የአሰልጣኞች ገጽ – ሰውነት ቢሻው [ክፍል 3]


የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን። የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ቃለመጠይቅ በክፍል አንድ እና ሁለት ይዘን መቅረባችን ይታወሳል።

የዛሬው የክፍል ሶስት መሰናዷችን ደግሞ ስለ አሰልጣኝነት ስራ ካለፈው የቀጠለ እና ስለወጣቶች እግርኳስ ትኩረት አድርጓል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


የአሰልጣኝነት ስራን ከመጀመርህ በፊት በአርአያነት ተከትለህ ሙያውን እንድትጀምር ያደረገህ አሰልጣኝ አለ? ወይስ በመምህርነት ሙያህ መስራት ኖሮብህ ወደ ሰቆጣ በመሄድህ በልጅነትህ ያለምከውና ያላሳካኸው የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የመሆን ነባር ውስጣዊ ፍላጎትና ቁጭት በቂ ነበር?

★እኔ ታዋቂ አሰልጣኝ አላሰለጠነኝም፡፡ በእርግጥ በተለያየ ጊዜ በእነርሱ አማካኝነት የሚሰጡ ትምህርቶችን የመከታተል እድል አግኝቻለሁ፡፡ በምስራቅ አፍሪካ አገሮች የነበሩ አሰልጣኞች እዚህ አዲስ አበባ መጥተው የፊፋ Pilot Project Seven የሚባል ኮርስ ልንወስድ ስንል መንግስቱ ወርቁና ታደሰ ገ/መድን (ሁለቱንም ነፍስ ይማርልን!) ለመነሻ የሚሆን ነገር አስተምረውኛል፡፡ በክለብ ደረጃ ያሰለጠነኝ አንድም ትልቅ አሰልጣኝ አልነበረም፡፡ በክልሎች በነበረኝ ቆይታዬም በወሎ የመምህራን ቡድን ውስጥ እርስ በእርሳችን ነበር የምንሰለጣጠነው፡፡ በቃ ሻል ያለ ሰው ይነሳና ያሰለጥናል፡፡ በጎጃምም ቢሆን ወደ ባህርዳር ከሄድኩኝ በኋላ ያኔ ፔዳጎጂ ዲፓርትመንት ውስጥ እነ ጋሽ አባይነህ ደስታና አቶ ነጋልኩ አፈወርቅን የመሳሰሉ የስፖርት መምህራን እግርኳስ ያሰለጥኑን ነበር፡፡ እኔም እንደዚሁ አብሬ እየተጫወትኩ አሰለጥን ነበር፡፡ ደብረ ማርቆስ እያለው ተማሪ ሆኜ በሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲጫወት “መንግስቱ ለሉቻኖ ሰጠው…..፤ ሉቻኖ ለኢታሎ አሳለፈለት…..፤ ኢታሎ መልሶ ለሉቻኖ…..፣ ሉቻኖ ለክፍሎም…..፣ ክፍሎም በረጅሙ መታ…….” የሚለውን የእግርኳስ ቀጥታ ስርጭት በሬዲዮ እሰማ ነበር፡፡ መንግስቱን፣ ሉቻኖንና ሌሎቹንም ያወኳቸው በመልክ አይቼ ሳይሆን ስለነሱ የሚባለውን በሬድዮ ሰምቼ ነው፡፡ በውድድሩ ሉቻኖና መንግስቱ ጎሎችን ያስቆጥሩ ነበር፡፡  ‘እኔም እንደነ መንግስቱ ኳስ መጫወት አለብኝ፡፡’ የሚል ፍላጎት ውስጤ ሰረጸ፡፡ ብሄራዊ ቡድን ለመጫወት አልፎም ለማሰልጠን ያገኘሁትን ፍላጎት ውስጤ እንዲገባ ያደረገው ይኸው የልጅነት ምኞቴ ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ አስተማሪ ሆንኩኝና ወደ ክልል ስሄድ በተጫዋችነት ብሄራዊ ቡድንን ማለም የማይታሰብ ሆነ፡፡ በክለቦችም በትልቅ አሰልጣኝ ስር ሳልሰለጥን ቀረሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋሽ ሽፈራው አጎናፍር የሚባል የስፖርት ዲፓርትመንት ሀላፊና መምህር  የዩኒቨርሲቲውን የእግርኳስ ቡድን ሲያሰለጥን እኔ ስፖርት ሳይንስ ባላጠናም እዛም እጫወት ነበር፡፡  ስለዚህ በአሰልጣኝነት በትልቅ ደረጃ የመሰልጠን እድል ስላልነበረኝ በኳስ ተጫዋችነት እንደ አርአያ የወሰድኩት እነ መንግስቱ ወርቁን ነው፡፡ 

ከውጪ አገር አሰልጣኞች ለእግርኳስ ባለው አተያይና የቡድን አመራር ፍልስፍናው የበለጠ የሚስብህ አሰልጣኝ ማን ነው?

★እኔ የአለም ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾችን መርጠህና የተዋጣላቸውን ተጫዋቾች ሰብስበህ አሸነፊ መሆንን እንደ ትልቅ ስኬት አላይም፡፡ መጠነኛ ደረጃና ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ሰብስቦ ለውጤት የሚበቃውን አሰልጣኝ የበለጠ አደንቃለሁ፡፡ 


እግርኳስ ፌዴሬሽኑ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቅጥር ውል የሚፈጽመው የነጥብ ውድድሮች ሲቃረቡ ነው፡፡ ቡድኑ የሙሉ ጊዜ አሰልጣኝ የማይኖረው ጊዜም አለ፡፡ እናንተም ስትቀጠሩ ሐላፊነቱን ከክለብ ስራ ጋር ደርባችሁ ስትሰሩ ይታያል፡፡ ሙሉ ጊዜውንና ትኩረቱን ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሰጥን አሰልጣኝ አለመቅጠር በውጤታማነት ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ምንድን ነው? 

★ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድን ሁሌም ቢሆን አሰልጣኝ ሊኖረው ይገባል፡፡ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን የሴቶች፣ የወጣትና ታዳጊ ብሄራዊ ቡድኖችም ሁሌም ቋሚ አሰልጣኝ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ውድድሮች ኖሩም አልኖሩ በቋሚነት የተቀጠረው አሰልጣኝ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ተጫዋቾችን ይመለምላል፡፡ ታዳጊዎችን ያያል፤ በተለያዩ ቀናት አዳዲስ ብቅ ብቅ የሚሉ ወጣቶችን እየሰበሰበ ስልጠና ይሰጣል፤ የራሱን እቅድ ይነድፋል፤ በአገሪቱ የእግርኳስ እድገት ውስጥ ባሉ ስራዎች አሻራውን ያሳርፋል፡፡ አሰልጣኙ እና ተጫዋቾች የተበጣጠሰ እና በየጊዜው የሚቀጣጠል ግንኙነት እንዳይኖራቸው ቋሚ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድን ተጫዋቾች ከአርባምንጭ መርጬ ከሆነ ልጁን ባለበት አካባቢ እየሄድኩ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አየዋለሁ፤ ስለዚህ ከተጫዋቹ ጋር በዚህ መንገድ ዘላቂ ግንኙነታችንን አስቀጠልን ማለት ነው፡፡ ዋናው ነገር ደግሞ የውህደት ጊዜ ማግኘቱ ነው፤ በእረፍት ወቅት ተጫዋቾችን እየጠራህና የወዳጅነት ጨዋታዎችን እያደረክ ወቅታዊ አቋምና ውህደትን ትገመግማለህ፡፡ በዚህ ጊዜ ተጫዋቾችም ስነልቦናዊ የሆነ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ለራሳቸው ‘እኔ እኮ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ነኝ፡፡’ የሚል እምነት ይኖራቸዋል፡፡ አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ “ልቀነስ እችላለሁ፡፡” የሚል ስጋት ሳይኖርባቸው በማንኛውም አሰልጣኝ ላይ ያልተመሰረተ ትጋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ቡድኑም የተላመደ መንፈስ ይኖረዋል፡፡ ሁሌም የማይገባኝ አሰልጣኙ ለምንድነው ለሶስት ወር የሚቀጠረው? ገንዘቡ አለ አይደል እንዴ! ለምን ለአራት አመት አይፈርምም? መቼም አንድ አሰልጣኝ የሚከፈለው ገንዘብ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑን በጀት አያናጋውም፡፡ አሰልጣኙ የረጅም ጊዜ እቅዱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን ጊዜ በመስጠት እንዲሰራ ማስቻል እና ቡድኑም ቀጣይነቱን ይዞ እንዲዘልቅ ማድረግ ለወደፊቱም ቢታሰብበት መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ 

በአገራችን እግርኳስ ተጫዋቾች “በተፈጥሮ ያላቸው ነገር” ተብሎ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ አነጋገር አለ፡፡ ጥቅል አባባሉን ግልጽ አድርግልን፡፡      “ያለን ነገር” ምንድን ነው?

★ፈጣሪ ሁሉንም ሰው ሲፈጥር ለእያንዳንዱ ጥሩ ጥሩ ነገር ሰጥቶት ነው፡፡ ያንን የተሰጠንን ነገር ደግሞ ወደ ትልቅ ደረጃ ማድረስ የሚቻለው በስራ ነው፡፡ “እኛ ቀጫጮች ነን፤ ተክለ ሰውነት አልተሰጠንም፤ አልታደልንም፡፡” ማለት አግባብ አይደለም፡፡  አንድ ተጫዋች በተክለሰውነቱ ቀጫጫ እንዳይሆን በስንት አመት እድሜው የጡንቻ ማዳበር (Muscle Development) ስራ መስራት ጀመረ? በሳይንሳዊው አካሄድ ተሞክሯል ወይ? 

ሌላው በፕሪምየር ሊጉም ይሁን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ብዙ ጊዜ የቅብብሎች ስህተት እናያለን፡፡ በአስር ሜትር ርቀት ውስጥ የሚደረጉት  ቅብብሎች (simple passes) በቀላሉ ሲቆረጡ (Intercept ሲደረጉ) እናያለን፡፡ ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ቅብብሎችን በትክክል መከወን (Accurately Pass ማድረግ) ያልቻልነውስ በምን ምክንያት ነው? ይሄ ነገር መታየት አለበት፡፡ ተሰጥኦ ቢኖረን ኖሮ ይህን አይነት ስህተት ስለማንሳሳት ስልጠናና ማዳበርም ባላስፈለገው ነበር፡፡ “ባለን ነገር” ቢሆን በተፈጥሮአዊው ቀጫጫ ተክለሰውነታችን ማንንም እየገፈተርን መጣል በቻልን፡፡ ነገርግን ባለን አካላዊ አቅም ከኛ በላይ ጉልበት ያለውን ሰው መገዳደር አንችልም፡፡ ይሄ ሳይንሳዊ እውነት ነው፡፡ በጉልበት የሚበልጠንን ሰው ለመቋቋም ክብደታችንን መጨመር አለብን፤ ጡንቻዎቻችንን ማዳበርና ማጠንከርም ይጠበቅብናል፡፡ እንግዲህ በሳይንሱ ስናየው ከሌሎች ጋር እኩል ነው የተፈጠርነው፤ ሰውነታችን የተገነባውም ከሴሎች፣ ቲሹዎች፣ መስሎችና ሌሎችም ጥቃቅን አካላት ነው ፡፡ 

“የእኛ” የሚባል ነገር የለም፡፡ እኔ ማንም ሰው ያለው ነገር አለኝ፤ ያ ሰው ይሰራበታል፤ እኔ አልሰራበትም፡፡ በቃ የምንለያየው በዚህ ላይ ነው፡፡ 

