ቅዱስ ጊዮርጊስ በሪቻርድ አፒያ ላይ ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አገኘ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ያስፈረመው ጋናዊው አጥቂ ሪቻርድ አፒያን ዝውውር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስም ዝውውሩ በተቀመጠው አሰራር መሰረት የተከናወነ ነው በሚል ይግባኝ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ፌዴሬሽኑም በድጋሚ ተመልክቶ የተጫዋቹን ዝውውር አፅድቋል።

ፌዴሬሽኑ የሪቻርድ አፒያን ዝውውር ውድቅ ያደረገው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከተዘጋ በኋላ የፈረመ በመሆኑ ምክንያት መሆኑ ቢገለፅም ተጫዋቹ ከኦገስት ጀምሮ ክለብ አልባ የነበረ በመሆኑ እና በፌዴሬሽኑ የዝውውር ህግ መሰረትም ከኦገስት ወዲህ ክለብ የሌለው ተጫዋች ከዝውውር መስኮቱ መጠናቀቅ በኋላም የመፈረም መብት ያላቸው በመሆኑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲፈርም እንደተፈቀደለት ተገልጿል።

ጋናዊው አጥቂ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቀላቀል መፈቀዱን ተከትሎ በዛሬው እለት ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ላይ የመሰለፍ እድል ቢኖረውም የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን ባለማጠናቀቁ የማይሰለፍ ይሆናል።