ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ደደቢት ነጥብ ሲጥል አዳማ በግብ ተንበሽብሿል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል። ደደቢት ከመመራት ተነስቶ ከሀዋሳ ነጥብ ሲጋራ አዳማ ከተማ በጌዲዮ ዲላ መረብ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎል አዝንቧል።

በአዲስ አበባ ስታድየም 08:00 ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ደደቢት 2-0 ከመመራት ተነስቶ አቻ ተለያይቷል። በመጀመሪያ 45 ከወትሮው በተለየ ተዳክመው የተስተዋሉት ደደቢቶች በግል ስህተቶች በመጀመሪያው 10 ደቂቃ ሁለት ግቦችን አስተናግደዋለ። በ4ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች በረጅሙ የላኩትን ኳስ ወይንሸት ፀጋዬ ኳስዋን እንደመጣች ለማውጣት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ኳሱን ያገኘችው አጥቂዋ መሳይ ተመስገን ፍጥነቷን ተጠቅማ በማለፍ ቡድኗን መሪ ያደረገችውን ጎል ማስቆጠር ችላለች፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት በተመሳሳይ በ7ኛው ደቂቃ የደደቢት ተከላካዮችን ደካማ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጠቅማ ትርሲት መገርሳ የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ያሳደገች ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

ከሁለቱ ግቦች መቆጠር በኃላ ደደቢቶች በመጠኑም ቢሆን መሻሻሎችን አሳይተው የነበረ ቢሆንም እንደወትሮው እምብዛም የግብ እድሎችን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚሁ አጋማሽ የፈጠሯት ብቸኛ የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ የነበረችውም በ26ኛው ደቂቃ ላይ ኤደን ሽፈራው ከተከላካዮች ጀርባ በረጅሙ የጣለችላትን ኳስ ተጠቅማ ሎዛ አበራ ከሀዋሳዋ ግብጠባቂ ጋር 1ለ1 ተገናኝታ ያመከነችው ኳስ ብቻ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ ሀዋሳ ከተማዎች ተደራጅተው በመከላከል አልፎ አልፎ በረጃጅሙ ወደፊት በሚጣሉ ኳሶች የአጥቂዋ መሳይን ፍጥነት በመጠቀም የደደቢት ተከላካዮችን ሲፈትኑ ተስተውለዋል፡፡ መሳይ በተለይም በ46ኛው እና 58ኛው ደቂቃ ላይ ከደደቢቷ ግብጠባቂ ገነት አክሊሉ ጋር 1ለ1 ተገናኝታ ያመከነቻቸው ኳሶች በጣም አስቆጪ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

የጨዋታ የበላይነት የነበራቸው ደደቢቶች በተለይም በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ በቻለችው ብርቱካን ገ/ክርስቶስ አማካኝነት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በ62ኛው ደቂቃም በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ተመስርቶ የሄደውን ኳስ ሰናይት ቦጋለ በጥሩ አጨራረስ ቡድኗን ወደ ጨዋታ የመለሰች የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት የደደቢቶችን ተስፋ ልታጨልም የምትችለውን አጋጣሚ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል መሳይ ከሳጥን ውጪ አክርራ ብትመታም ኳሷን የግቡ አግዳሚ ሊመልስባት ችሏል፡፡
በቀሩት ደቂቃዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ደደቢቶች በስተመጨረሻም በ85ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ባስቆጠረቻት ግብ በሜዳቸው ሽንፈትን ከማስተናገድ ሊድኑ ችለዋል፡፡

አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ጌዴኦ ዲላን አስተናግዶ 6-2 በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል። ሴናፍ ዋቁማ ባንፀባረቀችበት ጨዋታ 4 ጎሎችን በማስቆጠር ለቡድኑ ድል ከፍተኛውን ድርሻ ስትወስድ አስካለ ገብረፃድቅ እና ሰርካዲስ ጉታ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል። ሳራ ነብሶ እና ትንቢት ሳሙኤል ደግሞ ለጌዴኦ ዲላ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።