እኛም ናይጄሪያዊውም ይኸው ነው በተፈጥሮ ያለን፡፡ እውነታው እንዲህ ሆኖ ሳለ “እኛ ሴሎቻችን ውስብስብና ጥቃቅን ናቸው፤ የሌሎቹ ደግሞ ከወፋፍራም፣ትልልቅና ጠንካራ ሴሎች የተሰራ ነው፡፡” ተብሎ መታመን የለበትም፡፡ ሌሎቹ ሰርተው እኛ ደግሞ ስላልሰራን ነው እንደዚህ ደቃቃ ተክለሰውነት የኖረን፡፡ ናይጄሪያዊውም ባይሰራ ኖሮ እንደኛው ቀጫጫ ይሆን ነበር፡፡ እነሱ ሰርተው ይበላሉ፥ እኛ አንበላም፡፡ እነሱ የተሻለ የልምምድ መሳሪያዎች አሏቸው፥ እኛ የለንም፡፡ ልዩነት የሚፈጥርብን ይኸው የስራና የመሳሪያዎች ጉዳይ ነው፡፡ በአዕምሮና በሰውነት እንዲሁም ኳሱን በመፈለግ ረገድ እኩል ነን፡፡ ነገርግን በስራና በመስሪያ ቁሳቁሶች እንለያያለን፡፡ “ናይጄሪያዎች ፈጣኖች ናቸው፤ እኛ ግን አይደለንም፡፡” ይባላል፡፡ እነሱ በተፈጥሮ ፈጣኖቹን ልጆች ይመርጣሉ፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚኖርብን ነገር ይኖራል፡፡ የሰው ልጅ ከአዝጋሚና ቀልጣፋ ወይም ፈጣን የጡንቻ ቀጫጭን ድሮች (Muscle Fibers) ነው የተፈጠረው፡፡ በሩጫው አለም ብናይ እንኳ በቤተ ሙከራ ምርምር ተደርጎበትና በሜዳ ላይ ተገምግሞ አዝጋሚ የጡንቻ ድሮች ያላቸው ስፖርተኞች የማራቶን ሯጮች ይሆናሉ፡፡ ፈጣን የጡንቻ ድሮች ባለቤት የሆኑት ደግሞ በአጫጭር ርቀቶች እና በእግርኳስም ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ በእግርኳስ ብዙውን ጊዜ በመስመሮች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ፈጣኖች ናቸው፡፡ ይበልጡን ፍጥነት በሚፈልገው ቦታ ተጫዋቾችን ለመመደብ እነዚህን ፈጣን የጡንቻ ድሮች ባለቤት የሆኑ ልጆችን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በልምምድ ወቅት ታዳጊዎችን የፍጥነት ስራ ካላሰራናቸው ቀሰ በቀስ በልምምድ ጥቂት መሻሻል ላይ የነበረው ተፈጥሮአዊ ፍጥነት ወደ ቀደመው ደረጃ ይመለሳል (relapse ያደርጋል)፡፡ በሒደትም ወደ አዝጋሚነት ሊቀየር ይችላል፡፡ ተፈጥሮአዊ ፍጥነትን ይዞ ለመቀጠልም ይሁን ይበልጥ ለማሻሻል የግድ ከፍተኛ የፍጥነት ልምምድ ያስፈልጋል፡፡ በተፈጥሮ ፈጣን ያልሆነን ደግሞ በፍጹም በልምምድ ፈጣን ልታደርገው አትችልም፤ ምክንያቱም ሲፈጠርም ያለው ዘገምተኛ የጡንቻ ድር (Slow Muscle Fiber) ስለሆነ፡፡ እንዲህ አይነቶቹ በፍጥነት ተፈጥሮአዊ ድክመት ያለባቸው ግን ደግሞ ጥሩ የእግርኳስ ክህሎትን የታደሉ ተጫዋቾችን በአንጻራዊነት የበዛ ፍጥነትን በማይፈልግ ቦታ ላይ ታሰልፋቸዋለህ፡፡ ሁሉንም ተጫዋች እኮ የግድ ‘ብረር’ አትለውም፤ ባለው ፍጥነት ሌሎች ጥሩ ጎኖቹን ትጠቀማለህ፡፡ ያለውን ፍጥነት ይዞ እንዲቀጥል እያሰራኸው እይታውን፣ ኳስ የማቀበል ክህሎቱን፣ የአካል ብቃቱን ፣ቴክኒካዊ ችሎታውን፣ የታክቲክ አረዳዱን፣ ጨዋታ የማንበብ ብቃቱን፣………….እና ሌሎቹንም አዎንታዊ ጎኖቹን ትጠቀምበታለህ፡፡ ስለዚህ “የእኛ” የሚባል ነገር የለም፡፡ እኔ ማንም ሰው ያለው ነገር አለኝ፤ ያ ሰው ይሰራበታል፤ እኔ አልሰራበትም፡፡ በቃ የምንለያየው በዚህ ላይ ነው፡፡ 

ከዚያ በተረፈ ግን ሁሉም ሰው ቢሰራ ሌላው አለም ላይ የተደረሰበት ደረጃ እንደርሳለን ብዬ ነው የማምነው፡፡ ቀላሉን ምሳሌ ብናነሳ እንኳ “የ<Possession Football> ነው የምንጫወተው፡፡” ይባል የለ እንዴ? እሱን የአጨዋወት መንገድ በትክክል ለመተግበር እኮ ቀድሞ ኳሷ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ያ ካልሆነ መቀባበል፣ ማጥቃትና ጎሎችን ማስቆጠር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ፈጣን ሰዎች ያስፈልጉሀል ማለት ነው፡፡ <Pressing Football> እንላለን፡፡ ፍጥነት ያለው ተጋጣሚህን press ለማድረግ አንተም እኮ ፍጥነት ያስፈልግሀል፡፡ ያለ ፍጥነት Pressing አለ እንዴ? ዝም ብሎ ቃሉን ብቻ መያዝና መደጋገም አይደለም ቁምነገሩ፤ የሚያስፈልገውንም ጭምር ማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ የተጫዋቾቹን ተፈጥሮአዊ የጡንቻ ድር ማወቅ፤ ለዛም የሚያስፈልገውን ስልጠና መስጠትና የሚገባቸው ቦታ ላይ ማጫወት፡፡ እኔ ያለኝ ጃፓኑ አለው፤ ጃፓኑ ያለውም እኔ አለኝ፡፡ የምንለያየው በስራ ነው፡፡

ቀደም ብሎ በብሄራዊ ቡድኑ አሁን አሁን ደግሞ በክለቦችም የውጪ አገር አሰልጣኞች እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ እናንተም አብራችሁ የመስራት እድል ገጥሟችኋል፡፡ በቅርቡ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ከመሆንህ በፊትም በቶም ሴንትፌይት ስር ምክትል ሆነህ ነበር፡፡  ከእነርሱ ሊገኝ የሚችለው ነገር ምንድን ነው? በውጤት ደረጃ ሲመዘንም ያስገኙት የተለየ ነገር የማይኖረው ከአገሪቱ አጠቃላይ የእግርኳስ ስርዓት ጋር ስለማይሄዱ ወይስ ሌላ የተለየ ምክንያት አለ?

