ቡሩንዲ 2018| የኢትዮጵያ ቅጣት ዝርዝር

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግርኳስ ምክር ቤት (ሴካፋ) ቡሩንዲ እያስተናገደችው ባለችው ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ የእድሜ ተገቢነት ላይ ጥያቄ ያነሳባቸው ሃገራት ላይ ቅጣት አስተላልፏል። የቅጣቱ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያ እና ዛንዚባር ናቸው።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ሶማሊያን 3-1 ቢያሸንፍም በጨዋታው ላይ እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች አይደሉም በሚል ሴካፋ ውጤቱን ሰርዞ ለሶማሊያ ፎርፌ ሰጥቷል። የእድሜ ተገቢነት የተነሳባቸው ተጫዋቾች በጨዋታው ላይ ሃትሪክ የሰራው መስፍን ታፈሰ፣ ሬድዋን ነስሩ እና ሙሴ ካንኮ ናቸው። የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ የፈረሙት ደብዳቤ እንደሚያሳየው ሶስቱ ተጫዋቾች ከውድድሩ እንዲሰናበቱ እና ቡሩንዲ በቆዩበት ወቅት የወጣውን ወጪ የሚያካክስ የ5000 የአሜሪካ ዶላር ውድድሩን በፋይናንስ ለደገፈው ፊፋ እንዲከፍል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ላይ ቅጣት ተላልፏል። በተቀጡት ተጫዋቾ ምትክም ቀይ ቀበሮዎቹ ሌሎች ተጫዋቾ ማምጣት አይችሉም። በውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚችሉት እ.ኤ.አ. በጥር 1 2002 በኃላ የተወለዱ ተጫዋቾች ናቸው መሳተፍ የሚችሉት።

የቡድን መሪው ሸረፋ ደልቾ ውሳኔውን በመቃወም ፌድሬሽኑ ይግባኝ ጠይቋል። የፌድሬሽኑ የህክምና ክፍል ሰብሳቢ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ነስረዲን አብዱራሂም ለስፖርት ዞን በሰጡት አስተያየት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተጠያቂ ናቸው የሚለያቸውን ላይ ቅጣት ማስተላለፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

እንደኢትዮጵያ ሁሉ የእድሜ ተገቢነት ጥያቄ የተነሳባት ዛንዚባር 15ሺ ዶላር እና ከውድድር እስከመታገድ ድረስ የሚያደርስ ቅጣት ተበይኖበታል። ዛንዚባር 12 ተጫዋቾቿ የእድሜ ተገቢነት ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።

ኢትዮጵያ በምድብ 1 ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ኬንያን ትገጥማለች። ውድድሩ ታንዛኒያ በ2019 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት ዋንጫ ለማለፍ እንደማጣሪያነት ያገለግላል።

የሴካፋ ሙሉ ደብዳቤ ይህን ይመስላል