የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አጫጭር ዜናዎች እና የዝውውር መረጃዎች

የሁለተኛ ዙር ተራዝሟል

የከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ዙር ሚያዝያ 13 ይጀምራል ተብሎ የነበር ቢሆንም የቀን ለውጥ ተደርጎበታል፡፡ አዲስ የወጣው የሁለተኛ ዙር መርሀ ግብር መሰረት 16ኛ ሳምንት ሚያዝያ 20 እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።


የኦሮሚያ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን

የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስብሰባ አርብ በአዳማ ተካሂዷል፡፡ 4:00 ሰዓት ላይ ተጀምሮ አመሻሽ ላይ የተጠናቀቀው ይህ ስብሰባ በ3 የእግር ኳስ ውድድር እርከን ላይ ያሉትን ቡድኖችን ያማከለ ነበር፡፡ ክለቦች የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የሁለተኛ ዙር ዕቅድ እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን በቀጣይነት በክልሉ ያሉት ቡድኖች ባሉት ውድድሮች ያለውን ተሳትፎ በጥንካሬ እንዴት መወጣት አለባቸው የሚል ሀሳብ ላይ ተወያይተዋል፡፡ የስፖርቱ ማህበረሰብ ከቡድኖች ጋር ያለውን ትስስር ሰፊ ሽፋን ያገኘ ሲሆን ከዚ ውስጥ በስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ላይ ስለሚታዩ ባህርያት እርምት እና ስነስርአት አያያዝ በስፋት ውይይት ተደርጎበታል።


የደሴ ከተማ

ከ2 ሳምንት በፊት አሰልጣኙን ያሰናበተው ደሴ ከተማ በዋና አሰልጣኝ እና ምክትል አሰልጣኝነት ባወጣው ማስታውቂያ መሰረት የመጨረሻ ሶስት እጩዎችን ለይቶ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ከእጩዎቹ መካከልም ኃይለየሱስ ጋሻውን በዋና አሰልጣኝነት ፣ በምክትል አሰልጣኝነት ደግሞ ብርሀኑ ተፈራ ሆነው ተሹመዋል፡፡

አማራ ውሀ ስራ

በውድድር አመቱ መጀመሪያ ላይ ከዋና አሰልጣኙ አብርሀም ጋር የተለያየው እና በምክትሉ መኮንን ተመርቶ መጀመሪያውን ዙር ጨዋታ በ9ኛ ደረጃ ላይ ያጠናቀቀው አማራ ውሃ ስራ አዲስ አሰልጣኝ ቅጥር በመፈፀም መኮንን ገብረዮሐንስን በዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩን ይፋ አድርጓል። አሰልጣኙ ከዚ በፊት በኢትዮጵያ ውሃ ስራ፣ በዳሽን ቢራ እና በጅማ አባጅፋር ውጤታማ ጊዜያቶችን ያሳለፈ አሰልጣኝ ነው፡፡


የተጫዋቾች ዝውውር

ባህርዳር ከተማ

የምድብ ሀ መሪ ባህርዳር ከተማ ሁለት የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾችን አስፈረርሟል፡፡ አቤል ውዱን ከፋሲል ከተማ እንዲሁም የቀድሞ የቡድኑ ተጫዋች የነበረው ተስፋሁን ሽጋውን ከወልዲያ አስፈርሟል። በተጨማሪም በዘንድሮ አመት ከለገጣፎ ለገዳዲ ወደ ባህርዳር ያቀናው ፍፁም ክፍሌ እና ከሀድያ ሆሳዕና የመጣው ያለው ፋንታሁን ከቡድኑ ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።


ሽረ እንደስላሴ

በምድብ ሀ የመጀመሪያውን አጋማሽ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ሽረ እንደስላሴ የቀድሞው የደደቢት ድንቅ አማካይ ዮናስ አርአያን ከቡራዩ፣ ግብ ጠባቂው ሐብቶም ቢሰጠኝን ከአአ ከተማ ወደ ቡድኑ የቀላቀለ ሲሆን ኪኒአርቢ እንድሪስ እና በፍቃዱ አለሙ በስምምነት ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል።