★እንግዲህ የሚመጡት አሰልጣኞች ትልልቅ ስብዕና የነበራቸው ከሆኑ ደረጃቸውና ሲሰሩት የነበረው ስራ ትልቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚፈልጉት ግብዓት በፊት ሲሰሩ በነበረበት ስታንዳርድ እንዲሆን ይሻሉ፡፡ የተጫዋቾች ችሎታ፣ የሜዳ ጥራት፣ የልምምድ ቁሳቁሶች አቅርቦት፣ አብረዋቸው እንዲሰሩ የሚመደቡላቸው ሰዎች የእውቀት ደረጃ እና ሌሎችንም ነገሮች በሚሹት መጠን እንዲሟላ ይጠብቃሉ፡፡ ፍላጎቶቻቸው እና የሚቀርብላቸው ነገር በማይመጣጠን ጊዜ ውጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ 

ዝም ብሎ የአሰልጣኝነት ኮርስ ስለወሰደ እና የጤና ቡድን ስላሰለጠነ ብቻ “ብቁ (qualified) ነው፡፡” ብለህ ከወይን እርሻው ላይ አንስተህ አምጥተኸው ከሆነ ደግሞ የሚሰራውን ነገር አያውቅም፤ እቅድም አይኖረውም፡፡ ከዚህ በፊት የመጡ ዝርዝር እቅድ የሌላቸው አሰልጣኞች ነበሩ፡፡ “እቅድህን አቅርብ፡፡” ሲባል ” እቅድ ምን ያደርጋል?” ያለ ስንትናስንት ገንዘብ የሚከፈለው ፈረንጅ አሰልጣኝ ነበረ፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰው የሚመጣው የአገሪቱን እግርኳስ ለመቀየር ሳይሆን እራሱ ሊማርና የስራ ልምድ ማስረጃን ለማደለብ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ የተጫዋቾቹን አቅምና ደረጃ የማያውቅ ማንኛውም ትልቅ ስም ያለው፣ መካከለኛ እና በጅማሮ ላይ ያለ አሰልጣኝ ቢመጣም ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በመደመሪያ አንድ አሰልጣኝ የሚያሰለጥናቸውን ተጫዋቾች ማወቅ አለበት፡፡ ለስራ መነሻ ትልቁ ግብዓት የሚሆነው ተጫዋቾችን ማወቅ ነው፡፡ “ተጫዋቾቹ ይህን ስለሚያሟሉ መነሳት ያለብኝ ከዚህ ነው፡፡” ብዬ ነው ስራዬን መጀመር ያለብኝ፡፡ እንደኛ አገር ባለ እግርኳስ ላይ ምንም ነገር ሳታውቅና ስለምታሰለጥነው ቡድን አስፈላጊ የመነሻ መረጃ ሳትይዝ የምትመጣ ከሆነ አላማህ ደመወዝህና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንጂ የአገሪቷን እግርኳስ መለወጥ አይደለም፡፡ ናይጄሪያ ብትሄድ ተጫዋቾቻቸው በአውሮፓ የሚጫወቱ በመሆናቸውና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ በመገኘታቸው  እነሱን መርጦ ማሰራት በጣም ቀላል ነው፡፡ የእኛን ልጆች ለማሰራት ግን ተጫዋቾቹን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አሰልጣኙን አምጥተህ ብታስቀምጠው ራሱ ተማሪ ነው የሚሆነው፡፡ 

እኔን የገጠመኝ ነገር አለ፡፡ ከሀያ አመት በፊት በሆላንዳውያን የተጻፈ Soccer Conditioning የሚል መጽሀፍ ነበረኝ፡፡ በመጽሀፉ ውስጥ ጥሩ የፍጥነት ልምምድ ማሰሪያ ዘዴ አለ፡፡ ከአስር አመት በፊት አካባቢ ይመስለኛል፦ አንድ ፈረንጅ አሰልጣኝ በዛች ዘዴ ልምምድ አሰርቶ ከጨረሰ በኋላ “እንዴት አየሃት?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ‘በጣም አሪፍ ዘዴ ናት፤ ከአስር አመት በፊት ስለ ልምምዱ አውቃለሁ፤ እንዲያውም የዚህ ልምምድ መመሪያን ከነገጹ ልነግርህ እችላለሁ፡፡’ አልኩት፡፡  ሰውየው ደነገጠ! በወቅቱ ልምምዱ ለተጫዋቾች የሚጠቅም አይነት ቢሆንም ለእኔም ይሁን ለተጫዋቾቹ አዲስ አልነበረም፡፡  አዳዲስ ነገሮችን ይዘው የማይመጡ ብዙ የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው አሰልጣኞች አሉ፡፡ ተጫዋቾቻችን በእኛው አገር አሰልጣኞች የሚያውቋቸውን ነገሮች እንደ  አዲስ ነገር የሚያስቡና የሚያሰለጥኑም አሉ፡፡ ከውጪ አሰልጣኞች ይዘው ከሚመጡት ነገር ይልቅ እዚህ የሚገጥማቸው ይበልጥ እንግዳ ይሆንባቸዋል፡፡ አካባቢው፣ ተጫዋቾቹ፣ ስልጠናው የሚሰጥበት መንገድና ሌሎችም አዳዲስ ነገሮች ይገጥሟቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አላስብም፡፡ በቴክኒካል ዲፓርትመንት ውስጥ የU17፣ U20፣ U23 እና የዋናው ብሄራዊ ቡድኖችን የሚመለከቱ ስራዎች አሉ፡፡ የU17 ብሄራዊ ቡድን ለማዋቀር በአገሪቱ ከ16 አመት በታች ያሉ ታዳጊዎች የሚጫወቱበት ሊግ ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ ሊግ ነው ምርጫ መደረግ ያለበት፡፡ ይህ በእያንዳንዱ የእድሜ እርከኖች ላለ ብሄራዊ ቡድን ይሰራል፡፡ በትክክለኛው እድሜ የሚቀርብ ብሄራዊ ቡድንም ለማዘጋጀት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ የተያያዘ መዋቅር ውስጥ በሚሰሩ ጥራት ያላቸው ስራዎች የዋናው ብሄራዊ ቡድን መጋቢ ቡድን ስለሚያገኝ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህ ዲፓርትመንት የሚሰራ፣ የአስተዳደር ስራዎች ላይ የተካነ፣ እውቀት ያለው፣  የተማረና በዘርፉ ልምድ ያካበተ የውጪ ዜጋ ከመጣ በአገራችን እግርኳስ እድገት ላይ ሊጠቅም ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በየትኛውም አለም እንዳለው ተጫዋቾቹን የሚያውቃቸው አሰልጣኝ ነው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው፡፡ አለበለዚያ ደግሞ ተጫዋቾቹ በፕሮፌሽናል ደረጃ በደንብ የሰለጠኑና ያወቁ መሆን አለባቸው፡፡ በመሆኑም የእኛን አገር ተጫዋቾች በፈረንጅ አገር አሰልጣኝ ማሰራቱ ብዙም ጠቃሚ ጎን የለውም ብዬ ነው የምናገረው፡፡ 

