ሪፖርት | የሙሉዓለም ወሳኝ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስን የሸገር ደርቢ አሸናፊ አድርጎታል

ተጠባቂ የነበረው የዘንድሮው አመት የሁለተኛ ዙር የሸገር ደርቢ በሙሉአለም መስፍን የመጨረሻ ደቂቃ የግንባር ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስን የ1-0 አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ብራዛቪል ላይ በመለያ ምት ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በተሰናበተበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ የተጠቀመባቸውን ተጨዋቾች ይዞ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ግን ወልዋሎ ዓ.የን 2-1 ከረታበት ጨዋታ የሶስት ተጨዋቾች ለውጥ አድርጓል። ቅጣት ላይ የሚገኘው ወንድይፍራው ጌታሁን ፣ ኤልያስ ማሞ እና ኃይሌ ገብረትንሳይ ለውጥ የተደረገባቸው ተጨዋቾች ሲሆኑ አክሊሉ አያናው ፣ መስዑድ መሀመድ እና ባፕቲስቴ ፋዬ ተተክተዋል። በለውጡ መሰረትም አስራት ቱንጆ ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት እንዲሁም የፋዬን መግባት ተከትሎ ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ መስመር አጥቂነት ሚና ተሸጋሽገዋል።

ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በጥቂቱ መነቃቃት የታየበት ቢመስልም በሙሉ የጨዋታ ጊዜው ከተጠበቀው እጅግ የወረደ እንቅስቃሴ የታየበት እና በቁጥር የተመናመኑ ሙከራዎችን የተመለከትንበት ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሳምሶን ጥላሁን ከቅጣት ምት እንዲሁም በባፕቲስቴ ፋዬ የግንባር ኳስ ሁለት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሊቀጥሉበት ግን አልቻሉም። ቡድኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ኳስ ከኃላ መስርተው እንዳይወጡ ያደርግ በነበረበት መንገድ ስኬታማ ቢሆንም ከዚህ እንቅስቃሴ የሚገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ግብ ሙከራነት መቀየር ግን ተስኖት ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ እያሱ ታምሩ ከመሀል ሜዳ ገባ ብሎ ያቋረጠውን ኳስ ለሳሙኤል ሳኑሚ አሳልፎለት የነበረ ቢሆንም የሳኑሚ ሙከራ በግቡ ጎን የወጣ ነበር። ከዚህ ውጪ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የታዩት ሙከራዎች ወደ ባፕቲስቴ ፋዬ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ላይ የተመሰረቱ እና ውጤታማ ያልነበሩ ናቸው።

በቅብብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ መግባት ተቸግረው የታዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም እንዲሁ ስኬታማ የማጥቃት ሂደትን መፍጠር አልቻሉም። ፈረሰኞቹ በሁለቱ መስመሮች በተለይም ትዕግስቱ አበራ በመስመር ተከላካይነት በተሰለፈበት የቡና የግራ ወገን ሰብሮ የመግባት አጋጣሚዎችን ሊያገኙ ሲቃረቡ ቢታዩም 20ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ አሻምቶት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ለጥቂት ሳይጠቀሙበት ከቀሩት ኳስ ውጪ ሀሪሰንን መፈታን የቻሉት በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነበር። ይህም የሆነው 45ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ አክርሮ ወደ ግብ ሲመታ ቢሆንም ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሳይቸገር በቀላሉ ይዞበታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ሁለት ደቂቃዎች እንዳለፉ አሜ መሀመድ በቀኝ መስመር በመግባት ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር 50ኛው ደቂቃ ደግሞ ለቡናማዎቹ ምርጡ በነበረው የግብ ሙከራ ሳጥን ውስጥ ባፒስታዬ ፋዬ ያመቻቸለትን ኳስ መስዑድ መሀመድ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ሮበርት ኦዱንካራ በአስደናቂ ቅልጥፍና አድኖበታል። ከነዚህ ሙከራዎች በኃላ ግን ጨዋታው ወደ ነበረበት መቀዛቀዝ ተመልሷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች እያሱ ታምሩን ወደ መስመር ተከላካይ ቦታ በመውሰድ ትዕግስቱ አበራን በአስቻለው ግርማ ተክተው የማጥቃት ሀይላቸውን ለማጠናከር ቢሞክሩም 56ኛው እና 79ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ቅያሪውን ባደረጉበት የግራ መስመር ላይ ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ቢያገኙም በቅብብል ስህተቶች ወደ ሙከራነት መቀየር አልቻሉም። በተለይም 79ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ በሚገርም ሁኔታ ከሁለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ታግሎ በማስጣል ወደ ፊት የላከው ኳስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በቁጥር በልጠው እስከ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ድረስ እንዲጠጉ ዕድል የፈጠረላቸው ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ተቸግረውበት የነበረውን ኳስ መስርቶ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ የመግባት ሂደት አሻሽለው የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአሜ መሀመድ ሙከራ በኃላ ሌላ ዕድል ባይፈጥሩም የጨዋታውን ፍጥነት ጨምረው ለመጫን ሞክረዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማን በጋዲሳ መብራቴ ቀይተው ካስገቡ በኃላ ደግሞ ዳግም ሙከራዎችን ማግኘት ችለዋል። ወደ አሜ መሀመድ ተጠግቶ በጥሩ አቋቋም ኳሶችን ይጠብቅ የነበረው አዳነ በ77ኛው እና 85ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች ኢላማቸውን ባይጠብቁም እጅግ አደገኛ ነበሩ። በመቀጠል አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ በሌላኛው ቅያሪያቸው አበባው ቡታቆን ወደ ሜዳ ሲያስገቡ በተቀሩት ደቂቃዎች በተሻጋሪ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እንዳሰቡ ያስታውቅ ነበር። በመሆኑም አበባው አስራት ቱንጆ ላይ ደርቦ ወደ ማዕዘን ምትነት የቀየራትን ኳስ ራሱ አሻምቶ ሙሉአለም መስፍን በ88ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ በማስቆጠሩ ፈረሰኞቹ ሶስት ነጥቦችን ይዘው መውጣት ችለዋል። ግቧ ስትቆጠር የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ደካማ የቆመ ኳስ የመከላከል መንገድን በግልፅ ያሳየ ነበር።

ለተመልካች ሳቢ ያልነበረው ጨዋታ በዚህ መልኩ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 33 በማድረስ ወደ ሶስተኛነት ከፍ ሲል ኢትዮጵያ ቡና ወደ 5ኛ ደረጃ ለመውረድ ተገዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ደጋፊዎችም ሆኑ ተጨዋቾች እርስ በእርስ መከባበራቸው የሚያስደስት ነበር። የቡናውን አጥቂ ባፕቲስቴ ፋዬን አንጎላ ሳለሁ ስላሰለጠንኩት በሚገባ አውቀዋለው። የቡና ተጨዋቾች ለርሱ ራጃጅም ኳሶችን በማድረስ ሁለተኛ ኳሶችን ለመጠቀም ሞክረው ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ ክፍተት ሰጥተናቸው የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ክፍተት ነፍገናቸው ጨዋታውን ተቆጣጥረን በማሸነፍ ወጥተናል። ብራዛቪል ላይ በሳምንቱ አጋማሽ ከባድ ጨዋታ አድርገን እና ረጅም ርቀት ተጉዘንም ጭምር ይህን ጨዋታ ማሸነፋችን በጣም አስደሳች ነው።

አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

ውጤቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። ጥሩ የቴክኒክ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች የያዘውን ተጋጣሚያችንን በልጠን ተጫውተናል። በጨዋታው ላይ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ብንሰራም ግቡ ሲቆጠርብን ትኩረታችንን አጥተን ነበር። የማዕዘን ምቱ ሲሻማ አንድ ተጨዋቻችን ተጎድቶ የነበረ በመሆኑ በቁጥር አንሰን ለመከላከል ተገደን ነበር። ከዛ ውጪ ግን እኛም ጥሩ የማግባት ዕድሎችን ሳንጠቀም ቀርተናል በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ። በመጀመሪያው አጋማሽም ቢሆን የተሻለ ተጭነናቸው ነበር። በሁለተኛው ግን ኳሱን ስለያዙት እና ብዙ እንድንሮጥ ስላደረጉን ከባድ ነበር።