይወስድት ዘንድ ጽፈነዋል፡፡

የኩማሲው ክለብ በሜዳው ያደረገውን ጨዋታ ሶስት የፍጹም ቅጣት ምቶች አምክኖ አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ካሸነፈ በኋላ ለመልስ ጨዋታ ወደብራዛቪል ሲያቀና የካራ ደጋፊዎች በሆቴልና በስታዲየም በሮች ላይ ተጫዋቾችን ከማዋከብ ባሻገር የልምምድ ሜዳ በመከልከል ክለቡ መረጋጋት እንዳይሰማው አድርገውት ነበር፡፡ ምንም እንኳ የካፍ ህግ አንድ ሃገር ወይም አንድ ክለብ ለአህጉራዊ ውድድር ወደሌላ ሃገር ወይም ክለብ ሲያቀና በተለይ ከጨዋታው 24 ሰዓት በፊት ጨዋታውን በሚያደርግበት ሜዳ ላይ ልምምድ የመስራት መብት እንዳለው ቢደነግግም በካራ ግን የሆነው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የካራ ደጋፊዎች የኮቶኮ ተጫዋቾችን ወደስታዲየሙ ገብተው ልምምድ እንዳይሰሩ የስታዲየሙን በራፍ ዘግተው ለረጅም ሰዓታት ያንገላቱአቸው ሲሆን በመጨረሻም ወደስታዲየሙ ገብቶ ልምምድ ለመስራት በኮንጎ የጋና አምባሳደር የሆኑት የአምባሳደር አታ ቡአፎ ጣልቃ ገብነት አስፈልጓቸው እንደነበር አሰምፓና ኤዶም የተባሉ የኤፍ. ኤም. ጣቢያዎች ዘግበውታል፡፡

ከዚህም ባሻገር የኮቶኮ ተጫዋቾች ከሆቴል ወደስታዲየም ይጓጓዙበት የነበረውን የክለቡን መኪና በቆሻሻና በዘይት በተለይም መጥፎ ጠረን ባላቸው ምግቦች፣ የአሳና የአሳማ ስጋ እንዲሁም የመኪናውን የውስጥ መቀመጫዎች ምግብ በመቀባትና በመቀመጫ ስር በማስቀመጥ ተጫዋቾችን ምቾት እንዳይሰማቸው አድርገዋቸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡

በጨዋታው ዕለት ከሆቴል ወደስታዲየም የሚሄዱበት አውቶቡስ ባለማቅረብም የኮቶኮ ተጫዋቾች የጋና ኤምባሲ ባቀረበላቸው ሁለት V8 መኪኖች መሄዳቸውን ክለቡ በኦፊሻል የትዊተር ገጹ አስነብቦ ነበር፡፡ ክለቡ እንደተናገረው ይህን ሁሉ በደል ለካፍ ያመለከተ ቢሆንም የካፍ ውሳኔ ሳይሰጥበት ክለቡ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ ቀደም በ1999 ከሌላው የሀገሪቱ ክለብ ቷል ደ ኮንጎ ጋር ሲጫወትም ተመሳሳይ እንግልት ደርሶበት እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