ለረጅም ዘመናት የኢትዮጵያን እግርኳስ ችግሮች መዘርዘር የተለመደ ነው፡፡ በችግሩ ዙሪያ ብዙ የመፍትሔ ሐሳብም ተሰጥቶበታል፡፡ ሆኖም የመፍትሄው ሀሳብ ተግባራዊነት አልፎአልፎ ደግሞ ሀሳቡ ተግባራዊ ተደርጎም የሚታየው ውጤት ያን ያህል የሚታይ አይደለም፡፡ ለዚህ እግርኳሱን የሚመሩት አካላት ምን ይጠበቅባቸዋል?

★በመጀመሪያ እግርኳሱ የማን ነው? መታወቅ ያለበት ነገር እግርኳሱ እኮ የህዝብ፣ የመንግሥት ፣ የባለሙያዎች፣……….የሁሉም ነው፡፡ ለእግርኳሱ የሚመደበው በጀት የህዝብና የመንግስት ነው፡፡ ከጊዮርጊስ፣ ቡና፣ እና ሌሎች በጣት የሚቆጠሩ ክለቦች ውጪ በድርጅት ይዞታ ስር ያሉ ክለቦች በመሆናቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህልውናቸው ከህዝብና ከመንግስት በጀት በሚገኝ ገንዘብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለእግርኳስ በአመት ከ1.5 ቢሊየን ብር በላይ ይወጣል፡፡ እግርኳሱ ግን ወደፊት ፈቅ አይልም፡፡ የእግርኳስ በጀት ባህል ሆኗል፡፡ “ኑሮው ስለተወደደ በጀት አነሰ እኮ!” ይባልና የሚበጀተው ገንዘብ ይንራል፤ እግርኳሱ ግን አብሮ ከፍ አይልም፡፡ ይህንን በጀት የፈቀደው አካል ማን ነው? መንግስት! ታዲያ ይህንን ነገር ለምን አያየውም? እግርኳሱ ላይ ያሉት አመራሮች እነማን ናቸው? በስፖርት ሳይንስና ስፖርት አስተዳደር ዘርፍ የስንት ዲግሪ ባለቤቶች ሆነው የተቀመጡ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እግር ኳስን ተጫውቶ ያለፈና ስለ እግርኳስ ጥሩ ግንዛቤ ኖሮት ቦታውን ያላገኘ ብዙ አካል አለ? እነዚህ አካላት ተገፍተው እግርኳሱ የሚመራው ስለ እግርኳስ ምንም በማያውቁ  ሰዎች ነው፡፡ የገንዘቡ መጠን በየጊዜው እያደገ ይሄዳል፤ ግን ለውጥ የሚያመጣ አመራር የለም፡፡ ስለ እግርኳስ የሚያወራውም ትንሽ ፍላጎት ካለውና በመጠኑ ካነበበ በቃ ያወራዋል፡፡ ሆኖም የሚያመጣውን ተጽእኖ ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፡፡ ለምሳሌ “የእኛ የሆነ ነገር” እና “የእኛ ያልሆነ ነገር” ስለሚባለው ጉዳይም በተጨባጭ ማስረዳትና ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ እግርኳሱን የሚመራው የበላይ አካል መመልከት ያለበት ብዙ ችግር አለ፡፡ ተገቢ ማሻሻያ ካልተደረገም በጀቱ ይበልጥ ያድጋል፤ እግርኳሱም የኋልዮሽ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ 

የብዙሃን መገናኛው አካል ማድረግ የሚኖርበትስ?

★ የሚዲያ ባለሙያዎች የተነገራቸውን ቢያቀርቡ ጥሩ ይሆናል፡፡ Counter Attack , Pressing, Counter Pressing, Fast Break የምትሉት ነገር አለ አይደል? ይህንን የሚናገር ሰው ሜዳ ገብቶ መስራትና ማሳየት አለበት፡፡ እኔ ሰው ያለውን ቃል ይዤ አላወራም፡፡ በምንም አይነት! ምንድነው Counter Attack? መቼ ነው ተግባራዊ የሚደረገው? በምን ሁኔታ ውስጥ እና የት ቦታ ነው የሚጀመረው? እንዳው ዝምብሎ በረጅም መምታት Counter Attack ይሆናል እንዴ?  በህብረትና በፍጥነት ተቀባብለህ መውጣትስ የመልሶ ማጥቃት አይሆንም ወይ? ሶስት የተጋጣሚ ተከላካዮች አጠገብ ላለ አጥቂህ በረጅሙ የምትልከው ኳስ ለተጫዋቹ የመድረስ እድሉስ ምን ያህል ነው? እንደዚህ አይነቱን ነገር ህብረተሰቡ እውነት አድርጎ ስለሚወስደው ወደ ስህተት እንዳንሄድ በጥልቀት አውቀን ብንናገር መልካም ነው፡፡ ሰው የሚያውቀውን ነገር ብቻ እንዲያውቀው ብናደርግ፣ ሙግትና ክርክር ውስጥ ባንገባም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ማንም ሰው ከራሱ አዕምሮ አፍልቆ የሚያመጣው መረጃ አይደለም፤ ኢንተርኔትን በመጠቀም የሚገኝ እንጂ፡፡ ሚዲያ እውቀት አስተላላፊ እንደ መሆኑ የተሻለ እውቀትን ብናስተላልፍ ጥሩ ነው፡፡፡፡ ማንም በራሱ ስለ እግርኳስ አዋቂ አይደለም፡፡ እውቀትን ትፈልጋለህ፤ የሚያውቀውን ትጠይቃለህ፤ ለጥያቄህ መልስን ታገኛለህ፤……ሚዲያው በዚህ መልኩ ቢሰራ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ 