ኢኮስኮ

በምድብ ሀ በ 8ኛ ደረጃ ላይ ከመሪው በ12 ነጥብ ዝቅ ብሎ 20 ነጥብ ሰብስቦ የሚገኘው ኢኮስኮ በከፍተኛ ሊጉ 7 ግቦች ያስቆጠረው በላይ ያደሳን ከመቂ አስፈርሟል፡፡ ከፋሲል ከተማ ጋር የተለያየው ኄኖክ አወቀም ሌላው ለክለቡ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡


ናሽናል ሴሜንት

በምድብ ለ 16 ነጥቦችን ሰብስቦ 12ኛ ደረጃ ላይ የጠቀመጠው ናሽናል ሴሜንት ከድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂው ሀሚድ ቶፊቅ እና አጥቂ ው ወሊድ ቶፊቅ አስፈርሟል፡፡


ያሬድ አበጀ

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ መንሸራተትን ያሳየው የምድብ ለ ተሳታፊው ሻሸመኔ ከተማ ከአሰልጣኙ ያሬድ አበጀ ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡ በክለቡ ያለፉትን ሁለት አመታት ከአሰልጣኝ ሚሊዮን አካሉ ተረክቦ ሲሰራ የቆየው የቀድሞው የባንኮች እና ሀዋሳ ከተማ አጥቂ በሻሸመኔ ከተማ የዘንድሮው ውጤት ማሽቆልቆል እና በክለቡ ውስጥ ያለው ስሜት ተቀዛቅዟል በሚል ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ባደረጉት ስምምነት ተያይተዋል፡፡


ቅሬታ

ከመጋቢት 20 ጀምሮ እገዳ ላይ የሆነው አሰልጣኝ ነፃነት ከብሬ በነገሌ ከተማ የቀረበትን እገዳ አስመልክቱ ቅሬታውን በሁለት ገልፅ አባሬ ደብዳቤ አስደግፎ ለኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌደረሽን ማስገባቱ የታወቀ ሲሆን ክለቡ በዚኛው ሳምንት ከአሰልጣኝ ነፃነት ጋር ያለውን ያለውን ነገር እንደሚሳውቅ ገልጧል።


አምበሪቾ ከ ሀላባ

በ8ኛው ሳምንት የተቋረጠው ጨዋታ ቀሪው 40 ደቂቃ በአዋሳ ስታዴዮም በሚያዝያ 11 ቀን እንዲጫወቱ ውሳኔ አግኝቷል።


የብዙዓየሁ እንዳሻው ወድቆ የመነሳት ታሪክ (በቴዎድሮስ ታደሰ)

ስም – ብዙአየሁ እደሻው

እድሜ – 28

የትውልድ ቦታ – ጅማ

ቁመት – 1:80

ክብደት – 75 ኪግ

ክለብ – ጅማ አባቡና


የእግርኳስ ህይወቱን በኮፓሽን ፕሮጀክት የጀመረው ብዙዓየሁ በመቀጠል በጅማ ከተማ አንድ አመት ቆይታ አድርጎ ወደ አየር ኃይል አመራ፡፡ በአየር ኃይልም ለስድስት ወራት ብቻ ከቆየ በኋላ በወቅቱ ለልምምዳቸውን በደብረዘይት እያደረጉ የሚገኙት ደደቢቶች በችሎታው በመማረካቸው የአዲስ አባባውን ክለብ ተቀላቀለ፡፡ በመጀመርያ የውድድር ዘመንም በደደቢት ከነጌታነህ ከበደ፣ የተሻ ግዛው እና ተመስገን ተክሌ ከፍተኛ የመሰለፍ ፉክክር የገጠመው ብዙዓየሁ በ2002 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከቡድኑ ጋር አሸናፊ ከሆነ በኋላ ባጋጠመው  የረጅም ግዜ ጉዳት ለክለቡ ብዙም  ግልጋሎት ሳይሰጥ በስምምነት ከሰማያዊዎቹ ጋር ተለያየ፡፡ ጉዳቱን ለማስታመም ወደ ትውልድ ከተማው ወደ ጅማ ከተመለሰ በኃላ በቀድሞ አደረጃጀት ብሄራዊ ሊግ በአሁኑ ከፍተኛ ሊግ ለሚጫተው ለቀድሞ ቡድኑ ለጅማ ከተማ ለአንድ አመት ፈረመ፡፡ በቡድኑ ውስጥም ለቡድኑ ወሳኝ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ግባር ቀደሙ ነበር፡፡

