ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | የኢትዮጵያ ክለቦች ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ዛሬ ይጠብቃቸዋል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ለመግባት የሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎች ማክሰኞ በአራት አፍሪካ ከተሞች ተጀምረዋል፡፡ ዛሬ ከሰዓት በርከት ያሉ ጨዋታዎች ሲደረጉ የኢትዮጵያ ክለቦች የሆኑት ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ምድብ ለመግባት ወሳኝ የሆነ ግጥሚያን ያደርጋሉ፡፡

ወላይታ ድቻ ከ10 ቀናት በፊት ዳሬ ሰላም ላይ በያንግ አፍሪካንስ የደረሰበትን የ2-0 ሽንፈት ለመቀልበስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ የጦና ንቦቹ ዛማሌክን ከውድድር ካስወጡ በኃላ ባሉት ሳምንታት በተደጋጋሚ በሊግ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ ለአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች የሆኑት እሸቱ መና እና ተክሉ ታፈሰ ከቅጣት መመለስ የተረጋጋ ለማይመስለው የድቻ የተላካይ ክፍል ጥሩ ይመስላል፡፡ ተጋጣሚው ያንጋ በበኩሉ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ ያንጋ ከዛምቢያዊው አሰልጣኝ ጆርጅ ሉዋንዲማና ጋር የተለያየ ሲሆን በምክትሉ ሻድራክ ንሳጂግዋ እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም የሚደረገውን ጨዋታ የሚመሩት ዩጋንዳዊያን አርቢትሮች ናቸው፡፡ ቺላንጌት አሊ እንዲሁም ረዳቶቹ ማርክ ሶንኮ እና ባሊኮዋ ንጎቢ ጨዋታውን እንዲመሩ በካፍ ተሸመዋል፡፡ ጨዋታው በደቡብ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ያገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ እሁድ ወደ ብራዛቪል አቅንቷል፡፡ ዛሬ በስታደ አልፎንስ ማሳምባ ደባት በሚደረገው ጨዋታ ፈረሰኞቹ ካራን በአጠቃላይ ውጤት 1-0 እየመሩ ነው፡፡ ለካርሎስ ማኑኤል ቫሽ ፒንቶ ቡድን መልካም ዜና የሚሆነው አስቻለው ታመነ ከቅጣት መመለስ ነው፡፡ ጨዋታውን የሚመሩ ካሜሮናዊያን አርቢትሮች ሲሆን በመሃል ዳኛነት አንቴይን ማክስ ኢፋ ኢሶማ እና ረዳቶቹ እረነስት ኢኮቦ እና ሳዶ ሃምዶ ናቸው፡፡ ፈረሰኞቹ ዓምና ወደ ኮንጎ ሪፐብሊክ አምርተው ሊፖርድስን ዶሊስን በምንተስኖት አዳነ ግብ 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በ2013 ቅዱስ ጊዮርጊስን የግብፁን ኤንፒን አሸንፎ ወደ ምድብ ከገባ በኃላ የኢትዮጵያ ክለቦች ወደ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምድብ አልፈው አያውቁም፡፡ ካፍ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ የምድብ ድልድል በመጪው ቅዳሜ ካይሮ ላይ የሚያወጣ ሲሆን እስካሁን ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር)፣ ዩኤስኤም አልጀር (አልጄሪያ) እና አል መስሪ (ግብፅ) ወደ ምድብ ያለፉ ክለቦች ናቸው፡፡

ዘገባውን ስፖንሰር ያደረገው ሴንትራል ሆቴል ሀዋሳን እናመሰግናለን!