አሁን እየሰራህ ወደምትገኝበት መስክ እናምራ…

★እኔ አሁን ከ 6-17 አመት ያሉ ህጻናትንና ታዳጊዎችን በተለያዩ የእድሜ እርከኖች መድቤ እያሰለጠንኩ ነው የምገኘው፡፡ ልምምዶቹን በተለያዩ አካባቢዎች እና ሜዳዎች ላይ እያከናወንን እንገኛለን፡፡ በአራቱ ቦታዎች ባሉት ሜዳዎች ማለትም በንግድ ባንክ ሜዳ፣ ዊንጌት ት/ቤት ውስጥ ባለው ሜዳ፣ በንፋስ ስልክ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ በሚገኘው ሜዳ እና በኦሜድላ ሜዳ ልጆቹን እያሰራን እንገኛለን፡፡ የስልጠናውን ስራ ከሌሎች ዘጠኝ አሰልጣኞች ጋር በመሆን አብረን እየሰራን ነው፡፡ 

ምንያህል ተስፋ ሰጪ ጎኖችን እያየህ ነው? እስካሁን ያለው የተጫዋቾቹ እንቅስቃሴስ ጥሩ ነገር የሚያስመለክት ነው?

★መቼም ሰው በተፈጥሮው የራሱን ነገር ያደንቃል አይደል! እኔም የማየው እንግዲህ በጣም አሪፍ የሆነና ተስፋ ያለው ነገር ነው፡፡ 

**እየውላችሁ ሳይንሱ “በጣም ትንሽ እድሜ ላይ ለሚገኙ ህጻናት ወላጆች የመጀመሪያው አሰልጣኞች ናቸው፡፡” ይላል፡፡ አያችሁ እናትየው ኳሱን እየመታች ለልጇ ታሳየዋለች፡፡ (ቃለ መጠይቁ እየተደረገ ባለበት አካባቢ መንገዱ ላይ ለልጇ ፕላስቲክ የውሀ መያዣ እየመታች እሱም እንዲመታና እንዲያቀብላት የምታደርግ እናትን ተመልክቶ የተናገረው)

እኔ ‘ልጆቹ ጎበዞች ናቸው፡፡’ እላለሁ፡፡ ከአምስትና ከስድስት አመታት በኋላ በትክክለኛው እድሜያቸው ለU17 በክህሎታቸው የዳበሩና በአግባቡ የሰለጠኑ ወጣቶች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ይቀላቀላሉ ብለን መቶ በመቶ በማመን እየሰራን እንገኛለን፡፡ የምንመለከተውም ነገር ተስፋ ሰጪነቱ እያደገ ነው፡፡ እናንተም እንድታረጋግጡ መጥታችሁ እዩ፡፡ ቅዳሜና እሁድ በሚቀርባችሁ በCMC የባንኮች ሜዳ ካልሆነም በንፋስልክ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሜዳ መጥታችሁ ማየት ትችላላችሁ፡፡ 

በታዳጊ ተጫዋቾች እድገት ሒደት ውስጥ ወሳኙ ነገር ምንድን ነው? እናንተ ለስልጠናው አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች የተማራችሁና ሰፊ የማሰልጠን ልምድ ያላችሁ አሰልጣኞች ናችሁ፡፡ ሆኖም በከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት በየሰፈሩ ህጻናትን ሰብስበው ለሚያሰለጥኑት ሰዎች የሚሆን ምክር ብትሰጥልን…

★ልክ ነው፡፡ በየትኛውም ቦታ ላይ ያለው የማሰልጠን ፍላጎት ጥሩ ነው፡፡ ነገርግን ሰው የሚሰራውን ስራ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ በየእድሜ ክልሉ ሊሰጡ የሚችሉና ሊሰሩ የሚገቡ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ በየሰፈሩ ባሉ ሜዳዎች መሰልጠኑ ብቻ አይደለም ቁምነገሩ፡፡ ለእያንዳንዱ ተጫዋች የሚሆን ምጥጥን (ratio) አለ፡፡ አንደኛው የተጫዋቾችን ቁጥር እና የሚጠቀሙትን የኳስ መጠን በመጫወቻ ሜዳው ስፋት  (Player:Ball:Pitch)  የሚወስነው ቁጥራዊ መመሪያ ነው፡፡ አሰልጣኞች ስልጠናውን ሲሰጡ በተጫዋቾች ቁጥርና ባላቸው የሜዳ ስፋት ላይ መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡ <መሀል በገባና ድሪብሊንግ> ብቻ ሳይሆን ተገቢ ስፋት ባለው ሜዳ ላይ የጨዋታ ሒደቶችንም መለማመድ መቻል አለባቸው፡፡ ወደ ጎል እየተጠጉም ጎሎችን ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ልምምድ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አሰልጣኙ በየእድሜ ክልሉ መሰራት ያለበትን ነገር በሙሉ ጠንቅቆ ማወቅ ካልቻለ ስልጠናው የማስ ስፖርት ነው የሚሆነው፡፡ ተጫዋቾችም በየእድሜ ክልላቸው ማወቅ የሚኖርባቸውን ሁሉ በጥራት አውቀው ማደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የጫና አሰጣጡ እና የሪከቨሪ መጠኑ ላይም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፤ አለበለዚያ ልጆቹን ማባከን ይሆናል፡፡ ከስራ በኋላ ደግሞ አቅምን ያገናዘበ የአመጋገብ ስርዓትንና እና የምግብ አይነትን ማመጣጠን መቻል ጥሩ ነገር ነው፡፡ በእኛ አገር ባለን አቅም ነው የምንመገበው፤ ሆኖም በተቻለ ሁኔታ ያወጣነውን የካሎሪ መጠን መተካት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ እድገት ተመጣጣኝ ምግቦችን ይፈልጋል፡፡ ተደጋጋሚ ጫና ሰጥተኸው ቤቱ እየሄደ አቅም በፈቀደ የተመጣጠነ ምግብ ካላገኘ  ከመፋፋት ይልቅ እየቀጨጨ ይሄዳል፡፡ ጥሩ የቴክኒክ ችሎታ ታይበትና በአካል ብቃት ደካማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የህጻናትም ሆነ የታዳጊ ተጫዋቾች ስልጠና ሲሰጥ እነዚህ ነገሮች ሁሉ መመጣጠን አለባቸው፡፡ በየሰፈሩ ያሉ ስልጠናዎችን ፍሬያማ ለማድረግም የተሻለ የገንዘብ አቅም ያላቸው ሰዎች ድጋፍ ቢያደርጉ ትልቅ ለውጥና እድገት ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡
 