በግዜው የጅማ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት አረጋይ ወንድሙ ወደ ደሴው ጥቁር አባይ በማምራታቸው ከሳቸው ጋር ለጥቁር አባይ ከፈረመ በኃላ ነበር የእግር ኳስ ህይወቱ መቀያየር የጀመሩት፡፡ በዲስፕሊን ችግር ከጥቁር አባይ ተሰናበተ በኃላ በብስጭት የአልኮል ሱስ ውስጥ በመዘፈቁ ሁለት አመታትን ያለስራ ከእግርኳስ እቅስቃሴ በመራቅ አስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረዶችን እንዲሁም ፈታኝና ተስፋ አስቆራጭ  አመታትን እዳሳለፈ ይናገራል፡፡ ‹‹ ኳስን ከመጫወት ከመከታተል ራሴን አርቄ ቆየሁ፡፡ ነገር ግን ከጊዜ በኃላ ያለሁበት ሁኔታ ለጤንነቴም ለህይወቴም እደማይጠቅመኝ ተረዳሁ፡፡ ስለዚህ በግሌ ልምምዶችን ማድረግ ቀጠልኩ፡፡  ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤና ቡድኖች ጋር ጨዋታ ማድረግም ጀመርኩ፡፡ በአንዱ ቀን ጨዋታ እያደረግን አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዩሀንስ ተመልክቶኝ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሙከራ እድል ሰጥቶኝ የሙከራዬም ግዜ አመርቂ ስለነበር የሁለት አመት ኮንትራት ፈርሜያለሁ ፡፡

ብዙአየሁ እዳሻው (ወሮ) ጅማ አባቡናን ከተቀላቀለ በኃላ በመጀመርያው ዙር የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ከጅማ አባቡና 3ኛ ጀረጃን ይዞ የመጀመርያውን ዙር እንዲያጠናቅቅ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል፡፡ በክለቡም በከፍተኛ ሊጉም ከቡድን አጋሩ ቴዎድሮስ ታደሰ ጋር በ6 ጎሎች ፉክክሩ ውስጥ ያለ ሲሆን በእንቅስቃሴ ረገድም በየሳምንቱ ወጥ አቋም ከሚያሳዩ ተጫዋቾችን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ብዙአየሁ እደሻሁ ከዚህ በኃላ ከጅማ አባቡናጋር ስኬትን ያልማል፡፡ ‹‹ማንም ሰው ሊሳሳት ይችላል፡፡ ነገርግን ስህተትን አውቆ መታረምና ስህተትን አለመድገም ነው ትልቁ ነገር፡፡ ለታዳሚዎች እንዲሁም ለሌሎች ተጫዋቾች የማስተላልፈው መልዕክት ዲሲፕሊን እንዲኖራቸው ነው፡፡ ለእግርኳሱ ትልቁ ነገር ዲስፕሊን ነው ፤ ጊዜው የፉክክር እንደመሆኑ ትንሽ ስህተት ዋጋ ታስከፍላለች፡፡ ስለዚህ ራሳቸውን ጠብቀው ጥሩ እንዲሆኑ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ በመጨረሻም በድጋሚ ወደክለብ እድገባ ትልቁን ድርሻ ለወሰዱት አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሀንስና ዳንኤል አወቀ አመሰግናለሁ፡፡››