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ያልተለመደውን  ዘመናዊ የህጻናት ስልጠና እየሰራህበት ትገኛለህ፡፡ በአብዛኛው የሚታወቀው የታዳጊዎች ስልጠና አስራ ሰባት አመት አካባቢ ነው የሚጀመረው፡፡ በአካዳሚ ደረጃ እንኳ ብናየው የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ የሚያሰራው ከ15 እና ከ17 አመት በታች ያሉትን ነው፡፡ በሌሎች አገራት ከማሰልጠኛ ማዕከላት እየወጡ ትልቅ ደረጃ የሚደርሱ ተጫዋቾች ብዙ ናቸው፡፡ከታች በጀመርከው ስልጠና ያንተ ልጆች አስራ ስምንትና ከዚያ በላይ እድሜ ላይ ሲደርሱ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ምን ያህል አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳርፋሉ ብለህ ትጠብቃለህ? “ለውጥ የሚያመጡ ልጆች” ይወጣሉስ ብለህ ተስፋ ታደርጋለህ?

★በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ያሉት ልጆች በራሳቸው መንገድ ነው ያደጉት፡፡ በሰፈራቸው እግርኳስን ሲጫወቱ ከርመው በየክልሉ በተደረጉ ውድድሮች ሻል ያሉት ልጆች ተመርጠው ወጣቶች አካዳሚ ውስጥ ገቡ፡፡ ተጫዋቾቹ በራሳቸው ልምድ ያገኙት እውቀት አለ፡፡ ያንን ይዘው ወደ አካዳሚው መጥተው እስከ አራት አመት ድረስ ተሰጥቷቸው ቢሰለጥኑ ምናልባት ከነጉድለታቸው ለክለቦች ሊያገለግሉና ሊጠቅሙ ይችሉ ይሆናል፡፡ 

<ጉድለታቸው> ስል በተክለ ሰውነት ግንባታ የጡንቻ ማዳበር ስራን በተለይም የእግር፣ የጭን፣ የሆድ ፣ የአንገት እና ሌሎቹን አስራ ሁለቱ የሰውነት ጡንቻዎች ማሳደግና ማጠንከር በሚገባቸው ደረጃ አለመስራታቸውን ነው፡፡ ይህ ልምምድ አስራ አራት አመት እድሜ ላይ ነው መጀመር ያለበት፡፡ ከአስራ ሰባት አመት በኋላ የልጆቹ አካል ቋሚ ቅርጽ ይይዛል፤ ሰውነታቸው ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ የጡንቻ አይነቶች ለማፋፋት ጊዜው ስላለፈ ብትለፋባቸውም ከመሰረቱ ስላልተሰራባቸው የምታገኘው የለውጥ ውጤት ከልጅነቱ በትክክለኛው አሰራር ከመጣው አንጻር ፍጹም የሚቀራረብ አይደለም፡፡ 

አንድ ማረጋገጫ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡ በጋና Right To Dream Academy የሚባል፣ ከአፍሪካ አንደኛ የሆነና በManchester City ሰዎች የሚደገፍ ማሰልጠኛን እንድጎበኝ ተጋብዤ ነበር፡፡ እዚያ የ11 አመት ልጅ በቀን ሁለት ጊዜ ፕሮግራም ወጥቶለት ልምምድ ይሰራል፡፡ የ13 አመቱ ልጅ ደግሞ በሳምንት ሶስት ጊዜ ጂምናዚየም ውስጥ ገብቶ የጡንቻ ማዳበር ስራን ይሰራል፡፡ “በትክክለኛው እድሜ ተገቢው ስራ” ማለት ይሄ ነው፡፡ እኛ አገር የትኛውን የአስራ ሶስት አመት ልጅ ነው የጡንቻ ማጠንከር ልምምድ የምናሰራው? እስቲ ንጽጽሩን እንይ፡- የጋናው ሰልጣኝ በአስራ ሰባት አመቱ የሚደርስበት የጡንቻ ማዳበር ስራን እና የእኛው ሰልጣኝ ገና በአስራ ሰባት አመቱ ወደ ጂምናዚየም የሚሄደውን፡፡ በተመሳሳይ የእድሜ እርከን ባሉ ውድድሮች በሰፋ የስልጠና ልዩነት አድገው ሁለቱ ሲገናኙ የሚታየው ጫናን የመቋቋም ሁኔታ ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ምክንያቱም ለአካል ብቃት በሚያስፈልጉ ልምምዶች ተክለ ሰውነቱን አዳብሮ የጨረሰ እና ገና ከተፈጥሮአዊ የሰውነት አለመታዘዝ ጋር የሚገዳደር ጡንቻን የማጎልበት ትግል እየጀመረ ያለ ፉክክር ነውና፡፡ ቴክኒካዊ ጉዳዮችንም ብንመለከት የምናገኘው ተመሳሳዩን ነው፡፡ ቴክኒክን በ17ና በ18 አመትህ ተምረኸው በምንም አይነት መንገድ ልታዳብረው አትችልም፡፡ ከዚህ እድሜህ በኋላ በጨዋታዎች ልታሳድግ የምትችለው የህብረትንና የውህደትን ስራ ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን የመተዋወቂያና የመግባቢያ ጊዜን ይሻል፡፡ መሰራት ያለበትን ነገር በየእድሜ ክልሉ መስራት መልመድ መቻል አለብን፡፡ አሁኑኑም መጀመር ይኖርብናል፡፡ ይህ ካልሆነ እግርኳሳችንን ከፍ ባለ ደረጃ ልናሳድገው አንችልም፡፡ 

ሰልጣኝ ህጻናቱን የምትቀበሉት በምን አይነት መስፈርቶች ነው?

★ማንም ልጅ መምጣትና መሰልጠን ይችላል፡፡ የሚችል፣ የማይችል፣ የወፈረ፣ የቀጠነ፣…..ሁሉም  ፍላጎት ያለው ህጻን መግባት ይችላል፡፡ በህጻንነታቸው ወፋፍራም የሆኑ ህጻናት አሉ፡፡ እነሱ በአንድና በሁለት ወር ውስጥ ክብደት ቀንሰው ሸንቃጣ ይሆናሉ፡፡ ኳሱም እየተመቻቸው ይሄዳሉ፡፡ ምንም የማይችሉትም ከስድስትና ከሰባት ወራት በኋላ በጣም አሪፎች ሆነው ታገኛቸዋለህ፡፡ 

ክፍያውን በተመለከተ ያለው መረጃስ…

★በጣም ርካሽ የሚባል ክፍያ ነው የምናስከፍለው፤ በወር 550 ብር፡፡ አንዳንድ ቦታ ለምዝገባ ብቻ 2500 ብር የሚያስከፍሉ አሉ፡፡ ወርሀዊ ክፍያቸው 1000 ብር የሆነበትም እናውቃለን፡፡ እኛ ለመሀከለኛው ማህበረሰብ ብለን ያቋቋምነው ስለሆነ ክፍያውን ረከስ አድርገነዋል፡፡ ጥሩ ተጫዋቾች ሆነው መክፈል የማይችሉትን ደግሞ በነጻ እናስተምራቸዋለን፡፡ በስፖርት ሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ ያላቸው፣ በካፍ ሲስተም ውስጥ ገብተው A እና B Licence የያዙና በእቅድ የሚመሩ አሰልጣኞች ጋር ነው የምንሰራው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለአሰልጣኞቹ ተገቢ የሆነ ደመወዝ ለመክፈል ወላጆች መጠነኛ ጭማሪ ቢያደርጉ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አሰልጣኞቹን ለመደጎም መቶ መቶ ብር እንኳ ጭማሪ ቢደረግ አሪፍ ነው፡፡ እየተጎዳህም መሰራትም ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ክፍያችን ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ዋናው አላማችን ትክክለኛውን የህጸናት እግርኳስ ስልጠና በተገቢው መንገድ ህጸናቱ እንዲያገኙ ማስቻልና ማስረጽ ነው፡፡ ገንዘቡ ኋላ ይመጣል፡፡ 

ቦታዎቹ የት የት ናቸው?

★ ቦታዎቹ ፡- የንግድ ባንክ ሜዳ-ትልቅ ክብር ነው የምሰጠው ፡፡ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በቃሉ ከአስተዳደር አካላት ጋር በመመካከር በነጻ ፈቀዱልን፡፡ እዚያ ሜዳ ላይ የኪራይ ክፍያ ስለሌለብን ወላጆች ላይ የክፍያ ጭማሪ አላደረግንም፡፡በዊንጌት፣ በጦር ሀይሎች፣ በንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንዲሁም በመካኒሳ እንሰራለን፡፡ ኮንሶላታ የሚባለውና በመካኒሳ ያለው የካቶሊኮች ግቢ ውስጥ የሚገኘው ሜዳ አስተዳዳሪው አባ ታመነ በነጻ እንድንጠቀም ፈቅደውልናል፤ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ከወላጆች ጋር በመማከር ኪራይ በምንከፍልባቸው ሜዳዎች ላይ መጠነኛ ጭማሪ እናደርጋለን፡፡ ዋናው ክፍያ እንድንጨምር የሚያስገድደን ምክንያት በምንሰራባቸው ሜዳዎች የኪራይ ክፍያ መክፈል ስለጀመርን ነው፡፡ በፊት በነጻ ነበር፤ አሁን ግን በወር ለሶስት ሜዳዎች 12,000 ብር እንከፍላለን፡፡ ይሄ እንግዲህ የ24 ልጆች ወርሀዊ ክፍያ ማለት ነው፡፡ የልጆቹ ቁጥር ሲታይ ብዙ ቢመስልም ከዛ ውስጥ በነጻ የምናሰራቸውም አሉ፡፡ ለተለያዩ ቁሳቁሶች መግዣ የሚውል ወጪም አለ፡፡ እስካሁን ድረስ በስራው አትራፊ ሆኜ የተጠቀምኩት ነገር የለም፡፡ በሙያህ ስትሰራና ስትደክም ደግሞ መጠቀም አለብህ፡፡ 

በገሚባ አስተዋውቃቸሁታል?
★ ብናስተዋውቀው ሰው ይበዛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ልንቀበል ከምንችለው በላይ ቢሆንብን የሰው ሃይሉ አነስተኛና በየቦታው የተከፋፈልን ስለሆነ ለማስተዳደር እንቸገራለን፡፡ ከተመሰረተ ከሁለት አመት ተኩል ጊዜ በላይ ሆኖታል፤ በርከት ያሉ ልጆች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም እኛ እስካሁን አላስተዋወቅነውም፡፡ 

ስልጠናው የሚሰጥባቸው ቀኖች የትኞቹ ናቸው?

★ ቀኖቹ ቅዳሜና እሁድ ናቸው፡፡ በCMC የንግድ ባንክ ሜዳ ቅዳሜ ከ2:00-4:00 ሰዓት ሲሆን እሁድ ደግሞ ከ4:00-6:00 ሰዓት ነው፡፡ በዊንጌት በሁለቱም ቀኖች ከ2:00-4:00 ሰዓት ነው፡፡ በመካኒሳ ቅዳሜ ጠዋት ከ4:30-6:30 ሰዓት እሁድ ደግሞ ከ8:00-10:00 ሰዓት ነው፡፡ በንፋስ ስልክ ቅዳሜና እሁድ ከ2:00-4:00 ሰዓት ነው፡፡